ፈልግ

Philippine family disability day group Philippine family disability day group 

ከዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ ፍቅርን መቀበል እንደሚያስፈልግ ጥሪ ቀረበ

በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከመጭው ሰኔ 15 – 19/2014 ዓ. ም. ለአሥረኛ ጊዜ ከሚካሄድ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ ፍቅርን መቀበል እንደሚያስፈልግ ጥሪ መቅረቡ ታውቋል። ለዚህ ታላቅ ጉባኤ የተዘጋጁ ሰባት የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮች እና በቪዲዮ ምስሎች የታገዙ ሌሎች ሰባት ምስክርነቶች ልዩ ልዩ ታሪኮችን፣ ያጋጠሙ ችግሮችን፣ ዳግም ስለ መታደስ እና ስለ እምነት የሚናገሩ መሆኑን፣ ለጉባኤው የጋራ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኙት የሮም ሀገረ ስብከት እና በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቤተሰብ ውስጥ የተለያዩ ሚናዎች ቢኖሩም አንድ ማንነት ብቻ እንዳለ፣ ሁላችንም የአንድ ቤተሰብ ልጆች መሆናችንን እና ማንም መርጦ የተወለደ እንደሌለ፣ እያንዳንዳችንም ህልውናን ለእናት እና ለአባት መስጠት እንዳለብን፣ ሕይወትን መቀበል እንጂ መስጠት እንደማንችል፤ ከተቀበልን በኋላ ማቆየት እንደምንችል፣ ዘንድሮ የሚካሄደው አሥረኛ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ በዝግጅት ወቅት ይፋ ባደረገው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቁጥር አራት ላይ አስታውቋል። ዘንድሮ ለአሥረኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የቤተ ሰብ ጉባኤ ምክንያት በማድረግ “ፍቅርን መቀበል”፣ በሚል ርዕሥ፣ በፊልም ዳይሬክተር በሆነው በአቶ አንቶኒዮ አንቶኔሊ የተዘጋጀ አጭር የቪዲዮ ቅንብር ለዕይታ የሚቀርብ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ አጭር የቪዲዮ ፊልም ዋና ገፀ ባህሪያት የሮም ከተማ ነዋሪ የሆኑት እናት ፣ አባት እና ሦስት ሴት ልጆቻቸው መሆናቸው ታውቋል። አራተኛ ልጃቸውን ለመውለድ በሚደርጉት ሙከራ ድንገተኛ የፅንስ መጨናገፍ ባጋጠማቸው ጊዜ ከባድ የአካል ጉዳት ያለባትን ሴት ልጅ በማደጎ ለማሳደግ መወሰናቸውን ፊልሙ ያስረዳል። ይህን በቤተ ሰብ ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን የተለመደ ታሪክ በተዋናይነት የምትገልጽ አሌሲያ፣ በችግር መካከል የሚታየው ርህራሄ አራቱን እህትማማቾች በፍቅር ለማገናኘት መቻሏ ተመልክቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ወንድማማችነትን መማር የሚቻለው ከልጅነት እውነታ ጀምሮ እንደሆነ፣ በቤተሰብ እና በኅብረተሰብ ውስጥ፣ በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት ፍቅር አብሮ መኖርን እንዴት መኖር እንዳለብን መናገራቸው ይታወሳል። “ምናልባት ይህን እውነታ ሁልጊዜ ለማወቅ ብንቸገርም ወንድማማችነትን በዓለም ውስጥ በትክክል የሚያስተዋውቀው ቤተሰቡ ነው!” ማለታቸው ይታወሳል። ከመጀመሪያው የወንድማማችነት ልምድ በመነሳት፣ በቤተሰብ ትምህርት በመታገዝ ፍቅርን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሳደግ የወንድማማችነትን ሕይወት በመላው ኅብረተሰብ እና ሕዝቦች መካከል ማንጸባረቅ የሚቻል መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መናገራቸው ይታወሳል።

11 April 2022, 16:15