በቺሊ የሚገኙ የሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ማኅበራት በቺሊ የሚገኙ የሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ማኅበራት 

ካርዲናል ታርክሰን፣ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች የለውጥ ተዋናይ መሆናቸውን ገለጹ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ሐላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ ለአራተኛ ጊዜ ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ስብሰባ በላኩት መልዕክታቸው፣ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች በማኅበራዊ ሕይወት ለውጥን ለማምጣት የሚያበረክቱት አስተዋዖ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ የልዩነት እና የማግለል ባሕልን በመቃወም በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ሰብዓዊ መብትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ማኅበራዊ ዕድገት የሚረጋገጠው ሕዝቦች በሰላም አብረው ሲኖሩ፣ ሥነ-ምሕዳራዊ ሕጎችን በማክበር ከፍጥረት ጋር መልካም ግንኙነት ሲኖር፣ የሕዝቦች ሰብዓዊ መብቶች ተከብረው ሁሉም ለጋራ ጥቅም በአንድነት ሲቆሙ እንደሆነ አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን ይህን መልዕክታቸውን በአውታረ መረብ አማካይነት ያስተላለፉት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለማችን ከፍተኛ ጉዳት ባስከተለበት ወቅት ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች በመጭው መስከረም ወር ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ተገናኝተው መልዕክታቸውን ለመቀበል በሚዘጋጁበት ወቅት መሆኑን ታውቋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማኅበራዊ ሕይወት ላይ ያስከተለውን ቀውስ በማስታወስ ሃሳባቸውን ያካፈሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ ወረርሽኙ በችርቻሮ ንግድ ላይ በተሰማሩት፣ በጎዳና ተዳዳሪዎች፣ በእጅ ሥራ ባለሞያዎች፣ በዓሳ አጥማጆች፣ በአርሶ አደሮች፣ በግንበኞች፣ በማዕድን ቆፋሪዎች፣ በሌሎች በርካታ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ ያስከተለውን ከፍተኛ ችግር አስታውሰዋል።

ድሆች ኢ-ፍትሃዊነትን በመዋጋት ላይ ናቸው

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ያዘጋጀው የአውታረ መረብ ላይ ስብሰባ ዋና ዓላማ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት በሦስት ዙር  በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ ያስተላለፉትን መልዕክቶች በማስታወስ፣ ከማኅበራዊ ሕይወት የተገለሉት እና ሰብዓዊ መብታቸውን የተቀሙ ሰዎች ላይ የሚታየውን ስጋት እና ጭንቀት አጉልቶ ለማሳየት መሆኑ ታውቋል። በተለይም የእርሻ መሬት፣ መጠለያ እና የሥራ ዕድል የሰው ልጅን ማኅበራዊ ፍትህ ለማረጋገጥ መሠረታዊ ርዕሠ ጉዳዮች እንደሆኑ መናገራቸው ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን ስብሰባውን ከብራዚል፣ ከሕንድ እና ከስፔን ሆነው የተካፈሉ ሰዎች ምስክርነት በመጥቀስ፣ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ለሚገኙ የማኅበራዊ እንቅስቃሴ አባላት ባቀረቡት መልዕክት፣ በፍትህ እጦት ምክንያት በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለማስታወስ የልብ መለወጥ ሊኖር እንደሚገባ አሳስበው፣ የኤኮኖሚ ሥርዓትን በአስቸኳይ ለሕዝብ ጥቅም የቆመ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ድሆች የሚሰቃዩት በፍትህ ማጣት ብቻ ሳይሆን ፍትህን ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስታውሰዋል። የሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች መስሠረታዊ ተግባር ፍትህን በማጣት ለሚሰቃዩት ፍትህን እንዲኖራቸው ማድረግ ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ ማኅበራዊ ኤኮኖሚ ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

ታሪክን መሥራት

ወደ ፊት የሚጠብቁ ጥረቶች ማኅበራዊ ትብብርን የሚጠይቁ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን ጥረቶቹ መጀመር ያለባቸው በማኅበረሰብ መካከል ተረስቶ ከቆየው ሕብረተሰብ መሆን እንዳለበት አስታውሰው ይህን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ በሰዎች መካከል ጥልቅ የሆነ የአንድነት እና የመተባበር ባሕል ሊኖር ይገባል ብለው፣ የሕዝቦች ሰላማዊ ግንኙነት ወደ እኩልነት፣ ወደ ፍትሕ፣ ወደ ማኅበራዊ አንድነት እና ወደ ሰላም ለሚደረግ ጉዞ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። ድህነትን ለማስወገድ በሚደረግ ጥረት ታሪክን በመሥራት ላይ እንደሆኑ ገልጸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው እንደተናገሩት ሁሉ ለሚደረጉት ጥረቶች መልካም ውጤት ማምጣት የሚቻለው በጥበብ እና በድፍረት እንጂ በምኞት እና በአመጽ አለመሆኑን አስረድተዋል።

የግድየለሽነት ባሕል ማስወገድ ያስፈልጋል

በማኅበረሰብ መካከል የሚታይ የኑሮ አለመመጣጠንን ለማስወገድ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ወደ አንድነት እና እኩልነት መድረስ እንደሚቻል ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያስተላለፉትን መልዕክት ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ በየአገራቱ ለሚገኙ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች የበኩላቸውን ድጋፍ የሚያደርጉ የአገር ውስጥ፣ የአህጉራት እና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ መተባብር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በእነዚህ ድርጅቶች አማካይነት የማኅበራዊ ለውጥ ሂደቶችን ማጠንከር እንደሚያስፈልግ፣ ሰብዓዊ ክብርን የሚያስጠብቁ የሥራ ዕድሎችን፣ ትርፍን ብቻ መሠረት ከሚያደርግ ኤኮኖሚ ይልቅ ማኅበራዊ ኤኮኖሚን መሠረት በማድረግ አድነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ የግድየለሽነት ባሕል በመዋጋት የራስን ሰብዓዊ ክብር ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ለማስከበር ጥርት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። 

12 July 2021, 16:22