ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ዜን ብፁዕ ካርዲናል ዜን  

የብፁዕ ካርዲናል ዜን በፖሊስ መያዝ ቅድስት መንበርን እንዳሳሰባት ተገለጸ

የሆንግ ኮንግ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ዜን፣ ግንቦት 3/2014 ዓ. ም. በአገሪቱ ብሔራዊ የጸጥታ ኃይሎች መያዛቸው እንዳሰጋት ቅድስት መንበር ገለጸች። ብጹዕነታቸው በጸጥታ ኃይሉ የተያዙት፣ በአገሪቱ የሰብዓዊ ዕርዳታን ከሚለግስ የውጭ አገር ድርጅት ጋር ባላቸው ግንኙነት ነው፣ መባሉን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ አስታውቀው፣ ሂደቱን በመከታተል እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዘጠና ዓመት ዕድሜ ያላቸው ብጹዕ ካርዲናል ዜን፣ እ. አ. አ ከ2002 እስከ 2009 ዓ. ም. ድረስ የሆንግ ኮንንግ ጳጳስ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ የተያዙትም ባገለገሉበት ከተማ ባለሥልጣናት መሆኑ ታውቋል። ከሥፍራው የወጡ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘገባዎች ጳጳሱ በዋስ መፈታታቸው አረጋግጠው፣ የፎቶግራፍ ምስላቸውንም በዋን ቻይ ፖሊስ ጣቢያ በራፍ መለጠፋቸው ተመልክቷል። እንደ አገሩ ሰዓት አቆጣጠር ረፋዱ ላይ የተለቀቁት ብጹዕ ካርዲናል ዜን ከፓሊስ ጣቢያው ወጥተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው ተመልሰዋል።

በፖሊስ መያዝ እና የቀረበበባቸው ክስ

የፖሊስ ምርመራ እንደተደረገባቸው የሚገልጹት የአካባቢው ምንጮች፣ ካርዲናሉ በጸጥታ ኃይሎች ሊያዙ የበቁት ሰብዓዊ ዕርዳታን ከሚለግሱ የውጭ ድርጅቶች ጋር በመገናኘታቸው እና ከዚህም በተጨማሪ “612 የሰብዓዊ መረዳጃ ፈንድ” ለተባለ ድርጅት በነበራቸው የአስተዳደር ሚና ጋር ተያይዞ እንደሆነ ተነግሯል።  የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ምላሽ፣ የብፁዕ ካርዲናል ዜን መታሰር ቅድስት መንበርን እንዳሳሰባት ገልጸው፣ ክስተቱን በከፍተኛ ትኩረት እየተከታተሉ መሆኑን ግልጸዋል።

ሌሎች ሦስት የፖሊስ ትዕዛዞች

ብጹዕ ካርዲናል ዜን እ. አ. አ በ2019 ዓ. ም. ተቋቋመው ያለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ከፈረሱ ድርጅቶች መካከል የአንዱ ድርጅት ባለ አደራ እንደነበሩ ታውቋል። ከካርዲናሉ በተጨማሪ የፈንዱን አስተባባሪዎች ጨምሮ ታዋቂዋ ጠበቃ ማርጋሬት ንግ፣ የቀድሞ ተቃዋሚ የፓርላማ አባል፣ ምሁር ሂ ፖ ኪዩን እና የዜማ አቀንቃኝ ዴኒዝ ሆ መታሠራቸውን በሆንግ ኮንግ የሚገኙ ሕጋዊ ምንጮች አረጋግጠዋል።

የተሰጣለባቸው ብይን

የሕግ አስከባሪው ምርመራ ያተኮረው፣ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ የቤጂንግ መንግሥት እ. አ. አ በሰኔ 2020 ዓ. ም. ያጸደቀውን የአገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት ሕግ ጥሰው ከውጭ ሃይሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት እንደሆነ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች የዘገቡ ሲሆን፣ አዲሱ ሕግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውግዘት ማጋጠሙ ታውቋል። በሕጉ የተዘረዘሩት ሌሎች ወንጀሎች፥ መገለል ፣ መገንጠል እና ሽብርተኝነት እስከ እድሜ ልክ እሥራት ሊያደርስ እንደሚችል ታውቋል። ካርዲናል ዜን እ. አ. አ በ2019 ዓ. ም. ተማሪዎች በመንግሥት እርምጃዎች እንዲያምፁ አድርገዋል በሚል ሰበብ ክስ የተመሠረተባቸው መሆኑን፣ በርካታ የሆንግ ኮንግ ሚዲያዎች በቅርቡ መዘገባቸው ሲታወስ፣ ካርዲናል ዜን “የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የሃይማኖት ማኅበረሰቦችን እያሳደደ ነው” በማለት በጥብቅ ሲተቹት መቆየታቸው ይታወሳል። 

12 May 2022, 18:34