ፈልግ

በሜክሲኮ የሚገኝ የጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ በሜክሲኮ የሚገኝ የጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ 

ካርዲናል ፓሮሊን፣ ቤተክርስቲያን ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጎጂዎች ቅርብ መሆኗን ገለጹ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በሜክሲኮ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ቤተክርስቲያን በኮቪድ-19 ለተጎዱት የሕክምና አገልግሎቶችን በማቅረብ፣ በማጽናናት እና ችግራቸውን በመካፈል ከጎናቸው መሆኑን ገለጽ። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ይህን የተናገሩት በሜክሲኮ በሚገኝ የጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ባቀረቡት ስብከት፣ ማንኛውንም ዓይነት ተስፋ መቁረጥ፣ ፍርሃት እና መደናገጥን የሚያሸንፍ ጠንካራ እና ጽኑ እምነት ሊኖረን ይገባል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓለማችንን ክፉኛ የጎዳው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጤናችንን በማቃወስ፣ እንቅስቃሴያችንን በመከልከል እና አቅመ ደካማነታችንን ግልጽ አድርጎ በማሳየት በርካታ ቤተሰቦችን ሐዘን ውስጥ በመክተት ተስፋቸውን እንዲቆርጡ ማድረጉን አስታውሰዋል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን እሑድ ሰኔ 13/2013 ዓ. ም በሜክስኮ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ውስጥ ባቀረቡት ጸሎት፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተስፋፋው የሕዝቦች ስቃይ እንዲያበቃ፣ ተስፋቸውም እውን እንዲሆን በማለት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕርዳታን ለምነዋል።

ዓለማች ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በሌሎች በርካታ ችግሮች ውስጥ በሚገኝበት በዚህ ዘመን ቤተክርስቲያን እንደ ቤተሰብ ከእያንዳንዱ ማኅበረሰብ ጎን በመቆም፣ መከራቸውን በመጋራት፣ በጸሎት በመተባበር፣ በስጋ ብቻ ሳይሆን በመንፈስም በጥልቅ የተጎዱትን ስታጽናና መቆየቷን አስታውሰዋል። ዛሬ ቢሆን ወደ እግዚአብሔር የምናቀርበውን ልመናችንን በማደስ፣ በማር. 4፡ 35 – 41 ላይ እንደተጠቀሰው፣ ማዕበሉ እና አውሎ ነፋሱ ጀልባዋን በመታት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ፈርተው ወደ ኢየሱስ በጮሁ ጊዜ ከጥፋት እንዳዳናቸው ሁሉ፣ እኛም ዛሬ በጭንቃን ጊዜ እግዚአብሔር እንዳይተወን፣ ዕርዳታውን እና ፈውሱን እንዲልክልን በማለት ጩሄታችንን ወደ እርሱ እናቀርባለን ብለዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በስብከታቸው እግዚአብሔር በተመሰገኑ መልካም ሰዎች አማካይነት አለኝታነቱ እየገለጸ መሆኑን ተናግረው፣ እነዚህ ሰዎች በቸርነታቸው አማካይነት በስጋም ሆነ በመንፈስ አገልግሎታቸውን ማበርከታቸውን አስረድተው ከዚህ በተጨማሪም በጸሎታቸውም አግዘውናል ብለዋል። በዚህ ከባድ ጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር ከጎናችን ሆኖ ጸሎታችንን በማድመጥ፣ በመከራ የተጎዳውን ማኅበረሰባችንን እና መላው ዓለማችንን በኅብረት መልሰን እንድንገነባ ኃይላችን እና ጥበባችን እየሆነልን ይገኛል ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በሜክሲኮ ጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ተገኝተው፣ የደቀ መዛሙርት ጀልባ በማዕበል እና በአውሎ ነፋስ መመታቱን በማሳታወስ ባቀረቡት ጸሎታቸው፣ እንደ ሌሎች የላቲን አሜሪካ አገራት፣ ሜክሲኮም ለበርካታ ዓመታት ያህል በማኅበራዊ ሕይወት አለመስተካከል፣ በድህነት፣ በአመጽ፣ በተቀናጀ ወንጀል፣ በፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ሐይማኖታዊ ልዩነቶች መጎዳቷን ገልጸው የእመቤታችንን ዕርዳታ ተማጽነዋል። ከዚህ ችግር ለመውጣት የሜክሲኮ ሕዝብ በመተባበር፣ ከቀደምት አባቶቹ የወረሰውን የማንነት እሴት እና ታሪክ መዘንጋት የለበትም ብለዋል። እንደ ክርስቲያናዊ ቤተሰብም በላቲን አሜሪካ ውስጥ ለሜክሲኮ መልካም ባሕሎችን የሰጠን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ስጦታውን ሳያቋርጥ እንዲሰጠን መለመን እንደሚያስፈልግ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አሳስበዋል።

ተስፋን በመሰነቅ በሜክሲኮ የተሻሉ ዕድሎች እየተከፈቱ መሆኑን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ በሜክሲኮ እርቅ የሚወርድበት፣ በሕዝቦቿም መካከል ሰላማዊ እና በፍቅር አብሮ መኖር የሚቻልበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን ተናግረዋል። ይህን ለማሳካት ምዕመናን እምነቱን እንዲያሳድግ አደራ ብለዋል። አክለውም ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ ደቀ መዛሙርቱ እምነት እንዲኖራቸው መጠየቁን አስታውሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ዛሬም ቢሆን ማንኛውንም ዓይነት ተስፋ መቁረጥ፣ ፍርሃት እና መደናገጥን የሚያሸንፍ ጠንካራ እና ጽኑ እምነት እንዲኖረን ይጠይቀል ብለዋል። እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሙሉ እምነት እንዲኖር፣ መልካም ምስክርነትን በመስጠት የግል እና ማህበራዊ ሕይወትን የሚለውጥ ጠንካራ እምነት እንዲኖር አደራ ብለውዋል። አንዳንድ ጊዜ ዕለታዊ ሕይወታችን ከእምነታችን ጋር አለመመሳሰሉ ክርስቲያኖች በዓለም ውስጥ ለሚሰጡት ምስክርነት እንቅፋት መሆኑን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በሜክሲኮ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት አስረድተዋል።   

22 June 2021, 16:46