ፈልግ

የቤተ ክርስቲያን እናት ወደ ሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም የቤተ ክርስቲያን እናት ወደ ሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም  

የቤተ ክርስቲያን እናት ወደ ሆነች ቅድስት ማርያም ጸሎት እንድናቀርብ ጥሪ ቀረበ

በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ዋና ቆሞስ ክቡር አባ አኜሎ ስቶያ፣ በግንቦት ወር ሙሉ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የሚቀርብ የጸሎት ዕቅድ ለምዕመናን ይፋ አድርገዋል። በሳምንት ሁለት ቀናት፣ እነርሱም ዕሮብ እና ቅዳሜ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እና በባዚሊካው ውስጥ ልዩ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት እንደሚካሄድ ክቡር አባ ስቶያ ለምዕመን ግልጽ አድርገዋል። ከዚህም ጋር በማያያዝ በሰኔ ወር ሊካሄድ ለታቀደው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ ስኬታማነት እና ለዓለም ሰላም ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎት እንድናቀርብ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን ጥሪ አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በግንቦት ወር ውስጥ በሁለቱ ቀናት፣ በተለይም ዕሮብ እና ቅዳሜ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እና በባዚሊካው ውስጥ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎት እንደሚቀርብ የባዚሊካው ዋና ቆሞስ ክቡር አባ ስቶያ፣ በሳምንቱ ውስጥ የተመደቡ ሁለቱ የጸሎት ቀናት በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል የሚታጀቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። በጸሎት ሥነ-ሥርዓቶቹ መካከል የሚቀርብ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እ. አ. አ 1964፣ “የቤተ ክርስቲያን እናት” ብለው የሰየሙት ቅዱስ ምስል መሆኑን፣ ከጥቅምት 11/2014 ዓ. ም. ጀምሮ የባዚሊካው ቆሞስ ሆነው የተመደቡት ፍራንችስኮስዊ ካኅን ክብር አባ አኜሎ ስቶያ ገልጸዋል።

የሮም ሀገረ ስብከት እና የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተዳደር በጋራ ያስተባበሩት ዕቅድ እንዳለ የገለጹት ክቡር አባ ስቶያ፣ ለወሩ በተዘጋጀው የጸሎት መርሃ ግብር መሠረት በሮም ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙ ቁምስናዎች፣ የምዕመናን ማኅበራት፣ ገዳማውያት እና ገዳማውያ በግንቦት ወር በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እና ባዚሊካ ውስጥ የሚቀርበውን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በኅብረት የሚካፈሉ መሆኑን አስረድተዋል። ክቡር አባ ስቶያ አክለውም፣ ባሁኑ ጊዜ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የሚገኘው እና ቀደም ሲልም በቆስጠንጢኖስ ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ዋና ትኩረታቸው እንደሚሆን ገልጸዋል።

በሮም ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ተከብሮ የቆየው የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ምስል፣ ልዩ እንክብካቤ እና ክብር ሲሰጠው የቆየ፣ እ. አ. አ ኅዳር 21/1964 ዓ. ም. የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ፣ በሦስተኛው ዙር የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ፣ እመቤታችን ማርያም “የቤተ ክርስቲያን እናት” በማለት የሰየሟት ምስል እንደሆነች ክቡር አባ ስቶያ ገልጸው፣ የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን ከሚካፈሉ መላው የእግዚአብሔር ሕዝብ እና የሮም ከተማ ነዋሪዎች ጋር በአንድነት ልዩ ትኩረትን በመስጠት ጸሎታቸውን ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

በግንቦት ወር በሚውሉ አራት ቅዳሜዎች፣ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የሚጀምረውን የጸሎት ሥነ ሥርዓት የሚመሩት ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ኮማስትሪ መሆናቸውን ክቡር አባ ስቶያ አስታውቀው፣ በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ሁሉም ምዕመናን እንዲገኙ መጋበዛቸውን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዓለም ሰላም ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎታችንን እንድናቀርብ ደጋግመው መጋበዛቸውን አስታውሰው፣ በቅዱስነታቸው ሐሳብ መሠረት በልዩ ስሜት ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ማርያም ዘንድ ለማቅረብ እንደሚፈልጉ አስረድተዋል።

በሳምንቱ ውስጥ የተመደበው ሌላው የጸሎት ቀን ዕሮብ መሆኑን የገለጹት ክቡር አባ ስቶያ፣ በግንቦት ወር በሙሉ፣ በየዕሮብ ዕለት፣ ከሰዓት በኋላ ከአሥር ሰዓት ጀምሮ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ወደ እመቤታችን ማርያም የሚቀርብ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት መኖሩን አስታውቀዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስሎች መኖራቸውን ክቡር አባ ስቶያ ገልጸው፣ በባዚሊካው ውስጥ የሚቀርብ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የሚፈጸመው ከሰዓት በኋላ በአሥራ አንድ ሰዓት ላይ በሚቀርብ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መሆኑን ገልጸዋል።

በቫቲካን የሚገኝ ታላቁ የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ዓመቱን በሙሉ ንግደት የሚደረግበት ቤተ መቅደስ እንደሆነ የገለጹት ክቡር አባ ስቶያ፣ ቤተ ክርስቲያኑ ለጸሎት የሚጋብዙ በርካታ መንፈሳዊ ምስሎችን እና የሥነ ጥበብ ሥራዎችን የያዘ መሆኑን ገልጸዋል። መንፈሳዊ ታሪኮችን የያዙ ጥንታዊ የጥበብ ሥራዎች በሙሉ ግንኙነታቸው ከአርቲስቶቹ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ በታዋቂው የሥነ ጥበብ ሰው ማይክል አንጄሎ ተቀረጾ በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በክብር የተቀመጠው የምሕረት እናት ምስል፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ለወላዲተ አምላክ ካለው ፍቅር ጋር የተገናኘ መሆኑን አስረድተዋል።

በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሀሳብ መሠረት የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ዋና ዓላማ በተለይ በመላው ዓለማችን ሰላም እንዲሆን እና በመጪው ሰኔ ወር በቫቲካን ውስጥ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ ስኬታማ እንደሆን፣ እንዲሁም በመላው ዓለም የምትገኘውን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ለመንከባከብ እና ለመምራት የሚያስችል ጥንካሬን እና ጤናን ለር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለመለመን መሆኑን በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ዋና ቆሞስ ክቡር አባ አኜሎ ስቶያ አስረድተዋል።  

03 May 2022, 16:47