የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን  

ካርዲናል ፓሮሊን፣ ሰላም የፍትህ እና የቸርነት ውጤት መሆኑን ገለጹ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ለኮሪያ ዓለም አቀፍ የሰላም መድረክ በላኩት መልዕክት፣ ሰላም የፍትህ እና የቸርነት ውጤት መሆኑን በኮሪያ ውስጥ ሰላም እንዲወርድ ቤተክርስቲያን የምትጫወተውን ሚና በገለጹበት ወቅት አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ለመድረኩ በላኩት መልዕክት፣ “ፍትህ የሌላው መብት ሳይረገጥ ተገቢው ክብር እንዲሰጠው የሚያደርግ ሲሆን፣ ቸርነትም የሌሎችን ፍላጎት እንደ ራስ ፍላጎት መቁጠር እንደሚገባ ያሳስበናል” ብለው፣ ይህም በሰዎች መካከል ፍሬያማ አንድነትን እና ወዳጅነትን ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል። በመሆኑም እውነተኛ ሰላም በዓለማችን የሚመጣው ፍትህ በቸርነት እና በፍቅር ሲታገዝ ነው ብለዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በቪዲዮ መገናኛ በኩል አስተያየታቸውን የገለጹት፣ የሁለቱ ኮርያዎችን ውሕደት በማስመልከት በደቡብ ኮሪያ ውስጥ ዓመታዊ ጉባኤያቸውን ከነሐሴ 25-27/2013 ዓ. ም. ድረስ ለሚያካሂዱ፣ ከሃያ አገራት በላይ የተውጣጡ ባለሙያዎች ፣ ተመራማሪዎች እና የመንግሥት ባለስልጣናት ለሚሳተፉበት መድረክ መሆኑ ታውቋል።

“አዲስ ራዕይ ለሁለቱ ኮሪያዎች ግንኙነቶች እና ማህበረሰብ - ለሰላም ፣ ለኢኮኖሚ እና ለሕይወት” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀው ጉባኤ የሚካሄደው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በአውታረ መረብ አማካይነት መሆኑ ታውቋል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ በሁለቱ ኮሪያዎች መልካም ሰላምን ለመፍጠር የቅድስት መንበር የምትጫወተው ሚና ምን እንደሆነ በስፋት በገለጹበት ጽሑፋቸው እንዳስታወቁት፣ የቤተክርስቲያናቸው ሚና በሁለቱ የባሕረ ሰላጤ አገሮች መካከል ሰላምን እና እርቅን ለማምጣት የሚረዱ መርሆዎችን ፣ እሴቶችን እና ሀሳቦችን ከቤተክርስቲያን ባሕል እና ከወንጌል ጋር ባማዛመድ ገንቢ ሃሳቦችን ማቅረብ እንደሆነ አስርድተዋል።

መቀበል ፣ ማራመድ ፣ ማዳመጥ

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ሕዝቦች እና አገራት እንደ ወንድም እና እንደ እህት፣ እንደ እግዚአብሔር ልጆች እርስ በእርስ በመገናኘት ለሰው ልጅ ሕይወት እና ሁለገብ ዕድገት የሚረዱ መንገዶችን በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ አንዱ ሌላውን ተቀብሎ በማስተናገድ፣ ጥረቱ ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ እና በመደማመጥ እንደሆነ አስርድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አንዱ ሌላውን ተቀብሎ ማስተናገድ ማለት መቀራረብ፣ ግልጽነት፣ ትዕግስት እና በሌላው ላይ ሳይፈርዱ ደግነትን መግለጽ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል። የአንድነት ጥረት ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግን አስመልክተው ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ሲናገሩ፣ የሰውን ልጅ ሕይወት ተገንዝቦ ክብርን ካልሰጡለት ሰላም የሰፈነበት ማኅበራዊ ዕድገትን ማምጣት የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል።  

መደማመጥ ያለበት የጋራ ውይይት

የማድመጥ እና የጋራ ውይይት ውድ ጊዜን መስዋዕት ማድረግን የሚጠይቅ መሆኑን የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ መደማመጥ ግጭቶችን የሚያስወግድ ባሕላዊ የእርቅ እና የሰላም መንገድ መሆኑን አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የጋራ ውይይት ሌሎችን በሚገባ ለመረዳት እና ለሚያቀርቡት ሃሳብ አድናቆትን ለመስጠት፣ የሰዎችን ፍላጎት ለማክበር የሚያግዝ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።

ሰላም ፣ ፍትህ እና በጎበት

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ በመጥቀስ፣ ሰላም፣ ጦርነት ባለመኖሩ ወይም በፕለቲካ ተቀናቃኞች መካከል ጥላቻ ባለመኖሩ ብቻ የሚገለጽ አለመሆኑን አስረድተው፣ ሰላም የፍቅር ውጤት እና ፍቅርም ፍትህ ከሚያስገኘው ውጤት በላይ የሆኑ ውጤቶችን የሚያቀዳጅ መሆኑን ገልጸው፣ እውነተኛ ሰላምን በዓለማችን ውስጥ ለማንገሥ ፍትህ በቸርነት መደገፍ አለበት ብለዋል።

ወዳጅነት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ወዳጅነት ማኅበራዊ ይዘት እንዳለው እና ከአንድነት እና ከኅብረት ጋር እርስ በእርስ መደጋገፍ እንዳለባቸው መናገራቸው ይታወሳል። ይህንንም ሲገልጹ፣ ዛሬ የምንገኝበትን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጊዜ በማስታወስ፣ “ሁላችንም በአንድ ጀልባ የተሳፈርን በመሆችን ከመካከላችን ማናችንም ውሃ ውስጥ እንዳሰጥም እርስ በእርስ ተጋግዘን መጓዝ አለብን” ማለታቸው ይታወሳል። “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ የጋራ ውይይት፣ መነጋገር፣ መደማመጥ እና አንዱ ሌላውን መረዳት መቻል ወዳጅነትን ለማሳደግ የሚያስችል መንገድ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ለኮሪያ ዓለም አቀፍ የሰላም መድረክ የላኩትን መልዕክት ሲያጠቃልሉ፣ በዓለማችን ውስጥ እውነተኛ ሰላምን ለማንገሥ ፍትህ በቸርነት የታገዘ መሆን ይኖርበታል ብለው፣ በመሆኑም ሰዎች በመካከላቸው የሚለያይ ነገርን ከመፈልግ ይልቅ አንድነትን የሚያሳድጉ እሴቶችን መፈለግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።                       

31 August 2021, 16:27