ፈልግ

በፓኪስታን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ በፓኪስታን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ 

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ተግዳሮት የሚመለከት ስብሰባ ተካሄደ

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እስካሁን ያስከተላቸውን ተግዳሮቶች የሚገመግም ስብሰባ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት መካሄዱ ተገለጸ። በላቴራን የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የተካሄደው ምክክር መጭውን ማኅበራዊ ሕይወት በማስተካከል ሁሉን አቀፍ ዘላቂ የኤኮኖሚ ግንባታን ማካሄድ እንደሚያስፈልግም ተወያይቷል። ስብሰባውን የምጣኔ ሃብት ባለሞያዎች የተካፈሉት ሲሆን በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጊዜያዊ ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ እና በጳጳሳዊ አካዳሚ የማኅበራዊ ሳይንስ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ስቴፋኖ ዛማኚ ስብሰባውን መካፈላቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ትናንት ጥር 4/2014 ዓ. ም. በሮም የተካሄደው ስብሰባው፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥያቄ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ትኩረቱም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኤኮኖሚ እና ማኅበራዊ ሕይወት ላይ ያደረሳቸውን ችግሮች ለመቋቋም በሚረዱ ዘዴዎች ላይ መምከሩ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ. በካቲት ወር  2020 ዓ. ም. በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ኮሚሽን መምሪያ ከፍተኛ ሃላፊዎችን ተቀብለው ባነጋገሯቸው ወቅት፣ መምሪያው ከፍተኛ ሃላፊነት የተጣለበት መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በወቅቱ ለመምሪያው ከፍተኛ አባለት ባስተላለፉት መልዕክት ኮሚሺኑ ቤተክርስቲያንን እና መላውን ሰብዓዊ ቤተሰብ ከወረርሽኙ ለመታደግ ከፍተኛ ሃላፊነት የተጣለበት መሆኑን ተናግረው፣ በየአገራቱ በሚገኙ ቤተክርስቲያኖች መካከል የጋራ ውይይቶችን በማካሄድ፣ በተለያዩ አገራት ውስጥ ተጨባጭ ዕርዳታዎችን ለማቅረብ የሚያግዙ እቅዶችን ማውጣት እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ መረጃ መሠረት በአውታ መረብ አማካይነት የተካሄደው ስብሰባ ዋና ዓላማ በወረርሽኙ ዙሪያ እንስካሁን የተደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶችን የሚገመግም ሲሆን፣ ወረርሽኙ አሁን ባለው የኤኮኖሚ እና ማኅበራዊ ሕይወት የታየውን አለመመጣጠን በመገንዘብ ኤኮኖሚያዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ዕድገቶችን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በአገራት፣ በማኅበረሰብ እና በግለሰብ ዘንድ እያደገ የመጣውን ኢፍትሃዊነት ለመዋጋት ሃላፊነት መውሰድ እንደሚገባ የሚያሳስብ እንደነበር ታውቋል።

ወደፊት ችግሮችን ለመጋፈጥ የሚያግዙ መመሪያዎች

ስብሰባው በወደፊቱ ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ባሕላዊ ተግዳሮቶች ላይ ለማሰላሰል እና ለመወያየት ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ችግሮችን ለመፍታት መመሪያዎችን ለማዘጋጀት ያለመ እንደነበር ተመልክቷል። ስብሰባው ላይ ተገኝተው ሃሳባቸው ያካፈሉት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጊዜያዊ ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መምሪያ አስተባባሪ የሆኑት እህት አሌሳንድራ ስሜሪሊ፣ በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ ምክትል ዋና ጸሐፊ ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ እና በጳጳሳዊ አካዳሚ የማኅበራዊ ሳይንስ ፕሬዚደንት የሆኑት ፕሮፌሰር ስቴፋኖ ዛማኚን ጨምሮ የተለያዩ የኤኮኖሚ እና ማኅበራዊ ሳይንስ ጠበብት መሆናቸው ታውቋል።

13 January 2022, 15:48