ፈልግ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣  

ካርዲናል ፓሮሊን፣ ዩኒቨርሲቲዎች ለዘመናችን ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጡ ይገባል ማለታቸው ተገለጸ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ “ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲዎች በመቶ ዓመታት ውስጥ ለአገር ዕድገት ያበረከቱት የዕውቀት እና የባሕል አስተዋጽኦ” በሚል ርዕሥ በጣሊያን ከተማ ሚላኖ ሲካሂድ ቆይቶ ግንቦት 10/2014 ዓ. ም. በተፈጸመው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። ብጹዕነታቸው በንግግራቸው ዩኒቨርሲቲዎች ለዘመናችን የተለያዩ ጥያቄዎች ልባዊ ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባም አስታውሰዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ለጣሊያን ማኅበረሰብ እና ለቤተ ክርስቲያን የሚያበርክቱትን ከፍተኛ አስተዋፅኦን በገመገሙበት ንግግራቸው፣ የዩኒቨርሲቲዎችን ሚና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አስተምህሮዎች እና ከዓለም ታሪክ ጋር በማዛመድ አስተያየታቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጣሊያን ውስጥ የሚገኝ የቅዱስ ልብ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ መቶኛ ዓመቱን ያከበረው ኅዳር 28/2014 ዓ. ም. ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት መቶ ዓመታት ውስጥ ለጣሊያን ማኅበረሰብ ያበረከታቸው አስተዋፅኦችን እና ተባባሪ መሥራች የሆነች ብጽዕት አርሚዳ ባሬሊ መታወሳቸው ታውቋል። አባ አጎስቲኖ ጄሜሊ እ. አ. አ. በ 1919 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት በጣሊያን ባሕላዊ ሕይወት ላይ ተጽዕኖን መፍጠር ከተፈለገ “የዩኒቨርሲቲዎቻችን መኖር እጅግ አስፈላጊ ነው” ማለታቸውን ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን አስታውሰዋል። 

ከዘመኑ ጋር ያለውን ግንኙነት ማሳደግ

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ለስብሰባው ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር፣ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ፣ ትምህርት በሰው ሕይወት ውስጥ ያለውን አስፈላጊነት እና በዕድገት ላይ የሚፈጥረውን ተፅእኖ በማስመልከት የገለጻቸውን ሃሳቦች አስታውሰው፣ ይህንንም ከዘመኑ የዕድገት ደረጃ እና ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጋር በእያንዳንዱ የሰው ሕይወት ውስጥ ለማስረጽ ፍላጎት እንዳለ ገልጸዋል። ብጹዕነታቸው በማከልም በዘመናዊነት ፈተና ሳይሸነፉ ነገር ግን ዘመኑ ከደረስንበት የዕድገት ደረጃ ጋር ግንኙነትን መፍጠር የካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲዎች የመጀመሪያ ጥረት መሆኑን አስረድተው፣ በዚህ የቤተ ክርስቲያን ልዩ አገልግሎት በመመራት፣ ለዕውቀት ያለውን ጉጉት ሳያባክኑ መንፈሳዊነትን ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ትችቶች ሚብራሪያን የሚያገኙበት ቦታ

“እምነት ዛሬ ከዘመኑ የዕድገት ደረጃ ጋር የሚደራደርበት አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሎን፣ ማኅበረሰባችንን የተለያዩ ቀውሶች ሲያጋጥሟቸው ዩኒቨርሲቲዎች የትችቶች ማመሳከሪያ ቦታ ሆነው እንደሚያገለግሉ ገልጸው፣ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን ልዩ ገጽታ ሲዘረዝሩ፣ ከዘመኑ ጋር በሚደረግ ውይይት ውስጥ የሰው ልጅ የደረሰበት ንቃተ ህሊና፣ እውነት ፍለጋ የሚጠቀምባቸውን አሳማኝ ሥነ-ምህዳራዊ እና ስነ-ልቦናዊ እይታን የሚያካትት መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው፣ እምነት ማለት ሰው ለመኖር በተጠራበት በማንኛውም ቦታ እና ጊዜ፣ የሚያመሰግንባቸውን ምክንያቶች በማወቅ፣ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ተስፋ ማድረግ ነው" በማለት አስረድተዋል።

ንቆ የመተው ባሕል

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ እ. አ. አ በ1990 ዓ. ም. “ከቤተ ክርስቲያን ልብ” በማለት ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ድንጋጌ ውስጥ፣ ምሁራዊ አቀራረብ ነፃ እና ራሱን በቻለ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚያቀርበው ወሳኝ የጥናት ውጤት፣ ሰብዓዊ ክብርን እና ባሕላዊ ቅርሶች ለመጠበቅ እና ለማሳደግ፣ ለማጥናት፣ ሌሎችን በማስተማር ለአከባቢው ማኅበረሰቦች፣ ለአገር እና ለዓለም ዕድገት የሚሰጠው እገዛ እንዳለ መግለጻቸው ይታወሳል። በዓለም ፖለቲካ ውስጥ ለውጦች የተደረጉባቸው 80ዎቹ እና 90ዎቹ ዓመታት ዩኒቨርሲቲዎች ዘመናዊው ምርምሮችን ማካሄድ የቀጠሉበት መሆኑን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ እ. አ. አ. በ 2000 ዎቹ ዓመታት ውስጥ "ሌላውን ችላ የማለት እና የማግለል ስሜት የበላይነትን ያገኘ እንደነበር አስታውሰው፣ ሌላው ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ ድሃ፣ የውጭ አገር ዜጋ፣ ስደተኛ የሚል ገጽታ መንጸባረቅ መጀመሩን አስታውሰዋል። በዚህ ዘመን ውስጥ የታዩት ለውጦች እያንዳንዳችን በድንገተኛ የንብረት መወረስ፣ ከስደት እና ከመንከራተት ሊያተርፈን አልቻለም ብለው፣ በሌላ አገላለጽ የንቀት ባሕል ለሁላችንም አልጠቀመንም ብለዋል። 

"የአስተሳሰብ ጥማት"

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤኔዲክቶስ 16ኛን እና የዩኒቨርሲቲዎች የ2005-2006 የትምህርት ዘመንን መጀመሪያ ተልዕኮን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ዛሬ በስፋት በሚመራው ምክንያታዊ አስተሳሰብ መካከል ሳይንሳዊ ጥናትቶችን ማካሄድ፣ የእግዚአብሔርን ምክንያታዊነት ለማወቅ የተከፈተ ዕድል እንደሆነ ገልጸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ "ምክንያታዊነት ያለው እምነት የዘመናዊ ሳይንስ ምርምር ውጤት ነው” በማለት አጥብቀው መናገራቸውን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል። እግዚአብሔርን የማያውቁ ከሆነ እምነት ሊኖር እንደማችል ገልጸው፣ በመሆኑም የቅዱስ ልብ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ ለኅብረተሰቡ እና ለቤተ ክርስቲያን ያበረከተውን እና እያበረከተ ያለውን አስተዋፅዖ አጠናክሮ እንደሚቀጥ ገልጸው፣ በዘመናችን ውስጥ የአስተሳሰብ ጥማት መኖሩንም አብራርተዋል።

የልብ ጉዳይ

ቤተ ክርስቲያን ከሳይንስ እና ከተለያዩ የእውቀት መስኮች ጋር ለመነጋገር “የተቀደሰ” ቦታ እንደሆነች የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ ነገር ግን የራሷን ሃሳብ አጥብቃ በመያዝ ከሌላው ጋር ለመወያየት ጽኑ ፍላጎት ያላት መሆኑን ገልጸዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ አስተምህሮአቸው፣ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ማኅበረሰብ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት "ያለ ፍርሃት ክፍት ናት" ማለታቸውን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰው፣ ፍርሃት በዛሬው ዓለም ውስጥ ከወረርሽኙ፣ ከኤኮኖሚያዊ ቀውስ ርና በአውሮፓ ውስጥ ካለው ጦርነት ጋር የተያያዘ መሆኑን በማስረዳት፣ “ጥበብን ከተላበሰ ልብ ውስጥ በሚገኝ በጎነት፣ የእምነት ስጦታ የሆነውን ተስፋ መሰጠት ያስፈልጋል” ብለዋል። "ልብ እውነት የሚገኝበት ሚስጢራዊ ቦታ ነው” ያሉት ብጹዕነታቸው፣ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ሁል ጊዜ እና በማንኛውም ሁኔታ ልባዊ ዩኒቨርሲቲ ሊባል እንደሚችል ገልጸው፣ ከልብ የበለጠ ዓለም አቀፋዊ ቅርበት ያለው እና የታማኝነትን ስሜት በተሻለ መንገድ መግለጽ የሚችል ከቅዱስ ልብ ዩኒቨርሲቲ ሌላ እንደሌለ በመግለጽ፣ ተባባሪ መሥራች ለነበረች ብጽዕት አርሚዳ ባሬሊ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ደፋር ልብ፡ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ለምዕመናን በሙሉ የሚሰጠው ውድ ስጦታ እንደሆነ ገልጸው፣ ደፋር ልብ የሌሎችን ጥያቄ በደስታ ለመቀበል ዘወትር ክፍት መሆኑን አስረድተዋል።

19 May 2022, 18:02