ፈልግ

አረጋዊያን የማኅበረሰባችን አለኝታ ናቸው!

በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና የሮም ሀገር ስብከት ከሰኔ 15 - 19/2014 ዓ. ም. ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን የጋራ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ሁለቱ ጽሕፈት ቤቶች ለአሥረኛ ጊዜ ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን በዓል በሚያደርጉት ቅድመ ዝግጅት ሰባት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮችን እና ሌሎች ሰባት ምስክርነቶችን በቪዲዮ ምስል ማዘጋጀታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በግል ሕይወት ያጋጠሙ ችግሮችን፣ አዲስ ሕይወት መጀመርን እና እምነትን አስመልክተው ምስክርነታቸውን የሰጡት ምዕመናን በተለያዩ የሞያ ዘርፍ፣ በስፖርት እና በሥነ-ጥበብ ሥራ ተሰማርተው የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል። የሕይወት ምስክርነታቸውን ከሰጡት መካከል አንዱ እና የሮም ከተማ ነዋሪ የሆነው አቶ ሮቤርቶ፣ ጥንታዊ የሮማውያን ባሕል በሚዘረዝር የሥነ-ጥበብ ሥራው፣ አያቶች ተሰባስበው በሚኖር ቤተሰብ ውስጥ የሚጫወቱት ሚና ትልቅ እንደሆነ በሚገልጽ፣ “የፍቅር ውረስ” በተሰኘ አጭር ፊልም ተውኔት ላይ ተሳትፏል።

በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና የሮም ሀገር ስብከት በኅብረት ያዘጋጁት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አያቶችን እና አረጋውያንን ለማበረታታት የተዘጋጀው ሲሆን፣ በተጨማሪም የዕድሜ ባለ ጸጎች በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ተፈላጊነት አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑ ታውቋል። በአቶ አንቶኒዮ አንቶኔሊ መሪነት የተዘጋጀው አጭር የቪዲዮ ፊልም፣ ድረ-ገጽ ላይ ከሚገኙ ሌሎች ፊልሞች ጋር ተዘጋጅቶ ተቀምጧል።           

"አያቶች እና አረጋውያን የቤተሰባችን አካል ናቸው” በሚለው ርዕሥ ሥር የተገለጸው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፣ በዘመናችን እያደገ የመጣውን እና የአረጋውያን ማግለል ስሜትን የሚለውጥ፣ የዕድሜ ባለጸጎች ለቤተሰብ እና ለማኅበረሰብ የሚያበረክቱትን ድጋፍ በመገንዘብ ክብር እንዲሰጣቸው ለማድረግ መሆኑ ታውቋል። “የዕድሜ ባለጸነት ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሽ የሚሰጥበት ተጨማሪ ጊዜ ነው” ያለው አስተምህሮ፣ በዚህም አዲስ፣ ልዩ እና የበሰለ መልስ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጿል።  

የፍቅር ጥሪ በእያንዳንዱ የሕይወት ደረጃ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚቀርብልን ጥያቄ እንደሆነ የሚነግረን የትምህርት ክርስቶስ አስተምህሮ፣ ይህም ማለት አያቶች እና አረጋውያን ከልጆች ፣ ከልጅ ልጆች እና ከወጣቱ ማኅበረሰብ ጋር ባላቸው ግንኙነት ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን ጸጋ በተግባር እንዲኖሩት መጠራታቸውን የሚያረጋግጥ ነው።

የዚህ ጥሪ ምላሽ በሁለት አቅጣጫዎች የተከፈለ መሆኑን የሚገልጸው አስተምህሮ፣ የመጀመሪያው፥ አረጋውያን ያካበቱትን የሕይወት ልምድ ለሌሎች ማካፈል የሚችሉት በተሞክሯቸው፣ በትዕግሥታቸው እና በጥበባቸው አማካይነት እንደሆነ ሲገልጽ፣ ሁለተኛው አቅመ ደካማ የሆኑ አረጋውያን በተቸገሩ እና በደከሙ ጊዜ ከሌሎች ሰዎች ሊቀበሉ የሚችሉትን ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ የሚመለከት መሆኑን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ገልጾ፣ በዚህ መንገድ አረጋውያን ለእራሳቸው እና ለሚያገኟቸው ሰዎች እውነተኛ ዕድገት ተጨማሪ ዕድልን ሊሰጡ እንደሚችሉ ያስረዳል።

18 May 2022, 16:39