ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ሰመራሮ፥ ቅድስና፣ ትኅትናን እና የልብ ንጽሕናን የሚጠይቅ መሆኑን ገለጹ

በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች የሚከታተል ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪ፣ ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ፣ “ቴሌ ፓቼ” ከተሰኘ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ቅድስና ትኅትናን እና የልብ ንጽሕናን የሚጠይቅ መሆኑን ገለጹ። በቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ግንቦት 7/2014 ዓ. ም. ይፋ የሚደረገውን የአሥር ብጹዓት እና ብጹዓን የቅድስና አዋጅ በማስመልከት ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ቅድስና ማለት በአስቸጋሪ ጊዜ እና ቦታ ላይ ለኢየሱስ ክርስቶስ ጥሪ ምላሽ መስጠት እንደሆነ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ፣ እሑድ ግንቦት 7/2014 ዓ. ም. ይፋ በሚደረግ የ10 ብፁዓን እና ብጹዓት የቅድስና አዋጅ ላይ ለመገኘት ከልዩ ልዩ የዓለምችን ክፍሎች በርካታ ምእመናን ሮም መግባታቸው ታውቋል። ዕለቱን በማስመልከት፣ “ቴሌ ፓቼ” ከተሰኘ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ቴሌቪዥን ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት፣ በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች የሚከታተል ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ፣ ቅድስናቸው የሚታወጅላቸው እያንዳንዱ ብጹዓን እና ብጹዓት፣ በተለያዩ ወቅቶች እና አካባቢዎች፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ነጸብራቅ ሆነው መኖራቸውን አስታውሰዋል። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛን ሐዋርያዊ አስተምህሮን በመጥቀስ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ሰመራሮ፣ ቅድስናን አንድ የሚያደርገው ለኢየሱስ ክርስቶስ ጥሪ መልስ መስጠት እንደሆነ ገልጸው፣ ይህም በተለያየ ጊዜና ሁኔታ ላይ የሚፈጸም መሆኑን አስረድተዋል። በቅዱሳን የስም ዝርዝር ውስጥ ታላቅ የሕይወት ታሪክ እና አቅም የሌላቸው ሰዎች መካተታቸውን የገለጹት ብጹዕነታቸው፣ ይህ ማለት ደግሞ የቅድስና ጥሪ የሚመራው በሥልጣን፣ በሃብት ብዛት፣ በስመ ገናናነት ሳይሆን በቅንነት እና በልብ ንጽህና የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል።

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጥሪ

በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ይህን በሚያህል ቁጥር ወደ ቅድስና መድረስ ማለት፣ ሰዎች ልባቸውን፣ ሕይወታቸውን እና ጸሎታቸውን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በማቅረብ ለጥሪው ምላሽ መስጠታቸውን የሚያመለክት መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ሰመራሮ ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ መንፈሳዊነት መናገራቸውን ያስታወሱት ብጹዕነታቸው፣ መንፈሳዊነት በኅብረት የመጸለይ እና አብሮ የመሆን ልኬት መሆኑን ገልጸው፣ ቅድስና በቤተ ክርስቲያን መሬት ላይ የሚበቅል ፍሬ መሆኑን አስረድተዋል።

የቅድስና ስያሜ

በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት በኩል የተከናወኑ ረጅም እና በርካታ ሥራዎች መኖራቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ሰመራሮ፣ የቅድስና ስያሜ ከሁሉም በላይ ምስክርነቶችን በማዳመጥ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጸዋል። ሊብራራ የሚገባው ጽንሰ-ሐሳብ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሰመረሮ፣ የቅድስና ስያሜ ከስመ ጥርነት ወይም ከታዋቂነት ጋር መገናኘት የለበትም ብለው፣ ይልቁን በሰዎች ዙሪያ በሚደረጉ ጸሎቶች እና ልመናዎች አንፃር፣ የእግዚአብሔር ሰዎች ምላሽ እንደሆነ አስረድተው፣ ብዙውን ጊዜ በድንገት የሚከሰት እና ያልተጠበቀ ምላሽ የሚሰጠው ቢሆንም በጥልቀት መመልከት ማስተዋል ያስፈልጋል ብለዋል።

የበዓሉ ዝግጅት ተጠናቋል

በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባ ግንቦት 7/2014 ዓ. ም. የቅድስናን አዋጅ ይፋ ለማድረግ ሁሉ ነገር የተጠናቀቀ መሆኑን ያስታወቁት ብጹዕ ካርዲናል ሰመራሮ፣ ከሎጂስቲክስ አኳያ በቂ ዝግጅቶችን ማድረግ ለቅድስት መንበር በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፣ ከተለያዩ የዓለማችን አካባቢዎች የሚመጡ ምዕመናንን ተቀብሎ በበቂ ሁኔታ ማስተናገድ አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል። ብጹዕነታቸው ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር የነበራቸውን ቆይታ ሲፈጽሙ እንደተናገሩት፣ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የጤና ሁኔታ እጅግ መልካም እንደሆነ አረጋግጠዋል። በጉልበታቸው ለሚሰማቸው ሕመም በቅርቡ ፈውስን እንደሚያገኙ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

14 May 2022, 18:23