ፈልግ

ዱባይ ከተማ በተዘጋጀው ትዕይንት ላይ የተገኙት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፣ ዱባይ ከተማ በተዘጋጀው ትዕይንት ላይ የተገኙት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፣  

ካርዲናል ፓሮሊን ለዓለም ሰላም ግንባታ የእርስ በእርስ ትውውቅ ሊኖር እንደሚገባ አስታወቁ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፣ እ. አ. አ በ 2022 በዱባይ የተከበረውን ብሔራዊ የትዕይንት ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በዓለማችን ውስጥ ሰላምን ለማንገሥ መልካም የእርስ በእርስ ትውውቅ ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል። ብጹዕነታቸው አክለውም የእርስ በእርስ ግንኙነትም ለሰላማዊ የጋራ ሕይወት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እ. አ. አ በ 2020 በአረብ ኤምረቶች፣ ዱባይ ከተማ መከበር ሲገባው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ዘንድሮ የተዘጋጀው የቅድስት መንበር የ2020 ብሔራዊ ትዕይንት እስከ መጋቢት 22/2014 ዓ. ም. የሚቆይ መሆኑ ታውቋል። ዱባይ ከተማ በተዘጋጀው ትዕይንት ላይ የተገኙት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፣ ዓለም አቀፍ ሰላምን ለማምጣት የጋራ ውይይት፣ እሴቶችን መጋራት እና እርስ በእርስ መቀራረብ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ምሥረታ 50ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና እንዲሁም በግላቸው ለአገሩ ሕዝብ መልካም ምኞታቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፣ መላው የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ሕዝብ እና ሠራተኛው ማኅበረሰብ በብልጽግና እና በሰላም እንደሚባረኩ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። በተጨማሪም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ. አ. አ የካቲት ወር 2019 ዓ. ም. ወደ ተባበሩት አረብ ኤምረቶች ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የተደረገላቸውን ታሪካዊ አቀባበል እና መስተንግዶ አስታውሰዋል።

በቅድስት መንበር እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መካከል ያለው ግንኙነት

በቅድስት መንበር እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል በርካታ ግንኙነቶች መመሥረታቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፣ የባሕል እና የሃይማት ልዩነቶች ቢኖሩም፣ ሁለቱ ወገኖች በመካከላቸው የሚጋሯቸው መሠረታዊ የጋራ እሴቶች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰላም ከፍተኛ አስተዋፅዖ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ገልጸዋል። ቀጥለውም በቅድስት መንበር እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ከ15 ዓመታት በፊት የተመሠረተውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና በቅርቡም በአቡ ዳቢ ከተማ ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት መከፈቱ፣ ሁለቱ ወገኖች በጋራ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸውን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በዱባይ “ኤክስፖ” ላይ የቅድስት መንበር ተሳትፎ አስፈላጊነት

ቅድስት መንበር በዱባዩ “ኤክስፖ” የመሳተፏን አስፈላጊነት የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ቅድስት መንበር በዱባይ ኤክስፖ መሳተፍ ምንም ዓይነት የንግድ ዓላማ የሌለው፣ በዋናነትም በአገራት ባሕሎች እና ሃይማኖቶች መካከል በሰላም አብሮ የመኖርን ሃሳብን ለማራመድ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል። ቅድስት መንበር በቁርጠኝነት ይህን ሃሳብ በሁሉም ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ፣ ትምህርታዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ሃይማኖታዊ ደረጃዎች በማስተዋወቅ፣ በሰብዓዊ ቤተሰብ መካከል እውን እንዲሆኑ ለማድረግ መሆኑንም አስረድተው፣ ይህን ለማሳካት፣ በተለይ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እየተስተዋሉ ካሉት ዘርፈ ብዙ ግጭቶች አንፃር፣ ሰላም እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ በመግለጽ፣ በዩክሬን የተከሰተው ጦርነት በርካታ ሰዎችን ለሞት፣ ለንብረት መውድም እና ለከፍተኛ ስቃይ እየዳረገ ያለ አሳዛኝ ሁኔታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሰላም አብሮ ለመኖር የሃይማኖትና የተቋማት ሚና

እያንዳንዱ በሰላም አብሮ የመኖር ጥረት ከሁሉ አስቀድሞ ለጋራ ሕይወት ባለው ቁርጠኝነት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት እና ለዚህም የጋራ ውይይት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህም በላይ ሃይማኖቶች እና ተቋሞቻቸው ግንዛቤን በማስጨበጥ እና ሕሊናን በማሳደግ ተልዕኮአቸውን ሊወጡ እንደሚችሉ እና እንደሚገባቸው ገልጸው፣ ቅድስት መንበር በዱባይ “ኤክስፖ” ላይ በመሳተፍ ያቀረበች ትዕይንት የጋራ ውይይትን፣ የእርስ በእርስ ግንኙነትን እና ወዳጅነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የሚያሳስብ መሆኑን ገልጸዋል። የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ እና የግብፁ ሱልጣን አል-ማሊክ አል ካሚል በመካከላቸው ያሉ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው፣ እ. አ. አ በ1219 ዓ. ም. ያደረጉት ወንድማዊ ግንኙነት በባሕሎቻችን እና በሃይማኖታች መካከል አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን፣ እንደዚሁም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ. አ. አ. የካቲት 4/2019 ዓ. ም. በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ አቡ ዳቢ ከተማ ከግብጹ የአል-አዝሃር ታላቁ ኢማም አህመድ ኤል-ታይብ ጋር ለዓለም ሰላም እና አብሮ ለመኖር የሚያግዝ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” የሚል ሰነድ በጋራ መፈረማቸውን ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን አስታውሰዋል። ሰነዱ ማንኛውንም ዓይነት ጥላቻን በፅኑ በማውገዝ፣ የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት አክራሪነትን በማስወግድ፣ ሕዝቦች በመቻቻል፣ በመከባበር እና በእውነተኛ የወንድማማችነት ስሜት መልካም ግንኙነቶችን መመስረት እንደሚያስፈልግ የሚጠይቅ ትንቢታዊ ሰነድ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ገልጸዋል። 

የሰብዓዊ ወንድማማችነት እና የትምህርት አስፈላጊነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የግብጹ አል-አዝሃር ታላቁ መስጊድ ኢማም፣ አህመድ ኤል-ታይብ እ. አ. አ. የካቲት 4/2019 ዓ. ም.  የፈረሙት “የሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ካስገኛቸው ፍሬዎች መካከል፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት አንድነት የጋራ ውይይት ፕሬዚደንት በሆኑት በብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ የሚመራ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ከፍተኛ ኮሚቴ ምሥረታ፣ ለሁለቱም ወገኖች የጋራ የሆነው "አብርሐማዊ ቤተሰብ" ግንባታ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጸድቆ መመሥረቱ በግንባር ቀደም የሚጠቀሱ መሆናቸውን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል።  ትምህርት ለእውነተኛ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ግንኙነቶች የሚያበረክተው ድጋፍ ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የትምህርት ሚኒስቴር እና በጳጳሳዊ ምክር ቤት የካቶሊክ ትምህርት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር በጋራ ያቀዷቸው ተከታታይ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን፣ እንደዚሁም ለአካባቢ ጥበቃ ቁርጠኝነትን በማሳየት እና የአብሮነት መርሆችን በጋራ ለመከተል ማቀዳቸውን አስታውሰዋል። ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁ፣ እ. አ. አ መጋቢት 19/2022 ዓ. ም. ቅድስት መንበር የተካፈለችበት የዱባይ ብሔራዊ “ኤክስፖ”፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ. አ. አ መጋቢት 19/2013 ዓ. ም. ለከፍተኛ የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪነት የተመረጡበን ዕለት የሚያስታውስ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም ቅዱስነታቸው ለጋራ ውይይት ታላቅ ፍላጎት ያንዳላቸው፣ በሰላም፣ በእኩልነት እና በሰብዓዊ መብቶች መከበር ላይ የተመሠረተ ማኅበረሰብን ለመገንባት፣ ሕዝቦችን እርስ በእርስ የሚያገናኙ ድልድዮችን ለመገንባት እና ወንድማማቾች እና እህትማማቾች የሚያደርጉ እሴቶችን በድጋሚ እንድናውቅ የሚያሳስብ መሆኑን አስረድተዋል። 

21 March 2022, 16:01