ፈልግ

በዩክሬን ማሪዩዎል ከተማ የደረሰ የጦርነት ቀውስ በዩክሬን ማሪዩዎል ከተማ የደረሰ የጦርነት ቀውስ  (ALEXANDER ERMOCHENKO)

ካርዲናል ፓሮሊን፣ ቅን ፍላጎት ካለ በዚህች ምድር ሰላምን ማንገሥ እንደሚቻል ገለጹ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን መጋቢት 13/2014 ዓ. ም. ከሮም በስተሰሜን ምዕራብ በኩል በምትገኝ ፓሶስኩሮ ከተማ የታነጸውን የሕጻኑ ኢየሱስ አዲስ የሕክምና ማዕከልን ጎብኝተዋል። ብጹዕነታቸው ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት ላይ ባሰሙት ንግግር፣ በሕዝቦች መካከል እውነተኛ ፍላጎት ካለ ሰላምን በምርድራችን ላይ ማምጣት የሚቻል መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህም ጋር፣ በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም አስቸኳይ ድርድር እንዲጀመር አሳስበው፣ ቅድስት መንበርም ሽምግልናን በማካሄድ የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፈቃደኛ መሆኗን በድጋሚ አረጋግጠዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዩክሬን ውስጥ በርካታ ሕጻናት ለድርብ ስቃይ መጋለጣቸው ሲታወቅ፣ በተለያዩ በሽታዎች ሲሰቃዩ የቆዩ የዩክሬን ሕጻናት፣ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ወደ መካከለኛው ጣሊያን፣ ፓሶስኩሮ ከተማ በመምጣት የሕክምና አገልግሎት ማግኘት መጀመራቸው ታውቋል። ማዕከሉን ለሕክምና አገልግሎት መርቀው የከፈቱት ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፣ በዩክሬን እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ከጋዜጠኞች በኩል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ሕጻናቱ በሕመም እና በስደት ምክንያት ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸው እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል። በዩክሬን በሕጻናት ላይ የሚደርሱ ስቃዮችን በፎቶግራፍ ምስል ከተመለከቷቸው በኋላ በስጡት አስተያየት፣ በንጹሐን ሰዎች ላይ የሚደርስ ስቃይ ተቀባይነት እንደሌለው፣ ከጦርነቱ ምንም ትርፍ እንደማይገኝ እና ዋጋውንም እየከፈሉ የሚገኙት አቅመ ደካሞች ተጋላጭ ማኅበረሰብ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ወደ ጥፋት የሚሄደው ጥፋት

ብጹዕ ካርዲናል ፔየትሮ ፓሮሊን በዩክሬን ውስጥ ላለፉት 27 ቀናት የተካሄደው ጦርነት የምስራቅ አውሮፓ አገር ዩክሬንን ወደ እሳት የቀየራት መሆኑን ገልጸው “ጦርነት ወደ ጥፋት የሚወስድ ሌላ ጥፋት ነው” በማለት ገልጸውታል። መጪው ጊዜ ምን እንደሚሆን ባናውቅም ለተፈጠረው እና እየተፈጠረ ላለው አደጋ መፍትሄን ማግኘት እንደተሳነን፣ ሆኖም ግን ውጥንቅጡ እንደሚወገድ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፣ ከሁሉም በፊት ጦርነቱ ቶሎ እንዲገታ እና መፍትሄን ሊያስገኝ የሚችል ድርድር እንዲጀመር ጠይቀዋል።

የሰላም “በጎ ፈቃድ”

በዩክሬን እየተካሄደ ያለው አስከፊ ጦርነት ቶሎ እንዲያቆም በማለት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ደጋግመው መናገራቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ቅድስት መንበር ጦርነቱን ለማስቆም ሁሉንም ነገር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠው፣ ለውጥን ለማምጣት እና ተግባራዊ ለማድረግ እውነተኛ ዓላማ ሊኖር እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ብጹዕነታቸው፣ በሁሉም ዘንድ የሚፈለግ ሰላምን ለማምጣት የሚያስችል መፍትሄ ለማግኘት ሁል ጊዜ ዕድል እንዳለ፣ የሚያስፈልገው በጎ ፈቃድ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።

የሩሲያ እና የዩክሬን መልካም ፈቃድ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ አማራጩ ጦርነት፣ ሁከት እና ሞት መሆን እንደሌለበት ተናግረው፣ ቅድስት መንበርም ጦርነቱን የሚያስቆም ድርድር መካሄድ እንዳለበት አጥብቃ የምታምን መሆኗን ተናግረዋል። ሁለቱ የጦርነቱ ተዋናይ ወገኖች የቅድስት መንበር ትብብር እንደሚጠቅማቸው ካመኑበት ቅድስት መንበር የሽምግልና ድጋፏን ለመስጠት ሁል ጊዜ ዝግጁ መሆኗን ብጹዕ ካርዲናል ፔየትሮ ፓሮሊን ገልጸዋል።

23 March 2022, 17:13