ፈልግ

ጦርነት በዩክሬን ከተማ ቼርኖቢል ካደረሰው ውድመቶች መካከል ጦርነት በዩክሬን ከተማ ቼርኖቢል ካደረሰው ውድመቶች መካከል  

ቅድስት መንበር፣ በጋራ ደኅንነት ውስጥ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ቦታ እንደሌለው አስታወቀች

ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚው በዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲያቆም ጥሪ አቅርቦ፣ አገራቱ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መስፋፋትን እንዲያስወግዱ በማሳሰብ፣ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ በጋራ ደኅንነት ውስጥ ቦታ የሌለው መሆኑን ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኒውክሌር ጦርነት ስጋት ላይ በተካሄደው ጉባኤ ላይ የተሳተፉት አገራት፣ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ጥቃትን እንዲያስወግዱ እና የሌሎች ሀገራት የግዛት አንድነት እና የፖለቲካ ነፃነት እንዲከበር የሚጠይቅ የጋራ ሰነድን ፈርመዋል። ዓርብ መጋቢት 30/2014 ዓ. ም. ይፋ የሆነው ሰነዱ፣ ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚው የኒውክሌር ጦርነት ስጋትን በማስመልከት ያደረገው ዓለም አቀፍ ጉባኤ አካል መሆኑ ታውቋል። “የሰው ልጅ እያካሄደ ያለው የትጥቅ ትግል እና ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ከባድ ጦርነት ወደፊት የኒውክሌር ጦርነት ሊከሰት እንደሚችል ከአጥቂዎች በኩል የተሰጠ ምልክት ነው” በማለት ጉባኤው አስታውቋል።

በአገሮች መካከል የሚታይ አለመተማመን

መግለጫውን ፈርመው ያጸደቁት አገራት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ንግግር በመጥቀስ፣ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት "አስፈሪ፣ ኢ-ሰብአዊ፣ መስዋዕትነትን ያስከፈለ እና ትርጉም የለሽ ጦርነት ነው” በማለት ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል። የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ውድመትን ሊያስከትል የሚችልባቸውን የተለያዩ መንገዶች የገለጸው ጉባኤው፣ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎች ውድመት የኒውክሌር ቆሻሻ ፍሰትን ሊያስከትል እንደሚችል እና ይህም መላውን ፍጠረት ሊጎዳ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ አባላት አገራት በአገራቱ መካከል ያለው አለመተማመን እና ጥርጣሬ እየጨመረ በመምጣቱ በምሥራቁ እና በምዕራቡ ዓለም መካከል የበለጠ ውይይት እንዲደረግ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል። በአገሮች መካከል የሚታይ ከፍተኛ ኢ-ፍትሃዊነት፣ የፓርቲዎች የስልጣን ምኞት እና ጥማት ወደ ኒውክሌር ጦርነት ሊያመራ የሚችል የግጭት ውጤት መሆኑን አክለው አስታውቀዋል።

ሕይወትን ላማሻሻል የሚያግዝ ሳይንሳዊ ግዴታ

መግለጫው በዩክሬን የኬሚካል እና ባዮሎጂካል የጦር መሣሪያዎችን እና እንዲሁም በጦር ሜዳ ላይ ሰው ሰራሽ አእምሮን ያለ አግባብ መጠቀምን አስጠንቅቋል። የሳይንስ ጠበብት አክለውም፣ የሰውን ልጅ በጦርነት ወደ ጥፋት መንገድ ከመግፋት ይልቅ “ሙሉ እና ሰላማዊ ሕይወት” እንዲኖረው መርዳት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። መግለጫው በተጨማሪም የሳይንስ ጠበብት ሃላፊነት በምርምር ውጤቶቻቸው ላይ መዛባት እንዳይከሰት መናገር እና መርዳት እንደሆነ፣ እንዲሁም የሰው ልጅ የወደፊት ዕጣው የሚመካው የሥነ-ምግባር መርሆችን በመቀበል ላይ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ተናግሯል።

የጋራ ደህንነትን ያለ ኒውክሌር ጦር መሣሪያ ማስጠበቅ

የቅድስት መንበር መግለጫ በመቀጠልም፣ የዓለም መሪዎች የኒውክሌር ጦርነትን አስወግደው መደበኛ ኃይሎችን ለመጠቀም ያላቸውን ከባድ ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪውን አቅርቧል። የሳይንስ ጠበብት ይፋ ባደረጓቸው ዘጠኝ ነጥቦች፣ ሁሉም አገራት በሌሎች አገራት የግዛት አንድነት እና የፖለቲካ ነፃነት ላይ ማስፈራሪያን ከማድረግ እንዲቆጠቡ፣ ግጭቶችን ለማስወገድ ኃይል እንዳይጠቀሙ፣ ጦርነትን ፈርተው ለሚሸሹ ስደተኞች መጠለያን መስጠት፣ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ምርትን እንዳያስፋፉ፣ የኒውክሌር ጦር መሣሪያን ላለመጠቀም እንዲወስኑ እና የጦር መሣሪያ እሽቅድምድም እንዲቀንሱ፣ የኒውክሌር ሃይልን ለጦር መሣሪያ ግንባታ እንዳይውል ማድረግ፣ የኒውክሌር ጦርነት እድልን ለመቀነስ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ እና አሁን ያለውን የጦር መሣሪያ ገደብ ስምምነቶችን ማክበር የሚሉት ይገኙባቸዋል። 

ሰላምን መሻት የሁሉም ግዴታ ነው

በመጨረሻም ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚው አባላት፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በዩክሬን ያለው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ተማጽነው፣ የሳይንስ ሊቃውንት የፈጠራ ችሎታቸውን ወደ ተሻለ የሰው ልጅ ሕይወት በመምራት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ መግለጫው አክሎም፣ የሃይማኖት መሪዎች አሳሳቢ የሆኑ ሰብዓዊ ጉዳዮችን በጽናት ማወጃ እንዳለባቸው እና ሁሉም ሰው “በሰው ልጅ እጣ ፈንታ” ላይ ያለውን እምነት በድጋሚ በማረጋገጥ፣ ጦርነትን የማስወገድ የጋራ ግዴታ እና ሃላፊነት እንዳለበት በመግለጽ ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚው መግለጫውን አጠናቅቋል። 

11 April 2022, 16:21