ፈልግ

ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ በኦርቪዬቶ ካቴድራል የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን መርተዋል ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ በኦርቪዬቶ ካቴድራል የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን መርተዋል  

ካርዲናል ሳንድሪ፣ ሰላምን እና ዕርቅን መፍጠር የዕለት ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አሳሰቡ

በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ፣ መጋቢት 28/2014 ዓ. ም. በመካከለኛው ጣሊያን፣ ኡምብሪያ ክፍለ ሀገር ወደምትገኝ ኦርቪዬቶ ከተማ በመሄድ፣ በአገሪቱ ፋይናንስ ፖሊስ ለሚመራ የፀረ-ሽብር ማሰልጠኛ ማዕከል ተማሪዎች የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን መርተዋል። ብጹዕነታቸው በከተማው በሚገኝ ካቴድራል ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ባቀረቡት ስብከት፣ በጦርነት ወቅት ሰዎች እርስ በእርስ ለመተጋገዝ መነሳሳታቸው፣ እያንዳንዱን ሰው እንዴት ማክበር እንደሚገባ የሚገልጸውን፣ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለው የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ጥበብ ይገልጻል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ወደ ከተማዋ ሲደርሱ ከ140 ሰልጣኞች እና ከማሰልጠኛ ማዕከሉ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው በአንዳንድ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር፣ በኢራቅ እና በሶርያ ያለውን ሁኔታ በማስታወስ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በዩክሬን ውስጥ የሚካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነትንም በማንሳት ተወያይተዋል። ብጹዕነታቸው በመቀጠልም በጣሊያን ሪፐብሊክ እና በቅድስት መንበር መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ተወያይተዋል።

የማሰልጠኛ ማዕከሉ ማኅበረሰብ ከብፁዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ጋር የነበራቸውን ውይይት ከፈጸሙ በኋላ ወደ ካቴድራሉ ሲደርሱ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጓልቲዬሮ ሲጂስሞንዲ ለብፁዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን ቀጥለውም ሀገረ ስብከታቸውን በማስመልከት አጭሩ ገልጻ አድርገውላቸዋል። በመቀጠልም ብፁዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ፣ በጣሊያን ፋይናንስ ፖሊስ በሚመራ የፀረ-ሽብር ማሰልጠኛ ማዕከል ተማሪዎች እና የማሰልጠኛ ማዕከሉ ኃላፊዎች የተካፈሉበትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የመሩ ሲሆን፣ በቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ስብከታቸውን አቅርበዋል።  

ብፁዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ለሰልጣኞቹ ባሰሙት ስብከት፣ ሰልጣኞቹ እየተከታተሉት ባለው ስልጠና ራሳቸውን ለሀገር እና ለኅብረተሰብ አገልግሎት ያበረከቱ መሆናቸውን አስረድተው በማከልም፣ ወደ መሰዊያው ከሚያቅርቡት ዳቦ እና ወይን ጠጅ ጋር ሕይወታቸውን፣ ትውልድ አገራቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ለማገልገል የሚያቀርቡ መሆናቸውን አስረድተዋል። በዕለቱ የተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል፣ የእስራኤልን ሕዝብ በምድረ በዳ ያጋጠመን ታሪክ እንደሚያስታውስ ገልጸው፣ የእስራኤል ሕዝብም በአንድ ወቅት በሙሴ ላይ ማጉረምረም መጀመሩን እና ቀጥሎም እግዚአብሔርን መንቀፍ መጀመሩን አስታውሰው፣ ይህም የሰው ልጅ በዘመናት ውስጥ የሚያሳየው ቀጣይነት ያለው ልምድ መሆኑን ተናግረዋል። ብጹዕነታቸው ስብከታቸውን በመቀጥል፣ ዛሬ በዘመናችንም ከኃያላን መንግሥታት መካከል፣ ባለፈው የኢምፔሪያሊስት አገዛዝ አስተሳሰብ የታወሩ እና  በራእያቸው የተመረዙት በሙሉ ሞትን እና ውድመትን በማስፋፋት የሕይወትን ክብር የሚረግጡ እንዳሉ አስረድተዋል።

ቅዱስ ፍራንችስኮስ የተናገሯቸው እና ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው የጠቀሷቸው በጥበብ የተሞሉ በርካታ ትንቢታዊ ቃላት መኖራቸውን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ፣ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኑ፣ አዲስ ዓለምን ያለ አንዳች አመጽ መገንባት፣ የእያንዳንዱን ሰው እና የወንድማማችነት ክብርን ሁል ጊዜ በማጉላት እና በመጠበቅ፣ በዚህም በመታገዝ አዲስ ስልጣኔን ለማሳደግ ሰላም፣ ዕርቅ፣ እርስ በእርስ መከባበር፣ እና የጋራ ውይይት በየዕለቱ ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ፣ የሞት ፍርድ ከሚወስኑት ተቃዋሚዎቹ ጋር ባደረጋቸው ንግግሮቹ፣ ከመሠረታዊው ፈተና ጋር ፊት ለፊት እንድንገናኝ ያደርገናል ብለው፣ ከአብ ጋር ባለው ጥልቅ ግንኙነት እና በመስቀል ላይ ስቃዩ፥ "አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" ሲል ራሱን ለአባቱ በአደራ መስጠቱን አስታውሰዋል።

07 April 2022, 16:57