ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፣  

ካርዲናል ቼርኒ፣ በዓለማችን የሚፈጸሙ ግፎች፣ ሰዎች እኩል መብት እንደሌላቸው ይገልጻል አሉ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፣ በመካሄድ ላይ ለሚገኝ አንድ የምሁራን ጉባኤ ባቀረቡት መልዕክት፣ በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች በሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግፎች ለሁሉም ሰው እኩል መብት አለመኖሩን ይገልጻል ብለዋል። በሌላ ወግን ካቶሊካዊነት ለዘላቂ ዓለም አቀፍ ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋፅዖ ገልጸው፣ በመንግሥታት መካከል ያለውን አንድነት እና የወንድማማችነት እሴት አዲሱን ትውልድ ማስተማር ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በካናዳ የሚገኝ የኖርማን ፓተርሰን የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ጥናት ማዕከል፣ ካርሌቶን ዩኒቨሲቲን፣ ቅዱስ ሚካኤል ኮሌጅን እና ቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ በማስተባበር ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ የተጋበዙት ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፣ "የካቶሊክ እምነት ለዘላቂ ዓለም አቀፍ ልማት የሚያበረክተው አስተዋፅዖ" በሚል ርዕሥ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን አቅርበዋል። “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚል ርዕሥ ይፋ የሆነውን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መሠረት በማድረግ ለስብሳባው ተካፋዮች ባቀረቡት ጽሑፋቸው፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራን እና በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች እየተካሄዱ የሚገኙ ደም አፋሳሽ ጦርነቶች በመገንዘብ፣ ዛሬ በጋራ መኖሪያ ምድራችን ውስጥ ወንድማማችነትን ማጎልበት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ገልጸው፣ ከዚህም በተጨማሪ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅርቡ እንደገለጹት፣ ከዚህ በፊት በካናዳ ውስጥ የተለያዩ ቤተሰቦች የገዛ መሬታቸው እና ባሕላቸው እንዲተው የተደረጉበትን አደጋ ለማሸነፍ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያደረገችውን ​​ጥንቃቄ የተሞላበት ሂደት አስታውሰው፣ በዚህ የተሳሳተ ተግባር የትምህርት ቤት ኃላፊነት የነበራቸው ካቶሊካዊ ማኅበረሰብም መሳተፉን ገልጸዋል።

በሕጋዊ አንድነት ላይ የተመሠረተ ወንድማማችነት

ካቶሊካዊነት ለሰው ልጅ ቅድሚያን እንደሚሰጥ፣ ለማኅበራዊ አንድነት ሊያበረክት የሚችለውን አስተውጽኦንም እንደሚገነዘብ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፣ በዚህም ምክንያት የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገትን የሚያደናቅፉ መሰናክሎችን ለይቶ ለማስወግድ እንደሚጥር ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ እ. አ. አ በ1948 ዓ. ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የታወጀው የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ለሰብዓዊ ክብር ከሰጠው ከፍተኛ ግምት መካከል አንዱ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል አስታውሰዋል። ያም ሆኖ በሰብአዊ ክብር ላይ የሚፈጸሙ ግፎችን እስከ ዛሬ ድረስ እያየን እንገኛለን ያሉት ብጹዕነታቸው፣ እንደ ዘር ማጥፋት ወንጀል፣ ማሰቃየት፣ የሞት ፍርድ፣ አክራሪነት፣ ዘረኝነት እና በሴቶች ላይ የሚደረግ መድልኦ “ሰዎች በሙሉ እኩል መብት አላቸው” ብሎ ለመናገር የማይፈቅድ መሆኑን አስረድተዋል። ነገር ግን “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ከሚለው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን የምንማረው፣ ወንድማማችነት የሚመነጨው በሕዝብ አብሮ የመኖር መብት እና ግዴታ እንዲሁም ለማይገረሰስ ሰብዓዊ ማንነት የጋራ እውቅና ከመስጠት መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል አስረድተዋል። አክለውም ወንድማማቾችነት ያለ ምንም ልዩነት በወንዶች እና በሴቶች፣ በወጣቶች እና በአዛውንት መሠረታዊ እኩልነት እውቅና ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስረድተው፣ ሌላውን እንደ ጎረቤት እና እንደ ሰው በመመልከት እኩል እውቅና መስጠት መማር እና ሌሎችን ማስተማር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ወንድማማችነትን ማዳበር፣ የመጋራትን እና የአንድነት እሴቶችን ለሌሎች ማስተላለፍ የ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መሠረታዊ ሃሳብ መሆኑን በድጋሚ ያታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ቼርኒ፣ ቀጥለውም ግለሰባዊነት አንድን ሰው የበለጠ ነፃ፣ እኩል፣ ወንድም እና እህት እንደማያደርግ፣ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሁለንተናዊ ልማት የማግኘት መሠረታዊ እና የማይገሰስ መብት እንዳለው ካልተገነዘበ፣ ለወንድማማችነትም ሆነ ለወደፊት የሰው ልጅ ህልውና የማይጠቅም መሆኑን አብራርተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳንቸው ውስጥ ሁለት የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መሪ ሃሳቦችን ማዳበራቸውን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፣ እነርሱም የአንድነት መርህ እና የማኅበራዊ ቅርስ ሚና የሚሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤት፣ ቁምስና፣ የባሕል እና የመዝናኛ ማዕከላት ወንድማማችነትን የሚያሳድጉ፣ የነፃነት፣ እርስ በእርስ የመከባበር፣ የመጋራት እና የአንድነት እሴቶችን ለሌሎች ማስተላለፍ መቻል አለባቸው ብለዋል። አዲሱ ትውልድም ከእነዚህ እሴቶች ተምሮ የማግለል ባሕልን በመቃወም በሁለንተናዊ አንድነት ላይ መመሥረት አለበት ብለዋል።

የፍቅር መስፈርት

ከግለኝነት ሃሳብ በላይ የሆነው የፍቅር መስፈርት፣ በግል ንብረት ባለቤትነት መብት እና ሌሎች ተዛማጅ መብቶች ላይ ተግባራዊ ከሆነ፣ በእያንዳንዱ የመንግሥት አሠራር እና በመካከላቸው ባለው ዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረው ብጹዕ ካዲናል ሚካኤል ገልጸው፣ እያንዳንዱ አገር ከራሱ ወሰን አልፎ ለሌሎች አገራት ሕዝቦች ሁሉን አቀፍ ልማትን የማስተዋወቅ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል። በኤኮኖሚ ያደጉ አገሮች በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ላይ ጫናን ከማሳደር ይልቅ እርዳታን እንዲለግሱ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጠየቃቸውን አስታውሰው፣ ሁሉም ሰው በኅብረት ተከባብሮ እንዲኖር የሚያስችል እገዛን እንዲያገኝ በማለት ጥሪ አቅርበዋል። በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፣ ዛሬ ላይ የሚታዩ ዓለም አቀፍ ችግሮችን በፍቅር መስፈርት መለየት ማለት በአካሄዶች ላይ ጫናን መፍጠር ማለት ሳይሆን ማኅበራትን ማበረታታት እና መደገፍ ማለት እንደሆነ አስረድተው፣ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በመለወጥ እና ግለሰባዊነትን በማሸነፍ ራስን እንደ ወንድማማችነት መመልከት ያስፈልጋል ብለዋል።

27 April 2022, 14:51