ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ፋሬል፣ ሮም በሚገኝ የቅዱስ መስቀል ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ንግግር ሲያደርጉ ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ፋሬል፣ ሮም በሚገኝ የቅዱስ መስቀል ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ንግግር ሲያደርጉ 

ካርዲናል ኬቪን፣ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች የወንጌል አገልግሎት ዋና ተዋናይ መሆናቸውን ገለጹ

በቅድስት መንበር የምዕመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተወካይ፣ ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ፋሬል፣ ከምዕመናን ማኅበራት መሪዎች እና ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አዳዲስ እንቅስቃሴ ተወካዮች ጋር ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 20/2014 ዓ. ም ሮም በሚገኝ የኢየሱሳውያን ማኅበር ጠቅላይ ቤት ተገናኝተው ተወያይተዋል። ብጹዕናታቸው ከአባላቱ ጋር በነበራቸው ውይይት፣ ልዩ ልዩ የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ለወንጌል አገልግሎት ዋና ተዋናይ መሆናቸውን ገልጸው፣ "የክርስትና ጥሪ ምን እንደሆነ የሚረዱ ምዕመናንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ እንፈልጋለን" ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዛሬ የተካሄደው ውይይት ዋና ርዕሥ “በቤተክርስቲያን ማኅበራት ውስጥ የሥራ ሁኔታ፣ በፍትህ እና በበጎ አድራጎት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት” የሚሉ መሆናቸው ታውቋል። ለውይይት ከቀረቡት ርዕሠ ጉዳዮች መካከል በዋናነት፣ የጥምቀትን ምስጢር የተቀበሉት ምዕመናን  በሚኖሩበት አካባቢ በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ እና በክርስቲያን ማኅበረሰብ ውስጥ ወንጌል በመመስከር ሥራቸው እና አገልግሎታቸው እንዲቀደስ የሚያደርጉበትን፣ የወንጌል አገልግሎት የሚጠይቀውን የፍትህ መስፈርት በማሟላት የሚያበረክቱትን አገልግሎት ከሥራ ክብር እና  ግዴታ ጋር ማጣመር፣ የሠራተኛውን መብት እና ክብር እንዲሁም የቀጣሪ ማኅበራት ግዴታን ማክበር፣ የማኅበራት መሪዎች ከምዕመናን ተወካዮች እና ከአዳዲስ መንፈሳዊ ማኅበራት ተወካዮች ጋር፣ በምዕመናን እና ቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተቋቁመው ዕውቅናን ካገኙት ግለሰቦች ወይም ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የቤተክርስቲያን ማኅበራት ተወካዮች ጋር ተስማምተው ዓመታዊ ስብሰባን በማዘጋጀት የመደማመጥ፣ ሃሳብን የመለዋወጥ እና የስልጠና ዕድሎችን ማመቻቸት የሚሉ ይገኝባቸዋል።

አዳዲስ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎችን ማጤን

ሮም በሚገኝ የቅዱስ መስቀል ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትናንት ረቡዕ ሚያዝያ 19/2014 ዓ. ም. አዳዲስ የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ፣ እንቅስቃሴዎች እና የምዕመናን ማኅበራትን አስመልክቶ "የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎችን የምንሰበስብበት ጊዜ" በሚል ርዕሥ የአንድ ቀን ጥናታዊ ስብሰባ መካሄዱ ታውቋል። ሦስት ሥነ-መለኮታዊ ይዘት ባላቸው፣ እነርሱም የሐዋርያዊ አገልግሎት ጸጋ፣ ምስጢረ ጥምቀት፣ የወንጌል ተልዕኮ ጥናት መካሄዱ ታውቋል። ትናንት ጠዋት በዩኒቨርሲቲው ማዕከል ተገኝተው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምዕመናን እንቅስቃሴ አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ውይይት ያስጀመሩት፣ በቅድስት መንበር የምዕመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ፋሬል መሆናቸው ታውቋል።

ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ፋሬል ለውይይቱ ተካፋዮች ሰላምታቸውን ካቀረቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ ለምዕመናን ማኅበራት እና አዳዲስ እንቅስቃሴዎች የሚሰጡ ኮርሶችን ጨምሮ ልዩ ልዩ ዕቅዶችን፣ ሴሚናሮችን እና ጉባኤዎችን ማዘጋጀት ለጀመሩት ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የላዋ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ሥልጣስ ከተቀበሉ ጊዜ ወዲህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚገኙ የምዕመናን እንቅስቃሴዎች አስፈላጊነት ያለማቋረጥ መናገራቸውን አስታውሰው፣ ይህም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አዲስ የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት በማስፈለጉን እንደሆነ ገልጸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በመልዕክታቸው ደጋግመው ለወንጌል አገልግሎት ወደ ሕዝብ ዘንድ መሄድ እንዳለብን እና አዲስ የወንጌል ስርጭት አገልግሎትን ማካሄድ እንደሚገባ መናገራቸውን አስታውሰዋል።

የሐዋርያዊ አገልግሎት ጸጋ፣ ምስጢረ ጥምቀት እና የወንጌል ተልዕኮ፣ ሦስት ሥነ-መለኮታዊ ይዘት ያላቸው ርዕሠ ጉዳዮች መሆናቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ፋሬል፣ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በርካታ የምዕመናን እንቅስቃሴዎች የተወለዱበት ወቅት እንደነበር አስታውሰው፣ አስፈላጊነቱን የጉባኤው አባቶችም የተገነዘቡት መሆናችውን በመግልጽ፣ ዛሬ ከምንጊዜውም በላይ የክርስትና ጥሪ ምን እንደሆነ የተረዱ ምዕመናን ያስፈልጉናል ብለው፣ የክርስትና ሕይወት የወንጌል ምስክርነትን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል። በጦርነቶች እና በወረርሽኞች በሚያሰቃይ ዓለማችን፣ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን የሚያበረክቱ በቂ ካኅናት እና ደናግል በማይገኙባቸው አካባቢዎች የምዕመናን መንፈሳዊ ማኅበራት እና እንቅስቃሴዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የክርስትናን ሕይወት መመስከር ይችላሉ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የፍቅር ደስታ” በማለት ይፋ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳንን ምዕመናን እንዲያነቡት የጋበዙት ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ፋሬል፣ በተለይም በሦስተኛው እና በአራተኛው ምዕራፍ ላይ የተገልጸው ምክረ ሃሳብ፣ በሁለት የተለያዩ ጾታዎች መካከል ስላለ ፍቅር ከመናገር በተጨማሪ በባል እና በሚስት መካከል ስላለው ወንድምነት እና እህትነት እንዲሁም በመላው ዓለም የወንድማማችነት እና እህትማማችነት አስፈላጊነት የሚናገር መሆኑን አስታውሰዋል። “እያንዳንዳችን በሌላ ሰው ሕይወት ተጠያቂዎች መሆን አለብን” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን፣  በተመሳሳይ መልኩ ባል እና ሚስት የመላዋ ቤተክርስቲያን አካል እንደሆኑ ሊሰማቸው እንደሚገባ እና ችግር ውስጥ የሚገኙትን መርዳት እንዳለባቸው፣ ይህም የዓለማችን እና የኅብረተሰባችን የወደ ፊት እጣ ፈንታ እንደሆነ አስገንዝበው፣ በተለይ ከቤተሰብ ጋር የሚሠሩ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ይህን ተግባር መፈጸም ይገባል በማለት በቅድስት መንበር የምዕመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ፋሬል አሳስበዋል።

28 April 2022, 16:21