16ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ 16ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ 

አቡነ ማሪን፣ የጳጳሳት ሲኖዶስ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚገናኙበት መድረክ መሆኑን ገለጹ

በካቶሊክ ቤተክርስቲያን የብጹዓን ጳጳሳት ሶኖዶስ ምክትል ዋና ጸሐፊ እና የስነ-መለኮት ኮሚሽን አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሉዊስ ማሪን ዴ ሳን ማሪን፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች እርስ በእርስ የሚገናኙበት ወይም የሚተዋወቁበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ የቤተክርስቲያን አንድነት በገሃድ የሚገለጽበት፣ የጊዜውን እውነታ በሚገባ በማስተዋል የጋራ ግንዛቤ የሚገኝበት መድረክ መሆኑ አስረድተዋል። በሚቀጥለው ጥቅምት ወር 2014 ዓ. ም የሚከበረው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ሂደት ማስጀመሪያ በዓል ዋና ዓላማ፣ እግዚአብሔር እኛን ወደ ቤተክርስቲያኑ መካከል ልኮን በኅብረት እንድንጓዝ የሚያስታውሰን ጊዜ ነው” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን    

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የቤተክርስቲያን አንድነት በተግባር የሚገለጽበት፣ እያንዳንዱ ምዕመን እንደ ምዕመን፣ እያንዳንዱ የቤተክኅነት አባል እንደ ቤተክኅነት አባል ከእግዚአብሔር በተሰጠው የአገልግሎት ጸጋ አማካይነት ከወንድሞች እና እህቶች ጋር በመተባበር ለቤተክርስቲያን የበኩሉን ድጋፍን የሚሰጥበት መድረክ መሆኑን ብጹዕ አቡነ ሉዊስ ማሪን ዴ ሳን ማሪን አስረድተዋል። አቡነ ሉዊስ ማሪን ዴ ሳን ማሪን ይህን ካሉ በኋላ እ. አ. አ በ2023 ዓ. ም በቫቲካን ውስጥ ለሚካሄደው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ቅድመ ዝግጅት በእያንዳንዱ አገር ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች የሚጀምረው በመስከረም 29 እና30/2014 ዓ. ም በሚደረግ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት መሆኑን ገልጸዋል።

የአስተሳሰብ ለውጥ የሚታይበት መድረክ ነው

አቡነ ሉዊስ ማሪን ዴ ሳን ማሪን በመግለጫቸው፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ እያንዳንዱ የቤተክርስቲያን አባል ወይም ምዕመን ከእግዚአብሔር የተቀበለውን የአገልግሎት ጸጋ፣ መንፈስ ቅዱስ የሚያሳየውን መንገድ በመከተል ሃላፊነት በተመላበት መንገድ በተግባር የሚያስመሰክርበት መድረክ መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑም ምዕመን እንደ ምዕመን፣ ቤተክኅነት እንደ ቤተክኅነት ለቤተክርስቲያን አንድነት እና ዕድገት የበኩሉን እገዛ የሚያቀርብበት መድረክ እንጂ የርዕዮተ ዓለም ግጭቶች የሚታዩበት መድረክ አለመሆኑን አስረድተዋል።

ማስተዋል እና ፍሬያማ አገልግሎት የሚታይበት ነው

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ምዕመናን፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ ካኅናት እና ጳጳሳት ተሳትፎአቸውን በማሳደግ የሚሳተፉበት መድረክ እንደሆነ የገለጹት፣ አቡነ ሉዊስ ማሪን ዴ ሳን ማሪን፣ በዚህ አካሄድ ውስጥ ሁለት የሥራ ድርሻ መኖራቸውን ገልጸው፣ የመጀመሪያው በቅድመ ዝግጅቱ ወቅት በሮም የሚካሄደውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የሚካፈል ጳጳስ፣ እንደ ሐዋርያዊ አባትነቱ በሀገረ ስብከቱ ከሚገኙ ምዕመናን ልብ የሚመጡ ሃሳቦችን እና አስተያየቶች መቀበል እንደሆነ የብጹዓን ጳጳሳት ሶኖዶስ ምክትል ዋና ጸሐፊ እና የስነ-መለኮት ኮሚሽን አስተባባሪ ብጹዕ አቡነ ሉዊስ ማሪን ዴ ሳን ማሪን ገልጸዋል። በቀጣዩ ሂደትም ከምዕመናን የተሰበሰቡ አስተያየቶችን እና ሃሳቦች የሀገር ስብከቱ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ከቁምስና ምክር ቤት ተወካዮች ጋር ሆነው በጋራ ከማጤን በተጨማሪ ሌሎችንም ፍሬያማ የአገልግሎት መንገዶችን የሚያክሉበት ወቅት ይሆናል ብለው፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የቤተክርስቲያንን አንድነት እና ዕድገት የሚያጠናክሩ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ሃሳቦች የሚገኝበት መድረክ ቢባልም ብቸኛው መድረክ እንዳልሆነ ብጹዕ አቡነ ሉዊስ ማሪን ዴ ሳን ማሪን አስረድተዋል።

በክርስቲያኖች መካከል አንድነት

“በአንድነት ለመራመድ አንድ ላይ እንሁን” በሚለው መሪ ቃል፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የፈለጉት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ኅብረትን በመፍጠር፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን የተልዕኮ ጥሪ እውን የሚያደርጉበት መንገድ መሆኑን አቡነ ሉዊስ ማሪን ዴ ሳን ማሪን አስረድተው፣ ቅዱስ አንጦንዮስ “ክርስቲያኖች በክርስቶስ አንድ ካልሆኑ በቀር በመካከላቸው አንድነትን ሊያመጡ አይችሉም” ማለቱን አስታውሰዋል።

የተለያዩ አገልግሎቶች እና ጥሪዎች

ለብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስን ስኬታማነት ከቀረቡት የተግባር መርሃ-ግብሮች መካከል ሁለተኛው የክርስቲያኖችን አንድነት የሚያጠናክር የጋራ ስነ-መለኮታዊ ጥናት መሆኑን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ሉዊስ ማሪን ዴ ሳን ማሪን፣ ይህም በሁሉም ዘርፎች ቤተክርስቲያንን የሚያጠና ሥነ-መለኮታዊ ትምህርት መሆኑን አስረድተዋል። በክርስቲያኖች መካከል የተለያዩ አገልግሎቶች እና ጥሪዎች ቢኖሩም ክርስቲያኖች በሙሉ የእግዚአብሔር ሕዝቦች መሆናቸውን ገልጸዋል። የሲኖዶስ ዋና ትርጉሙ ይህ ነው ያሉት፣ በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የስነ-መለኮት ኮሚሽን አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሉዊስ ማሪን ዴ ሳን ማሪን፣ በእውነተኛ የክርስትና ሕይወት ውስጥ አስፈላጊው የሥልጣን ወይም የአስተዳደር ክፍፍል ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሚገለጥ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው ብለዋል። 

በሲኖዶሳዊ ሂደት ውስጥ የስነ-መለኮት ኮሚሽን አስተዋጽኦ 

በካቶሊክ ቤተክርስቲያን የብጹዓን ጳጳሳት ሶኖዶስ ምክትል ዋና ጸሐፊ እና የስነ-መለኮት ኮሚሽን አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሉዊስ ማሪን ዴ ሳን ማሪን፣ የሲኖዶሱን ሂደት ለማገዝ ባቀረቡት ስነ-መለኮታዊ አስተዋጽዖ፣ በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መከከል ስነ-መለኮት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው፣ ሁለተኛው የቫቲካ ጉባኤ “Gaudium et Spes” ወይም “ደስታ እና ተስፋ” ባለው ሐዋርያዊ ሰነዱ፣ የሥነ-መለኮት ትምህርት፣ የዘመናችን ሕዝብ በእምነቱ ግንዛቤን እንዲኖረው ለማድረግ፣ እግዚአብሔር አብ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን በመልበስ መገለጡን እና የመዳንን ወንጌል መመስከር እንድንችል ጥበብን ያቀዳጃል ብለዋል። 

ጳጳሳዊ ሲኖዶስ አራት ኮሚሽኖች አሉት

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በአራት ኮሚሽኖች የተዋቀረ ሲሆን እነርሱም ከ19 አገራት የተወጣጡ ሃያ አምስት አባላት ያሉበት የስነ-መለኮት ኮሚሽን፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚሽን፣ የመንፈሳዊ አገልግሎት ኮሚሽን እና የማኅበራዊ መገናኛ ኮሚሽን መሆናቸውን በካቶሊክ ቤተክርስቲያን የብጹዓን ጳጳሳት ሶኖዶስ ምክትል ዋና ጸሐፊ እና የስነ-መለኮት ኮሚሽን አስተባባሪ፣ ብጹዕ አቡነ ሉዊስ ማሪን ዴ ሳን ማሪን ገልጸዋል። 

19 August 2021, 16:35