ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፣ “የተራቡትን ከመመገብ በተጨማሪ የመቋቋሚያ ግብዓቶችንም ማቅረብ ያስፈልጋል” አሉ።

በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት የሚከታተል ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር፣ መስከረም 15/2014 ዓ. ም በምግብ ሥርዓት ላይ ለተወያየው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ መልዕክት አስተላልፈዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር ለጉባኤው ተካፋዮች በላኩት የቪዲዮ መልዕክት፣ ቅድስት መንበር በዓለም ውስጥ የምግብ ምርትን በእኩልነት ለማድረስ በሚደረግ ጥረት ሙሉ ትብብር የምታደርግ መሆኗን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጋላገር ለጉባኤው ተካፋዮች በላኩት መልዕክታቸው፣ “የምግብ ስርዓቶችን ለመለወጥ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመዋጋት ዓለም አቀፋዊ እርምጃን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። ይህን አስመልክተው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ረሃብ በሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ አሳዛኝ ሰብአዊ አደጋ ብቻ ሳይሆን ፣ እውነተኛ የማፈሪያ ምክንያትም ነው” ማለታቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር አስታውሰዋል። በመሆኑም “መግለጫዎችን እና ስትራቴጂዎች ከማውጣት አልፎ ወደ ውጤታማነት ለመሸጋገር የሚያግዝ አስቸኳይ እርምጃ ለመወሰድ ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል። ወሳኙ ጥያቄ፣ እ. አ. አ የ 2030 ዓ. ም. የዘላቂ ልማት አጀንዳ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ፣ ከ COVID-19 ወረርሽኝ በኋላ የሚኖሩንን የምግብ ስርዓቶች በማደስ እና የፕላኔታችንን ታማኝነት በመጠበቅ የእያንዳንዱን ሰው አጠቃላይ እድገት ማሳደግ የሚል መሆኑን አስረድተዋል።   

ባለፈው ሐምሌ ወር 2013 ዓ. ም በተካሄደው በቅድመ-ጉባኤ ስብሰባ ወቅት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ችግሮችን ተቋቋመን ፣ አካባቢያዊ ኢኮኖሚን ለማጠናከር ፣ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ለማሻሻል ፣ የምግብ ብክነትን ለመቀነስ ፣ ጤናማ እና ተደራሽነት ያላቸውን ምግቦች ለሁሉም ለማቅረብ ፣ የፍጥረታት ዘላቂነትን ለመጠበቅ እና የአከባቢ ባህሎችን ለማክበር መጣር አለብን” ማለታቸውን  ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጋላገር አስታወሰዋል።

ለተከበረ ሕይወት

የዕለት ምግብን ማግኘት መሠረታዊ የሰው ልጅ መብት እንደሆነ እና የተከበረ ሕይወት ለመኖር አስፈላጊ መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጋላገር አስገንዝበዋል። “የተራቡትን መመገብ በቂ አይደለም” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፣ ከዚህም በተጨማሪ ድሆችን እና ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑትን ለረጅም ጊዜ እራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማቅረብ አለብን ብለዋል። ከግብዓቶቹ መካከልም “ለመሬት አጠቃቀም እና ባለቤትነት ፣ ለገንዘብ አቅም እና ስልጠና ሰፊ ዕድሎችን ማመቻቸት” የሚሉ መሆናቸውን አስረድተዋል። ዘላቂ የምግብ ስርዓቶች ለሁሉም ገንቢ ምግብን ማቅረብ ይኖርባቸዋል ያሉት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፣ ፍትሃዊ የኑሮ ዘይቤዎችን መደገፍ እና የምርት እና የፍጆታ ሞዴሎችን ማስተዋወቅ ይኖርባቸዋል” ብለው፣ የእያንዳንዱን ሰው ተፈጥሮአዊ ክብርን ለማስጠብቅ፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ለመጠበቅ “የብክንነት ባህልን” በ “እንክብካቤ ባህል” መተካት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ስኬታማ ለመሆን

በዕቅዶች ስኬታማ ለመሆን ፣ የሰውን ልጅ ፣ ኢኮኖሚያዊ አቀምን፣ አካባቢያዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ድጋፎችን የሚያዋህዱ የምግብ ሥርዓቶች ራዕይን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለው፣ ያህን ራዕይ እውን ለማድረግ ድጋፍ እንደምታደርግ ቅድስት መንበር ለዓለም አቀፉ ማኅበሰብ ማረጋገጧን ሊቀ ጳጳሱ ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጋላገር መልዕክታቸውን ለጉባኤው ተካፋዮች ያስተላለፉት፣ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በአዳጊ ሕፃናት ላይ እያደረሰ ያለውን አስከፊ አደጋ አስመልክቶ የማስጠንቀቂያ ሪፖርት ካወጣ ከጥቂት ቀናት በኋላ መሆኑ ታውቋል።

ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ የዓለም ሕፃናት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚሰቃዩ እና ከእነዚህም መካከል 23 ሚሊዮን የሚሆኑ ዕድሜያቸው ከ 2 ዓመት በታች መሆናቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል።

25 September 2021, 15:28