ፈልግ

ካርዲናል ክርስቶፍ፣ ሲኖዶሳውዊ ሂደት መደማመጥን፣ መጋራትን እና ማስተዋልን የሚጠይቅ መሆኑን ገለጹ

በኦስትሪያ የቪዬና ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ ሾንቦርን፣ የሲኖዶስን ትርጉም እና እሑድ መስከረም 30/2014 ዓ. ም. በይፋ የተጀመረውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ አስመልክተው ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በ 2016 ዓ. ም. በቫቲካን ለሚካሄደው የመላው ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ጊዜ በተደጋጋሚ ከሚነሱት ጥያቄዎች መካከል አንዱ “ሲኖዶሳዊነት ማለት ምን ማለት ነው?” የሚል ሲሆን ለዚህ ጥያቄ ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ መልስ ሲሰጡ፥ ሲኖዶስ ወይም የቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት ማለት “በኅብረት መጓዝ” ማለት እንደሆነ አስገንዝበዋል። አክለውም በጋራ መጓዝ ስለምንችልበት መንገድ ተሰብስበን መወያየት እና መመካከር ያስፈልጋል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በዓለማች ውስጥ ብዙ ሰዎች በተረጋጋ ሁኔታ ላይ እንዳልሆኑ የገለጹት ካርዲናል ክርስቶፍ ስደተኞችን እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል።

ሲኖዶስ የሚገለጽበት ሁለተኛው መንገድ፣ በሕብረት መጓዝ ብንልም ይህን ጉዞ ብቻችን ማካሄድ አንችልም ያሉት ካርዲናል ክርስቶፍ፣ መሠረታዊ እውነታው ቤተክርስቲያንን የሚመለከት መሆኑን አስረድተው፣ በቤተክርስቲያን ሕይወት ሁለት ወገኖች መኖራቸውን እነርሱም አስተማሪ ቤተክርስቲያን እና ተማሪ ቤተክርስቲያን መሆናቸውን ገልጸው፣ አስተማሪ ቤተክርስቲያን የምንለው ቤተ ክኅነቱ ሲሆን ተማሪ ቤተክርስቲያን የሚባሉት ምዕመናን መሆናቸውን አስረድተዋል።

ሁላችንም የእግዚአብሔር ሕዝቦች ነን

የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆናችንን ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ እንደሚገልጽ ያስታወሱት ካርዲናል ክርስቶፍ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ስለ ቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት ሲናገሩ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ከተናገረን የተለየ አይደለም ብለዋል። ገና ብዙ መማር እንዳለብን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መናገራቸው ትክክል እና እውነት መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ፣ ለመማር ደግሞ ብዙ ማድመጥ ያስፈልጋል ብለው፣ በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ ካህናትን እና ምዕመናንን ለማድመጥ ጥረት እንደሚያደርጉ እና በአገራቸው ውስጥ በሚገኙ አምስት ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ላለፉት አሥር ዓመታት ያህል እርስ በእርስ በመደማመጥ በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ ያለውን ስንጋራ ቆይተናል ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አይደለም

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ በቁጥር የሚበልጥ የአንድ ወገን ፍላጎት ለማስጠበቅ እንደቆመ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አይደለም በማለት ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙን ጊዜ መናገራቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ፣ ሲኖዶስ መመሪያዎችን የሚያገኘው ከቤተክርስቲያን እና ከሐዋርያት ሥራ መሆኑን አስረድተዋል። ሐዋርያት በሲኖዶሳዊ አካሄድ ችግሮቻቸውን እንዴት ሊፈቱት እንደቻሉ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለሮም ሀገረ ስብከት መናገራቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ፣ ቅዱስነታቸው በሐዋ. ምዕ. 15 ላይ የተጻፈውን በመጥቀስ፣ አረማዊያን አስቀድመው ወደ አይሁድ እምነት ቀጥለውም ወደ ክርስትና እምነት እንዲመጡ ሃሳብ በቀረበ ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ እና በርናባስ በኢየሱስ ማመን በቂ ነው ባሉት ሃሳብ ላይ ሁለቱ ወገኖች መወያየታቸውን አስታውሰዋል። በውይይታቸው ወቅት እርስ በእርስ መደማመጥ ብቻ እንጂ ምክር ቤት አለመቋቋሙን ያስረዱት ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ፣ ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዳስረዱት ሁሉ እርስ በእርስ መደማመጥ ሲባል፣ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ በምትገኝ ትንሿ ክብ ብቻ ሳንገደብ ክርስቲያን እና ክርስቲያን ያልሆኑ የብዙ ሰዎች ታሪክ ለማድመጥ የተዘጋጀ ጆሮ ሊኖረን ይገባል ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ቀጥሎ ምን ማድረግ ይቻላል?

መላው ካቶሊካዊ ምዕመናን ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ሆነው የሚጠብቁት፣ ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ተሰብስበው እንዳደረጉት ሁሉ በሕይወት ልምዳቸው ላይ መወያየት መሆኑን ገልጸዋል። ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ፣ በዚህ ሲኖዶሳዊ የምክክር ወቅት ሀገረ ስብከታቸው በምዕመናን መካከል ውይይቶችን በማካሄድ ስለ ክርስትና ሕይወት ልምድ እና እምነትን ለልጆቻቸው ማስተላለፍን በማስመልከት ውይይት የሚያካሂዱ መሆኑን አስረድተዋል።

ምዕመናንን መሳተፍ

የምዕመናን ተሳትፎ መሠረታዊ አስፈላጊነት የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ፣ በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ አረጋዊያን ወጣቶች እና ሕጻናት የክርስትና ሕይወት ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ዕድል የሚሰጣቸው መሆኑን አስረድተዋል። በሌሎች የእምነት ተቋማት ውስጥ በርካታ ምዕመናን መኖራቸው፣ በተለይም ወጣቱ ትውልድ በልጦ መገኘቱ እርስ በእርስ በመደማመጣቸው እና የሕይወት ልምዳቸውን ስለሚናገሩ ነው ብለው፣ በየእሑዱ የሚቀርቡ የወንጌል ንባባትን ማዳመጥ፣ ‘ለክርስቲያናዊ ሕይወት የሚሰጡት ጥቅም እንደሆነ፣ ከእነዚህ ንባባት ምን እንማራለን?' ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል ብለዋል።

በኦስትሪያ የቪዬና ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ ሾንቦርን በቃለ ምልልሳቸው መጨረሻ ላይ “እግዚአብሔር ዛሬ የሚነግረንን ፣ በግል ፣ በማኅበረሰባችን ፣ በአገራችን ፣ በቤተክርስቲያናችን እና በዓለም አቀፍ ደረጃም እንዴት ማስተዋል እንደሚቻል መማር አለብን” ብለዋል።

14 October 2021, 16:44