የጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት የጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት  

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የፍቅር እና የታማኝነት ምሳሌ መሆናቸው ተገለጸ

እ. አ. አ ከጥቅምት 15/2020 ጀምሮ በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች የሚከታተል ጳጳስዊ ምክር ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የቤተክርስቲያን ፍቅር እና ታማኝነት ምሳሌ መሆናቸውን ገልጹ። ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ካረፉ ከ43 ዓመታት በኋላም ቢሆን የእምነት ምስክርነታቸው እንደ ብርሃን ደምቆ የሚታይ መሆኑን በቫቲካን ውስጥ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ከመሞታቸው አስቀድመው ስለ ሞት በማስተንተን በጻፉት መጽሐፋቸው “በብርሃን ውስጥ መኖር ምን ያህል እመኛለሁ” ማለታቸውን ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ አስታውሰው፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ካረፉት ከ43 ዓመታት በኋላ ዛሬም በብርሃን ውስጥ መገኘታቸውን ፣ ሐምሌ 30/2013 ዓ. ም ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ አስታውሰዋል።

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የተናገሩትን ወንጌላዊ መልዕክቶችን የጠቀሱት ብጹዕ ካርዲናል ስመራሮ፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የተቀዳጁትን ብርሃናዊ አካል ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛም መቀዳጀታቸውን አስረድተዋል። ይህም ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የተናገሩት የቤተክርስቲያን ማረጋገጫ መሆኑን አስረድተው፣ ቤተክርስቲያንም ካለፈው ጊዜ ይልቅ ዛሬ በሚገባ ተገንዝበዋለች ብለዋል።

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛን የሕይወት ታሪክ ለማስታወስ ዕድል ያገኙት ብጹዕ ካርዲናል ስመራሮ ከሮም ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ እና ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፣ እ. አ. አ በ1978 ዓ. ም ባረፉባት የካስተል ጋንዶልፎ ከተማም የዕረፍታቸውን 43ኛ ዓመት መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን የሚያቀርቡ መሆኑን ገልጸዋል። ብጽዕናቸው እና ቀጥሎም ቅድስናቸው በታወጀባቸው ዓመታት ስለ ር. ሊ. ጳ ጳውሎስ 6ኛ የተነገሩ የሕይወት ታሪኮች፣ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወቅትም የሚዘከሩ እና የእኝህ ታላቅ መንፈሳዊ አባት የሕይወት ታሪኮች የበለጠ ብሩህ ሆነው በልባችን ውስጥ የሚቆዩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የጳጳሳዊ ሕንጻዎች ዳይሬክተር የነበሩት ክቡር አቶ ሳቨሪዮ ፔትሪሎ በመስዋዕተው ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ መገኘታቸውን፣ ከእርሳቸውም ጋር የታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ወ/ሮ ኤሊያና ቨርሳቼ በካስተል ጋንዶልፎ ጳጳሳዊ መኖሪያ ሕንጻ ውስጥ የሚገኘውን እና ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ለመጨረሻ ጊዜ ያረፉባትን ክፍል ማስጎበኘታቸውን ብጹዕ ካርዲናል ስመራሮ ገልጸዋል። በሮም ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ በካስተል ጋንዶልፎ ከተማ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በኖሩበት የር. ሊ. ጳጳሳት መኖሪያ እና በውስጡ የተመለከቷቸው ቦታዎች ለር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ያላቸውን ፍቅር ከምን ጊዜም የበለጠ ለማሳደግ የረዳቸው መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ስመራሮ አስረድተዋል። ብጹዕነታቸው አክለውም፣ “ቅዱስ አባታችን ር. ሊ. ጳ ፍራንቸስኮ ወደ አዲስ የቤተክርስቲያን አገልግሎት እንድዛወር ጥሪ ካደረጉ በኋላ ያንን ውድ ሀገረ ስብከት ለቅቄ ስወጣ ፣ የር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ዕረፍት 43ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ለማክበር ከልብ እመኝ ነበር” ብለዋል።

የር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ዕረፍት 43ኛ ዓመት መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ከሁለተኛው የሐዋርያው ጴጥሮስ መልዕክት ምዕ. 1:18 ላይ፣ “ከእርሱ ጋር በተቀደሰው ተራራ ላይ በነበርንበት ጊዜ ይህን ከሰማይ የመጣውን ድምጽ እኛ ራሳችን ሰምተናል” የሚለውን ብጹዕ ካርዲናል ስመራሮ በማስተወስ፣ መልዕክቱ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛን ከማስታውስ ይልቅ ለማስተንተን የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል። ሆኖም ግን፣ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በጥልቅ የሚያስተነትኑ በመሆናቸው አብዛኞቹ ጽሑፎቻቸውን ፣ በተለይም የግል ጽሑፎቻቸውን በማንበብ በትክክል ምስጢራዊ እንደሆኑ በግሌ እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል። “የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን” በማለት በኢየሱስ ክርስቶስ ግልጸት ዕለት መታሰቢያ ዕለት እ. አ. አ ነሐሴ 6/1964 ዓ. ም ይፋ ያደረጉት የመጀመሪያው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ለዚህ ማረጋገጫ ይሆናል ብለዋል። ይህ የመጀመሪያው የር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ለጋራ ውይይት በር መክፈቱን አስታውሰው፣ እግዚአብሔር አብ ከሰማያት ሆኖ ለሰዎች በሙሉ እንዲናገሩ ለሙሴ፣ ለኤሊያስ እና ለኢየሱስ ክርስቶስ ድምጹን ማሰማቱ፣ በምድረ ገነት ውስጥ የሚዘምሩ መላዕክት ብቻ ሳይሆን፣ በቅዱሳን መካከልም ውይይት እንዳለ የሚያስረዳ ነው ብለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ስመራሮ አክለውም፣ “ቅድስት ሥላሴዎች እርስ በእርስ በመካከላቸው እንደሚነጋገሩ ሁሉ፣ የሰማይ ቅዱሳንም እንዲሁ ይነጋገራሉ” ብለዋል። በመሆኑም “ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እንደተመኙት ሁሉ፣ በምድር ላይ ያለችው ቤተክርስቲያን በመልዕክቶቿ አማካይነት ከሕዝቧ ጋር መወያየት የምትፈልግ ከሆነ ፣ በሰማያዊው ቤት የሚትገኝ ቤተክርስቲያንም የራሷን ተነሳሽነት ፣ ምሳሌነት እና  መመዘኛዎቿን ልትናገር ይገባታል ብለዋል።

በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች የሚከታተል ጳጳስዊ ምክር ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ በስብከታቸው ማጠቃለያ ላይ፣ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛን በሰጦታ ለሰጠን እግዚአብሔር ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ምዕመናን ለቅዱሱ አባታችን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጸለይ እንደሚገባ አሳስበዋል። ብዙዎች የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ አስተምሕሮዎች ከቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ሐዋርያዊ አስተምሕሮች ጋር በተጓዳኝነት በመነበብ ቀጣይነት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበውል። 

12 August 2021, 16:48