የምእመናን ፣ የቤተሰብን እና የሕይወትን ጉዳይ የሚመለከተው ጳጳሳዊ ምክር ቤት የምስረታ በዓል ተከበረ። የምእመናን ፣ የቤተሰብን እና የሕይወትን ጉዳይ የሚመለከተው ጳጳሳዊ ምክር ቤት የምስረታ በዓል ተከበረ። 

የምእመናን ፣ የቤተሰብን እና የሕይወትን ጉዳይ የሚመለከተው ጳጳሳዊ ምክር ቤት የምስረታ በዓል ተከበረ

በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በ 2016 ዓ.ም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የምእመናን ፣ የቤተሰብ እና የሕይወትን ጉዳይ የሚመለከተው ጳጳሳዊ ምክር ቤት 5ኛ አመት የምስረታ በዓል በማክበር ላይ እንደ ሚገኝ ተገለጸ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በነሐሴ 15/2016 ዓ.ም በላቲን ቋንቋ “ Sedula Mater(እናት ሥራ በዝቶባታል) በሚል አርዕስት ይፋ ባደረጉት “ሞቱ ፕሮፕሪዮ” (motu proprio) በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎም (አንድ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ እንደራሴ በመሆኑ፣ በእዚህ በተሰጠው መንፈሳዊ ስልጣን በራሱ ተነሳሽነት ወቅታዊ ሁኔታዎችን ከግምት ባስገባ መልኩ የሚጽፋቸው ሰነዶች፣ የሚያደርጓቸው ሹመቶች፣ ውሳኔዎችን የተመለከቱ ጉዳዮችን ይመለክታል)   ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልእክት አማካኝነት ነበር ቅዱስነታቸው ይህንን ምእመናን ፣ ቤተሰብ እና ሕይወትን የሚመለከት ጳጳሳዊ ምክር ቤት ያቋቋሙት።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ይህንን ምክር ቤት ሲያቋቁሙ ለወጣቶች እና ለቤተሰብ እንክብካቤ መመሪያን በመስጠት ሕይወትን የማስተዋወቅ እና የምእመናንን ሐዋርያዊ ተግባራት ጽ / ቤቱ በከፍተኛ ትኩረት እንዲከታተለው በአደራ መልክ መስጠታቸው ይታወሳል።

የሰነዱ የመክፈቻ መስመር “ቤተክርስቲያን ለዘመናት ሁሉ ፣ መሐሪ እና አዳኝ የሆነው ጌታ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር በመከተል ይህንን ፍቅር በመግለጥ ሁል ጊዜ ለምእመናን ፣ ለቤተሰብ እና ለሕይወት እንክብካቤ እና ከፍተኛ ክብር ትሰጣለች” በማለት ይጀምራል።

ጳጳሳዊ ምክር ቤቱ ከተሰጠው መንፈሳዊ ግዴታ ውስጥ አንዱ የሆነው አሁን እኛ በምንኖርበት ጊዜ ውስጥ  ምዕመናን የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ምስክርነት በመረዳት ከቤተክርስቲያን ጋር እጅ ለእጅ በመተሳሰር ምዕመናን መንፈሳዊ ተግባራቸውን ያከናውኑ ዘንድ ጳጳሳዊ ምክር ቤቱ የራሱን አስተዋጾ የማድረግ ተግባር እና ኃላፊነት ተጥሎበታል።

ብዙ የቤተክርስቲያን ፊቶችን የሚወክል ምክር ቤት ነው

የምእመናን ፣ የቤተሰብ እና የሕይወት ጉዳዮችን እንዲከታተል የተቋቋመው ጳጳሳዊ ምክር ቤት የተቋቋመው የቀድሞዎቹ የሕይወት ጉዳይን እና የምዕመናን ጉዳዮችን ይመለከቱ የነበሩ ጳጳሳዊ ምክርቤቶች እንዲፈርሱ ከተደረገ በኋላ በአዲስ መልክ የተቋቋመ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ነው።

ካርዲናል ኬቪን ፋረል በአሁኑ ጊዜ የዚህ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ዋና አስተዳዳሪ ሆነው እያገለገሉ ሲሆን በአባ አሌክሳንድር አዊ ሜሎ እንዲሁም ምክትል ኃላፊዎች በሆኑት ሊንዳ ግሂሶኒ እና ጋብሪኤላ ጋምቢኖ ድጋፍ ተግባራቸውን እያከናወኑ እንደ ሚገኙ ተዘግቧል፣ ምክር ቤቱ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ካህናት ፣ መነኮሳት እና ምዕመናን ሠራተኞችን አቅፎ የያዘ ነው።

ለምዕመናን እና ለሕይወት ያለንን አክብሮት ማሳደግ

የምእመናን ፣ የቤተሰብ እና የሕይወት ጉዳዮችን እንዲከታተል የተቋቋመው ጳጳሳዊ ምክር ቤት በሕገ ደንቦቹ መሠረት ፣ የጳጳሳዊ ምክር ቤቱ ልዩ ተልእኮ ላይ መሠረቱን ያደረገ ሲሆን የካቶሊክ ምዕመናን በቤተክርስቲያኗ ሕይወት እና ተልእኮ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲሳተፉ ማበረታታት ተቀዳሚ ተግባሩ ነው።

እንዲሁም “በወንዶች እና በሴቶች መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ያላቸውን ልዩነት ፣ አንዱ ለአንዱ እንደ ሚያስፈልግ፣ ተመጋጋቢ መሆናቸውን፣ ተጓዳኝ መሆናቸውን እና ያላቸውን እኩል የሆነ ክብርን በጥልቀት ለማሳየት” የሚሰራ ምክር ቤት ነው።

ሌላው ግብ ሴቶችን እና ቤተሰቦችን “በአስቸጋሪ የእርግዝና ጊዜ ውስጥ የሕይወትን ስጦታ ከፍ አድርገው እንዲንከባከቡ እና ፅንስ ማስወረድን ለመቃወም” የሚረዱ ወይም የሚያግዙ ማህበራትን እና ድርጅቶችን ማስተዋወቅ ፣ እንዲሁም ፅንስ ያስወረዱ ሴቶችን ከገቡበት የአእምሮ ጭንቀት እንዲወጡ የሚረዱ ፕሮግራሞችን ማስቀጠል የምእመናን ፣ የቤተሰብ እና የሕይወት ጉዳዮችን እንዲከታተል የተቋቋመው ጳጳሳዊ ምክር ቤት አንዱ ተልዕኮ ነው።

የምእመናን ፣ የቤተሰብ እና የሕይወት ጉዳዮችን እንዲከታተል የተቋቋመው ጳጳሳዊ ምክር ቤት በተጨማሪም “ኃላፊነት በተሞላው መልኩ ልጆችን መውለድ የሚደግፉ ተነሳሽነቶችን እንዲሁም የሰውን ሕይወት ከፅንስ እስከ ተፈጥሯዊ ሞት ፍፃሜ ደረስ ለመጠበቅ” የሚደረጉትን ተግባራት በከፍተኛ መልኩ በማገዝ እና በማስተባበር ላይ ይገኛል።

ለቤተሰብ የሚደረግ ሐዋርያዊ እንክብካቤ

“በቤተክርስቲያኗ ውስጥ እና በሲቪል ማህበረሰብ ውስጥ መብቱን እና ሀላፊነቱን” በማሳደግ ቤተሰብ ክብሩን እና ደህንነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲኖር “በምስጢረ ተክሊል አማካይነት የተመሰረተ ጋብቻ እንዲበራከት ማድረግ” ደግሞ የምእመናን ፣ የቤተሰብ እና የሕይወት ጉዳዮችን እንዲከታተል የተቋቋመው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ሌላኛው ተልዕኮ ነው።

ይህንን ግብ ለማሳካት አንዱ መንገድ የዓለምን የቤተሰብ ስብሰባ (WMF) ጨምሮ የተለያዩ ጉባኤዎችን እና ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማደረግ ላይ የሚገኘው የምእመናን ፣ የቤተሰብ እና የሕይወት ጉዳዮችን እንዲከታተል የተቋቋመው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ ቀጣዩ የዓለምን የቤተሰብ ስብሰባ (WMF) በኮቪድ በሽታ ወረርሽኝ ምክንያት ከታቀደው ከአንድ ዓመት በኋላ እ.አ.አ በሚቀጥለው አመት ከሰኔ 22-26/2022 ዓ.ም ላይ ለማከናውን ከፍተኛ ጥረት በማደረግ ላይ ይገኛል።

ይህ ከአንድ ዓመት በኋላ እ.አ.አ በሚቀጥለው አመት ከሰኔ 22-26/2022 ዓ.ም ላይ የሚከናወነው የዓለም የቤተሰብ ስብሰባ ለ10ኛ ጊዜ የሚደረግ እንደ ሆነ የተገለጸ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “ሁለገብ እና የተስፋፋ” ብለው የጠሩትን ልዩ ቅርጸት እንደ ሚወስድ ከወዲሁ እየተጠበቀ ይገኛል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ልዩ የሆነውን ክስተት በሚያብራራ የቪዲዮ መልእክት የሮም ከተማ የዓለም የቤተሰብ ስብሰባ ዋና ቦታ ትሆናለች ነገር ግን እያንዳንዱ ሀገረ ስብከት ለቤተሰቦች እና ለማህበረሰቦች አካባቢያዊ ስብሰባዎች የትኩረት ቦታ ይሆናል ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን “በዚህ መንገድ ሁሉም ወደ ሮም ከተማ መምጣት የማይችሉትን ሰዎች እንኳን ተሳታፊ እንዲሆን ማደረግ ይቻላል” ማለታቸው ይታወሳል።

ከሰኔ 22-26/2022 ዓ.ም የሚከናወነው የዓለም የቤተሰብ ስብሰባ “ይህ ጥልቅ ምስጢር ነው” የሚል ርዕስ የተሰጠው ሲሆን ለዚህ የዓለም የቤተሰብ ስብሰባ ይሆን ዘንድ ይፋ የሆነው አርማ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ሰዎች ከጻፈው መልእክቱ 5፡32 ላይ የተወሰደ ሲሆን የስነ -መለኮት ትምህርት ምሁር እና አርቲስት በሆኑ የኢየሱሳዊያን ማሕበር አባል አባት ማርኮ ኢቫን ሩፕኒክ እንደ ተዘጋጀ ተገልጿል።

ስብሰባው በተጨማሪም “በቤተክርስቲያን ውስጥ እና በዓለም ውስጥ የምእመናን ታማኝ ተልእኮ እና እንቅስቃሴ” የማስተዋወቅ ተግባሩን ለመፈፀም እንደ ሚሰራ የምእመናን ፣ የቤተሰብ እና የሕይወት ጉዳዮችን የሚመለከተው ጳጳሳዊ ምክር ቤት አክሎ ገልጿል።

ዝግጅቱን በቫቲካን የቅድስት መንበር የምዕመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት ጉዳዮችን በበላይነት በሚከታተለው ጳጳሳዊ መክር ቤት እና የሮም ሀገረ ስብከት በትብብር የሚዘጋጅ የዓለም የቤተሰብ ስብሰባ ሲሆን በላቲን ቋንቋ “አሞሪስ ላቲሲያ” (የፍቅር ሐሴት) በሚል አርዕስት የዛሬ ስድስት አመት ገደማ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቤተሰብ ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ፍቅር በመግለጽ ይፋ ያደረጉት ጳጳሳዊ መልእክት ስድስተኛ ዓመት የሚዘከርበትን ቀን ምክንያት በማደረግ እና እንዲሁም አሁንም በላቲን ቋንቋ “Gaudete et exsultate” (ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ” በሚል አርዕስት ቅዱስነታቸው ይፋ አድርገው በነበረው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ላይ የተመረኮዙ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደ ሚከናወኑ ከወዲሁ ተገልጿል።

ዐሥረኛው የዓለም የቤተሰብ ስብሰባ “ሁለገብ እና ስፋ ያሉ ቅርጾችን” በመያዝ የተለያዩ ልኬቶችን በመጠቀም ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ቀመሮችን እንደ ሚያካትት ከወዲሁ እየተገለጸ ይገኛል። የሮም ከተማ ዋናው የስብሰባው ማዕከል ቦታ ትሆናለች ፣ ነገር ግን በዓለም አቀፉ የቤተስብ ስብሰባ የቤተክርስቲያን ዝግጅት እያንዳንዱ ሀገረ ስብከት ለራሱ ቤተሰቦች እና ማህበረሰቦች አካባቢያዊ በሆነ ደረጃ ስብሰባዎችን ማደረግ ይችላል። በዓለም ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ቤተሰብ የዚህ ስብሰባ ዋና ተዋናይ ሊሆን ይገባል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የስብሰባውን ያልተለመዱ ባሕሪያትን በተመለከተ እ.አ.አ ባለፈው ሐምሌ 2/2021 ዓ.ም በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት “ወደ ሮም መምጣት የማይችሉትን ጨምሮ ሁሉም ሰው መሳተፍ ይችላል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸው ይታወሳል። ብፁዕ አባታችን እያንዳንዱ ሀገረ ስብከት  ማኅበረሰቦችን በተቻለ መጠን በማንቀሳቀስ የስብሰባውን ጭብጥ መሠረት በማድረግ ተነሳሽነቶችን እንዲያቅዱ አሳስበዋል - “የቤተሰብ ፍቅር - ጥሪ እና የቅድስና ጎዳና” እንደ ሆነም አክለው መግለጻቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ አክለው እንደገለጹት “ይህንን ከቤተሰቦች ጋር በማደራጀት ተለዋዋጭ ፣ ንቁ እና የፈጠራ ችሎታ እንዲኖራችሁ እጠይቃለሁ” ማለታቸውም የሚታወስ ሲሆን “ይህ ከትዳር አጋሮች ፣ ከቤተሰቦች እና ከቀሳውስት ጋር ለቤተሰብ አገልግሎት በጋለ ስሜት ራሳችንን የምናቀርብበት አስደናቂ አጋጣሚ ነው” በማለት መናገራቸውም ይታወሳል።

20 August 2021, 13:48