ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በሲምፖዝዬሙ መዝጊያ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በሲምፖዝዬሙ መዝጊያ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት   (Vatican Media)

ካርዲናል ፓሮሊን፣ ካኅናት ዘወትር በምዕመናን መካከል ሊገኙ ይገባል አሉ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የካቲት 12/2014 ዓ. ም. በቫቲካን የተዘጋጀውን ሲምፖዝዬም ከተሳተፉት አባላት ጋር በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አቅርበዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ “የክኅነት መሠረታዊ ሥነ-መለኮት” በሚል ርዕሥ ከየካቲት 10/2014 ዓ. ም. ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው ሲምፖዚዬም ማጠቃለያ ዕለት ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ ካኅናት ዘወትር በምዕመናን መካከል መገኘት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት እውን በሆነው የምዕመናን የጋራ ክህነት ጥሪ” ካኅናት ከምዕመናን መካከል ሊሆኑ እንደሚገባ፣ ለሚገለገልበት ቋንቋም ትኩረትን በመስጠት “የአገልግሎት አድማሳቸውን እስከ ዓለም ዳርቻ” ማስፋት እንደሚገባ አሳስበዋል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ “የክኅነት መሠረታዊ ሥነ-መለኮት” የሚለውን የሲምፖዚዬሙ ርዕሥ ግልጽ የሚያደርጉ ማብራሪያዎችንም አቅርበዋል። በብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሊቀ መንበር በሆኑት በብፁዕ ካርዲናል ማርክ ኤሌት እና የክህነት ጥሪ ጥናት እና ምርምር ማዕከል በጋራ ያዘጋጁትን የሦስት ቀናት ሲምፖዚዬም የከፈቱት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መሆናቸው ታውቋል።

ሲምፖዚዬሙን የሚሳተፉት ካኅናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም የምእመናን ወገን፣ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል ላይ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የመሩትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከተካፈሉ በኋላ በጳውሎስ ስድስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ በመገኘት በሁለት ክፍሎች በቀረቡ ሦስት ጭብጦች ላይ እነርሱም፥ “ከጋብቻ እና ጾታዊ ግንኙነት መራቅ፣ ለምዕመናን ጥቅም የሚሰጥ መለኮታዊ ስጦታ እና መንፈሳዊነት” በሚሉ ጭብጦች ላይ በማትኮር ውይይት ማካሄዳቸው ታውቋል። በሲምፖዜዬሙ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግል፣ ክቡር አባ ጃንፍራንኮ ጊርላንዳ፣ ሞንሲኞር ፓውሎ ማርቲኔሊ እና እውቋ ጣሊያናዊ ደራሲ ወ/ሮ ኪያራ አሚራንቴ መሆናቸው ታውቋል።

የካኅን ማንነት

ብፁዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በሲምፖዚዬሙ መዝጊያ በቀረበው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በተነበበው ቅዱስ ቃል እና “ውድ አማዞን” በሚለው የድህረ ሲኖዶስ ምክርን በማስታወስ ባሰሙት ስብከት፣ እያንዳንዱ ካህን ከሁሉም በፊት በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አማካይነት የክርስትና ሕይወት ምንጭ የሆነውን ጸጋ የሚያፈስ “የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ” መሆኑን አስረድተዋል። ይህም፣ ካኅን በምስጢረ ክኅነት ጸጋ አማካይነት ብቻ ሊቀበለው የሚችል ታላቅ ኃይል" እንደሆነ ገልጸው፣ የካኅን ብቸኛ ማንነት የሚገኘው በቅዱስ ቁርባን እና በኑዛዜ ምስጢራት ውስጥ መሆኑንም አስረድተዋል።

 “በክህነት መሠረታዊ ሥነ-መለኮት” ውስጥ ሊገኝ የሚችል ሌላ አካል” አለ ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ የካኅን “ማንነት” ሲያብራሩ፥ ካኅን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚኖር ሆኖ እያለ፣ ራሱን ከወንድሞቹ ሊለይ የሚችልበት ምንም ዓይነት ምርጫ እንደማይኖር ገልጸው፣ ካኅን ምን ጊዜም ከኢየሱስ ጋር የሚኖር፣ ምንም እንኳን የግል ማንነት መሠረታዊ ገጽታዎችን እየተገነዘበ፣ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ 'የእረኝነት በጎ አድራጎት' ባለው መሠረት በተለይም የሀገረ ስብከት ካህን ከአገልግሎት ወንድሞቹ ጋር አብሮ የሚኖር፣ ልዩ ባህሪይ ያለው መሆኑን አስረድተዋል። 

በወንድሞች መካከል

“እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንድንሆን፣ ክርስቶስን በመምሰል አቀበታማ የሕይወት ጉዞን እንድንራመድ፣ ከወንድሞቹ ጋር እንድንገናኝ እና ወዳጆቹ እንድንሆን መርጦናል” ያሉት ብጹዕነታቸው፣ የተራራውን አቀበት ከክርስቶስ ጋር የወጡት ደቀ መዛሙርት ሰዎችን በተለይም ድሆችን ለማግኘት ቁልቁለትቱንም መውረዳቸውን አስታውሰዋል። ሐዋርያቱ ዘወትር ከኢየሱስ ጋር እንጂ ብቻውን እንዳልቀሩ ያስታወሱት ብጽዕ አቡነ ፓሮሊን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ቁልቁለቱን ከሐዋርያቱ ጋር ወርዶ ከእነርሱ ጋር አብሮ ይሠራል” በማለት ተናግረዋል። ቀጥለውም፣ “የሲኖዶሳዊነት ጣዕም” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን “ትንቢታዊ ቃል” በማስታወስ “ካኅን በእግዚአብሔር ቃል እና ደግሞ ሕዝቡንም የሚያሰላስል ነው” በማለት ተናገረዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ፣ ካህን "ከሌሎች ወንድሞቹ ሁሉ ጋር በክስተቶች መካከል የእግዚአብሔርን መልእክት እንዴት ማንበብ እንደሚችል ለማወቅ ጥረት የሚያደርግ ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

አሉባልታ ወሬ የሚያከትለው አደጋ

ይህን መነሻ በማድረግም አንድ ካህን ለሚገለገልበት ቋንቋም ትኩረትን ሊሰጥ እንደሚገባ ያሳሰቡት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ “ካህን የሚጠቀምበትን የንግግር ዘዴን የመመዘን ከባድ ኃላፊነት እንዳለበት፣ አሉባልታ ወሬ አደጋን ሊያስከትል ይችላል” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙ ጊዜ መናገራቸውን አስታውሰዋል። ካህናት የተወደደውን የእግዚአብሔር ልጅ ለማድመጥ በተጠሩት መጠን፣ ሐዋርያው ​​ጳውሎስ ወደ ኤፌ. በላከው መልዕክቱ 4:29 ላይ “ከእንግዲህ ከቶ ከአፋችሁ ክፉ ቃል አይውጣ፤ ነገር ግን ለሚሰሙት ጸጋን የሚሰጥ እና ለማነጽ የሚጠቅም፣ ለሰዎችም አስፈላጊ የሆነውን ቃል ተናገሩ” ማለቱን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በቫቲካን የተዘጋጀውን ሲምፖዝዬም ለተሳተፉት ካኅናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ለምዕመናን ወገን ባቀረቡት ስብከት ተናግረዋል።

21 February 2022, 18:03