ቅድስት መንበር፣ በሊባኖስ ውስጥ ችግሮች ከመብዛታቸው በፊት ዕርዳታ ሊናደርግላት ይገባል አለች

በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ አቡነ ሚሮስላው ቫኮቭስኪ ፈረንሳይ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአጋርነት ላዘጋጁት ጉባኤ በላኩት የቪዲዮ መልዕክት፣ ከአንድ ዓመት በፊት ከፍተኛ የሰው እና የንብረት ጥፋት የደረሰባት ቤይሩት ወደ ተረጋጋ ማኅበራዊ ሕይወት የምትደርስበትን አጋጣሚ ልናመቻችላት ይገባል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ሊባኖስ በከፋ ችግር ውስጥ ከመውደቋ በፊት” ያሉት ብጹዕ አቡነ ሚሮስላው፣ በሊባኖስ ጉዳይ ላይ ውይይት በማድረግ ላይ ለሚገኝ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በላኩት መልዕክት፣ ሊባኖስ አሁን ከምትገኝበት ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች በተጨማሪ ወደ ፊት ሊያጋጥማት በሚችሉ ችግሮች ላይ በመወያየት ተግቢው ምላሽ ልንሰጥ ይገባል ብለዋል። በሊባኖስ የባሕር ወደብ ከአንድ ዓመት በፊት የተከሰተው ኃይለኛ ፍንዳታ ለ200 ሰዎች የሕይወት መጥፋት እና በስድስት ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋን ማስከተሉ ይታወሳል። ይህን በማስታወስ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ ሐምሌ 1/2021 ዓ. ም ከተቀሩት የሐይማኖት መሪዎች ጋር ሆነው ሊባኖስን በጸሎታቸው ማስታወሳቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በጸሎት ሥነ ሥርዓቱ ማጠቃለያ ባስተላለፉት መልዕክት፣ “ሊባኖስ ካጋጠማት ችግር ወጥታ ራሷን እስክትችል ድረስ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስፈላጊውን ዕርዳታ ሊያደርግላት ይገባል” ማለታቸውን ብጹዕ አቡነ ሚሮስላው አስታውሰዋል።

የመልካም ለውጥ ጉዞ

በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ሚሮስላው በቪዲዮ መልዕክታቸው፣ ቅድስት መንበር፣ ይህ ጉባኤ፣ ሊባኖስን በገንዘብ በመርዳት፣ አሁን ከምትገኝበት ችግር በላይ በከፋ ችግር ውስጥ እንዳትወድቅ ሁኔታዎችን እንደሚያመች ተስፋ የምታደርግ መሁኗን ገልጸው፣ ነገር ግን ሊባኖስ አሁን ከምትገኝበት ችግር በማገገም፣ ዜጎቿን በሙሉ በሚጠቅም የለውጥ ጎዳና መጓዝ መጀመር ይኖርባታል ብለዋል።

ሕዝቡን መርጃ የሚሆን 350 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰብ

ትናንት ሐምሌ 28/2013 ዓ. ም በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 6፡00 እስከ ቀኑ 9፡30 ድረስ በፓሪስ ከተማ የተዘጋጀው ጉባኤ ዋና ዓላማ፣ እስካሁን ያለ ማዕከላዊ መንግሥት የምትገኝ ሊባኖስ አገሪቱ በታሪክ እስከዛሬ አጋጥሟት በማያውቅ የከፋ ችግር ውስጥ ከመውደቋ በፊት ድጋፍን ለማድረግ የሚያስችል የ350 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ዕርዳታን ለማሰባሰብ ያለመ መሆኑ ታውቋል። በዚህ የገንዘብ ዕርዳታ አማካይነት የአገሪቱን ዜጎች ለመርዳት እና የመድኃኒት እጥረትን ለማቃለል የታሰበ መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ትናንት ሐምሌ 28/2013 ዓ. ም በጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህረት ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በፓሪስ የተዘጋጀው ጉባኤ ፍሬያማ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ መግለጻቸው ይታወሳል። የተበባሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም በበኩላቸው፣ “በችግር ውስጥ የምትገኘውን ሊባኖስ በጋራ መልሶ ለመገንባት ጥረት የምናደርግበት ጊዜ አሁን ነው” ማለታቸው ይታወሳል።  

በቤሩት ፍንዳታ ፣ “ተጨማሪ አሳዛኝ”

ብጹዕ አቡነ ሚሮስላው በቪዲዮ መልዕክታቸው የፈረንሳዩን ፕሬዚደንት ክቡር አቶ አማኑኤል ማክሮንን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ለጥረታቸው አመስግነው፣ ሊባኖስ ችግር ውስጥ ከገባችበት ጊዜ አንስቶ ዕርዳታን ሲያደርግ የቆየውን ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብንም አመስግነዋል። አክለውም ቅድስት መንበር እና ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅቶች በሊባኖስ ውስጥ በተለይም ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተሰቦች ለማቋቋም፣ የጤና እና የትምህርት ማዕከላትን መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ የገንዘብ ዕርዳታ ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በተለያዩ ጊዜያት ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ “ቅድስት መንበር ያችን አገር ከችግር ለማውጣት ያላት ምኞት እና ጥረት ከፍተኛ ነው” ማለታቸውን በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ አቡነ ሚሮስላው ቫኮቭስኪ ገልጸዋል።

ሊባኖስ፥ ጠቅላላ የሰላም መልዕክት

“ሊባኖስ ለዘመናት ያህል አብሮ የመኖር ባሕልን በተግባር የገለጸች አገር ናት” ያሉት ብጹዕ አቡነ ሚሮስላው፣ “መልካም እሴቶቿ በከንቱ መጥፋት እንደሌለባቸው፣ ሊባኖስ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት በሚጥሩ አካላት ወጥመድ ውስጥ እንድትገባ መተው አያስፈልግም” ብለዋል። አክለውም “ሊባኖስ ከአገር በላይ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች መካከል የሰላም እና የወንድማማችነት ተምሳሌት ናት” በማለት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና ከእርሳቸውም በፊት የነበሩ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መግለጻቸውን አስታውሰው፣ በመሆኑም ሊባኖስ ይህን ጥሪዋን በተግባር መመስከር መቀጠል አለባት ብለዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ ሐምሌ 1/2021 ዓ. ም ከተቀሩት የሐይማኖት መሪዎች ጋር ሆነው ለሊባኖስ መጸለያቸውን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ሚሮስላው፣ ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክታቸው “በሥልጣን ላይ ያሉት በሙሉ የራሳቸውን ጥቅም ከማስቀደም ይልቅ በእውነተኛው የሰላም አገልግሎት ላይ ማትኮር አስፈላጊ ነው” ማለታቸውን እና “ጥቂቶች በብዙሃኑ የልፋት ውጤት ላይ መቆም ሊያበቃ ይገባል !” ማለታቸውን ብጹዕነታቸው አስታውሰዋል።

ማክሮን - ቅድሚያ የሚሰጠው መንግሥት መመሥረት ነው

ትናንት ሐምሌ 28/2013 ዓ. ም በፈረንሳይ ፓሪስ የተጀመረውን ጉባኤ በንግግር የከፈቱት የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ አማኑኤል ማክሮን፣ ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው በሊባኖስ ለውጥን ሊያመጣ የሚችል  ማዕከላዊ መንግሥት መመሥረት እንደሆነ አሳስበው፣ የፈረንሳይ መንግሥት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያደርገው ግፊት እንዳለ ሆኖ፣ የሊባኖስ የፖለቲካ ሁኔታ አሁንም ያልተረጋጋ መሆኑን አስረድተው፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናጂብ ሚክራቲ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት እየሞከሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የፈረንሳይ እና የአሜሪካ ኢኮኖሚያዊ ጥረት

ሊባኖስን ሁለት ጊዜ የጎበኙት የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ አማኑኤል ማክሮን ትናንት እንዳስታወቁት መንግሥታቸው ለሊባኖስ የሚውል 100 ሚሊዮን ዩሮ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ማድረጉን፣ ከ500 ሺህ በላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መድኃኒቶችን መመደቡን ገልጸዋል። በተመሳሳይ መልኩ ሰሜን አሜሪካም በበኩሏ በሊባኖስ ውስጥ ለሰብዓዊ ዕርዳታ የሚውል የ100 ሚሊዮን ዶላር መለገሷን አስታውቃ ይህም አሜሪካ በመጨረሻዎቹ ዓመታት ለሊባኖስ ያደረገችውን የዕርዳታ መጠን ወደ 560 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ማድረጉን ገልጻለች። የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ አማኑኤል ማክሮን በመልዕክታቸው አስረግጠው እንደተናገሩት፣ “የሊባኖስ ፖለቲከኞች ኢኮኖሚውን ለማሻሻል እና በሀገሪቱ ውስጥ ሙስናን ለመዋጋት አስፈላጊውን እርምጃ ካልወሰዱ በቀር የሚደረግላት ዕርዳታ ሁሉ መቼም ቢሆን አይበቃትም” ብለዋል።      

05 August 2021, 16:20