ፈልግ

የቨነዙዌላ ስደተኞች በመጠለያቸው አካባቢ የቨነዙዌላ ስደተኞች በመጠለያቸው አካባቢ 

አቡነ ብሩኖ ማሪ ፣ የስደተኞችን ችግር እየተጋሩ አብሮ መጓዝ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ብሩኖ ማሪ ዱፌ፣ ስደተኞችን ማክበር፣ ችግራቸውን እየተጋሩ በኅብረት መጓዝ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ። አቡነ ብሩኖ ማሪ ዱፌ ይህን ያሳሰቡት ከዚህ በፊት የተጀመረው “አብረን እንጓዝ” የተሰኘ መርሃ ግብር ቀጣይነት ለማስታወቅ ባስተላለፉት መዕክታቸው አማካይነት ነው። መርሃ ግብሩ ለሰደተኞች መልካም ተስፋን የሰነቀ እና ሳይቋረጥ ረጅም መንገድ የሚጓዝ የቅስቀሳ መርሃ ግብር መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እያንዳንዱ ስደተኛ ከበስተኋላው ሕመም ያለበት የመከራ ጉዞ የሚጠብቀው፣ ስብዕናው ታውቆለት መልካም ተቀባይነትን ተስፋ የሚያደርግ ነው” በማለት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ብሩኖ ማሪ ዱፌ ገልጸዋል። በካቶሊካዊ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅት አስተባባሪነት “አብረን እንጓዝ” በሚል መሪ ቃል ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያስጀመሩት የቅስቀሳ መርሃ ግብር መደምደሚያን ምክንያት በማድረግ ትናንት ሰኔ 9/2013 ዓ. ም ብጹዕ አቡነ ብሩኖ ማሪ ከሌሎች የሥራ ተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን በቫቲካን ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸው ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዕለቱ በተከበረው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ ሰዎች ተሰጥዎቻቸውን በሞያዎቻቸው በኩል እንዲያሳድጉ ዕድል ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ እና በዚህም ሰብዓዊ ክብራቸውን ማስጠበቅ መዘንጋት የለብንም ማለታቸው ይታወሳል።

“አብረን እንጓዝ” በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የቅስቀሳ መርሃ ግብር፣ ስደተኞች ሰብዓዊ ክብርን የተለበሱ፣ ጥበብ እና ተሰጥኦ ያላቸው እና የተሻለ ሕይወት ተስፋን ሰንቀው የሚጓዙ መሆናቸውን ብዙዎች ሰዎች እንዲገነዘቡ ማድረጉን ብጹዕ አቡነ ብሩኖ ማሪ ዱፌ አስረድተው፣ አብሮ መጓዝ ማለት የስደተኞችን ተስፋ መጋራት፣ ስደተኞችን ማግኘት፣ በእንግድነት እርስ በእርስ መቀባበል እና በስደተኛው ልብ ውስጥ ያለውን መልዕክት መጋራት ማለት መሆኑን ብጹዕ አቡነ ብሩኖ ማሪ ዱፌ ገልጸዋል። በዚህም ስለ ስደተኞች ያለን ግንዛቤ ተለውጦ መልካም ተስፋ ያለበት የጋራ ታሪክ አብሮ ለመኖር የሚያስችል፣ ልዩነትን አስወግዶ የጋራ ጥቅም የሚገኝበት ማኅበራዊ ሕይወት አብሮ ለመገንባት የሚያስችል መንገድ መሆኑን አስረድተዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን መልዕክታቸው፣ ስደተኞችን በክብር ተቀብሎ ማስተናገድ፣ ከአደጋ እና ጉዳት መከላከል፣ ከደረሱበት አካባቢ ማኅበረሰብ ጋር አብረው በሰላም እና በፍቅር የሚኖሩበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል ማለታቸውን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ብሩኖ ማሪ ዱፌ፣ ማወቅ ያለብን ስደተኞችን ብቻ ሳይሆን የመጡበት አገር፣ ያሳለፉትን የአመጽ፣ የጦርነት እና  የድህነት ሕይወትንም ጭምር መገንዘብ መሆኑን ገልጸው፣ የአገራቸውን ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታን ለይቶ ማወቅ እና ከመንግሥታቱ ጋር መገናኘት፣ ሰዎች ከመሰደድ ይልቅ ምርጫቸው ከሆነ በሚኖሩበት አካባቢ ዕርዳታን የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ አቡነ ብሩኖ ማሪ ዱፌ የሶርያ እና የኢራቅ ስደተኞችን በማስታወስ እንደተናገሩት፣ የእነዚህ አገሮች እና የወጣቶቻቸውን የወደ ፊት ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል ብለን በማሰብ ማገዝ እና መተባበር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ሌሎች ሐይማኖቶች አንድ ላይ የጋራ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

በካቶሊካዊ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅት አስተባባሪነት “አብረን እንጓዝ” በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የቅስቀሳ መርሃ ግብር ሥራውን የፈጸመ ቢሆንም ከስደተኞች ጋር መልካም ተስፋን እና ሰላምን ለማግኘት የሚደረግ ጉዞ ቀጣይነት እንዲኖረው ብጹዕ አቡነ ብሩኖ ማሪ ዱፌ አሳስበዋል። አክለውም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ በአውሮፓ የሚኖረን ተስፋ፣ ከስደተኞች ጋር ወዳጅነትን በመፍጠር በወንዳማማችነት እና በእህትማማችነት አብሮ የመኖር ተስፋ መሆኑን ገልጸዋል። የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክትም ስደተኞችን ተቀብሎ በክብር ማስተናገድ፣ የሚኖሩበትን አካባቢ እና የሥራ ዕድሎችን በማመቻቸት ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር ሰብዓዊ ክብራቸውን በማስጠበቅ አብሮ መኖር መሆኑን ብጹዕ አቡነ ብሩኖ ማሪ አስረድተው፣ “አብረን እንጓዝ” በሚል መሪ ቃል የተጀመረውን የቅስቀሳ መርሃ ግብር ለማስቀጠል የስደተኞችን ተስፋ መጋራት ያስፈልጋል ብለዋል።   

17 June 2021, 16:15