ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ 

ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማካሄድ ወደ ሶርያ መጓዛቸው ተገለጸ

በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ የዘጠኝ ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማካሄድ ወደ ሶርያ ተጉዘዋል። ብጹዕነታቸው በጉብኝታቸው ወቅት በጦርነት እና በአመጽ ጉዳት የደረበትን ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ እና ብጹዓን ጳጳሳትን ጎብኝተው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን አባታዊ ቅርበት ለመግለጽ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ሶርያን ለመጎንኘት የነበራቸው ዕቅድ እ. አ. አ ባለፈው ሚያዝያ ወር 2020 ዓ. ም. ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መራዘሙ ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ወደ ሶርያ ያደረጉት ጉብኝት ዋና ዓላማ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጦነት ለተጎዳው የሶርያ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ድጋፍ ለመግለጽ መሆኑ ታውቋል።

መጀመሪያ በደማስቆ ቆይታ ያደርጋሉ

ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ወደ ሶርያ ሲደርሱ የጉብኝታቸው መጀመሪያ ቦታ ደማስቆ ሲሆን፣ ከሶርያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት እና የአንጾኪያ ግሪክ ካቶሊካዊ ፓትሪያርክ ከሆኑት ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ዩሱፍ አብሲ ጋር የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚያሳርጉ መሆናቸው ታውቋል።

ብጹዕ ካርዲናል ሳንድሪ ከመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ቀጥለው በደማስቆ እና በቦስራ-ሃውራን ወረዳዎች የሚገኙ የመልቃይት ግሪክ የአምልኮ ሥርዓትን የሚከተሉ ካቶሊካዊ ካህናትን ካገኙ በኋላ በአካባቢው የሚገኘውን ካቶሊካዊ በጎ አድራጊ ጽሕፈት ቤትን፣ በቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር የሚመራ የወላጅ አልባ ሕጻናት መንከባከቢያ ማዕከልን እንደሚጎበኙ ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ በጣሊያን እና ፈረንሳይ መንግሥታት የሚታገዙ ሆስፒታሎችን እና የሳሌዢያን ቅዱስ ዶን ቦስኮ ማኅበር ዋና ጽሕፈት ቤትን ጎብኝተው፣ የከሌዳዊያን እና የአርሜኒያ ቤተክርስቲያናትንም የሚጎበኙ መሆናቸው ታውቋል።

ታርቱስ፣ ሆምስ፣ አሌፖ፣ ያብሮድ እና ማሎኡላ ይጎበኛሉ

ብጹዕ ካርዲናል ሳንድሪ ጉብኝታቸውን በመቀጠል በሶርያ ውስጥ የሚገኙ ታርቱስ፣ ሆምስ፣ አሌፖ፣ ያብሩድ እና ማሎኡላ የተባሉ አካባቢዎችን ጎብኝተው በምሥራቅ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ መሠረት የሚፈጸመውን መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚካፈሉ ተገልጿል። ቀጥለውም ወደ አሌፖ ከተማ የአካባቢው ካህናት፣ ደናግል፣ ምዕመናን እና የዕርዳታ ድርጅት ሃላፊዎች የሚካፈሉበትን፣ በላቲን የአምልኮ ሥርዓት የሚቀርብ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚመሩ ተገልጿል። በአሌፖ ከተማ በሚካሄድ የአብያተ ክርስቲያናት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው በአሌፖ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ስድስት ካቴድራሎች ውስጥ ጸሎት እንደሚያቀርቡ ታውቋል። በመጨረሻም ያብሩድ እና ማሎኡላ የተባሉ አካባቢዎችን ከጎበኟቸው በኋላ ወደ ደማስቆ ተመልሰው ዕሮብ ጥቅምት 24/2014 ዓ. ም. ወደ ሮም የሚመለሱ መሆናቸው ታውቋል።             

26 October 2021, 17:06