ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ ሮም በሚገኝ ቅድስት ሶፊያ ቤተ ክርስቲያን በተከበረው የአውሮፓ ቀን በዓል ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ ሮም በሚገኝ ቅድስት ሶፊያ ቤተ ክርስቲያን በተከበረው የአውሮፓ ቀን በዓል  (Vatican Media)

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ የአውሮፓ የሰላም ዕቅድ ቀጣይነት እንዲኖረው አሳሰቡ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ በሮም ከተማ የሚገኙ የዩክሬን ካቶሊካዊ ምዕመናን ቁምስና በሆነው በቅድስት ሶፊያ ቤተክርስቲያን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። ግንቦት 1/2014 ዓ. ም. የተከበረውን የአውሮፓ ቀን ምክንያት በማድረግ በሮም ከተማ ውስጥ ለሚኖሩ የዩክሬን ካቶሊካዊ ምዕመናን ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባቀረቡት ስብከት፥ ሌሎች ያወደሙትን መልሰው የገነቡ የአውሮፓ አህጉር መሥራች አባቶችን አስታውሰው፣ በዩክሬን ውስጥ ሰላምን እና ስምምነትን ማምጣት እንዲቻል እግዚአብሔር የመሪዎችን ልብ እንዲከፍት በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ግጭት አስፈሪ ቢሆንም፣ አውሮፓ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጥፋት በኋላ ከወደቀበት እንዲነሳ ያደረገው የሮበርት ሹማን ተነሳሽነት እና የሰላም ዕቅድ ዛሬም መቀጠል እንዳለበት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን አሳስበው፣ ጥንታዊው የአውሮፓ አህጉር አሁን ከሚገኝበት የጦርነት አዘቅት ወጥቶ ወደ ነበረበት የሰላም እና የብልጽግና ጎዳና እንደሚመለስ ያላቸውን ተስፋ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ገልጸዋል። ግንቦት 1/2014 ዓ. ም. በተከበረው የአውሮፓ ቀን፣ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ለዩክሬን ሕዝብ ዕርዳታ ማሰባሰቢያ ማዕከል ሆኖ በቆየው በቅድስት ሶፊያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባቀረቡት ስብከት፣ “በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት የብዙ ሰዎች ሕይወት ያጠፋ የጭካኔ ጦርነት ነው” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ  መናገራቸውን አስታውሰዋል።

ለጦርነቱ ሰለባዎች ጸሎት ተደርጓል

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን “ለዩክሬን ሰላምን፣ የጦርነት ሰለባ ለሆኑት በተለይም ለስደተኞች እና ተፈናቃዮች፣ ለሕጻናት፣ ቤት ንብረታቸውን ላጡ እና ያለ ረዳት ለቀሩት በሙሉ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ መጽናኛን ከእግዚአብሔር ዘንድ እንለምናለን ብለው፣ የፖለቲካ ባለ ስልጣናት ሰላም እና ስምምነት ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያስችላቸውን ልብ እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው በማለት፣ በቅድስት መንበር እውቅና የተሰጣቸው አምባሳደሮች በተገኙበት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ተናግረዋል።

ሞት ተሸንፏል!

በዕለቱ በተመደበው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ምስጢር በጥልቅ እንድንገባ በሚረዱን ሀሳቦች ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ስብከታቸው፣ የሞት ስልጣን በመልካሙ እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ መሸነፉን አስታውሰው፣ ሕይወትን የሚሰጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን አስገንዝበዋል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው የዘላለም ሕይወት በሮችን እንደከፈተልን፣ ሞትም ከዚህ በኋላ ኃይል የሌለው እና የተሸነፈ መሆኑን አስገንዝበዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እውነተኛው ሕይወት የምንገባበትን በር የከፈተልን መሆኑንም ገልጸዋል።

"የማይረሳው" የሮቤርት ሹማን መግለጫ

ከዩክሬን የሚመጡ ትዕይንቶች ጦርነቱ ያስከተለውን አሳዛኝ ሁኔታ በየቀኑ እንደሚያስታውሱን የገለጹት ካርዲናል ፓሮሊን፣ በአውሮፓ ውስጥ ሰፊና ደም አፋሳሽ ግጭቶች ከተፈጸሙ ከአምስት ዓመታት በኋላ፣ ማለትም እ. አ. አ. ግንቦት 9/1950 ዓ. ም. የተከበረው የሮቤርት ሹማን የማይረሳ መግለጫን አስታውሰዋል። በወቅቱ የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩ ሮቤርት ሹማን፣ የአዲስ ግጭት አደጋን ለመከላከል ብቸኛው መንገድ ቀዝቃዛ ጦርነትን ማወጅ እና የጦር መሣሪያን የታጠቀ ኃይል ማደራጀት እንዳልሆነ፣ ይልቅስ እርስ በእርስ በመከባበር ሃብትን በጋራ መጠቀም ወደ እውነተኛ እርቅ ሊያደረስ እንደሚቻል መናገራቸውን፣ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል። የአውሮፓ ፌዴሬሽን ለመመሥረት የሚያግዝ ዜዴን መፈለግ የተጀመረው በዚህ መንገድ እንደ ነበር እና "ለረጅም ጊዜ የጦር መሣሪያዎችን ለማምረት የወሰኑ ክልሎች ዕጣ ፈንታ የተለወጠውም በዚህ መንገድ መሆኑን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ለተገኙት ምዕመናን እና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች አስረድተዋል። 

10 May 2022, 16:47