ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን 

ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን ለሥነ ምሕዳር ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግለት አሳሰቡ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ሐላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን ሰባት ዓመት የሚወስድ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የተግባር መርሃ ግብርን ባስተዋወቁበት ጋዜጣዊ መግለጫቸው፣ ለሥነ ምሕዳር የሚሰጥ ጥበቃ እና እንክብካቤ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳሰበዋል። የተግባር መርሃ ግብሩ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችን፣ ገዳማዊያትን እና ገዳማዊያንን፣ የንግድ ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችን እና ሆስፒታሎችን የሚያካትት መሆኑንም አስረተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓለማችን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ባለበት እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንም ክፉኛ እየተጎዳች ባለችበት ባሁኑ ወቅት፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች እና ወጣቶች ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤ እና ጥበቃ እንዲደርረያስከተልን እንገኛለን በማለት ማሳሰባቸው ታውቋል። በዚህ ምክንያት ቅድስት መንበር ለሥነ ምሕዳር ሊሰጥ የሚገባው የተግባር መርሃ ግብር ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኗ ታውቋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ውዳሴ ላንተ ይሁን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አምስተኛ ዓመት መገባደጃን ምክንያት በማድረግ እ.አ.አ ግንቦት 24/2020 ዓ. ም በወጣው መርሃ ግብር በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት በተለያዩ አገራት የሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶችን፣ ቁምስናዎችን፣ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ማኅበራትን፣ የጤና እና የንግድ ተቋማትን፣ የእርሻ ድርጅቶችን፣ የትምህርት ተቋማትን፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያትን ያሳተፈ፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከጥፋት ለመከላከል ያለመ ዘላቂ የኑሮ ልማድ በተግባር እንዲውል የሚጠይቅ ማሳሰቢያ ይፋ መደረጉ ታውቋል።

በጋራ መኖሪያ ምድራችን ውስጥ የሚኖር ሰብዓዊ ቤተሰብ ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጦ እንደሚገኝ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ ጊዜ ሳይሰጠው የተጋረጠብንን አደጋ በጋራ መከላከል እንደሚያስፈልግ በቫቲካን የዜና አገልግሎት ባኩል ጋዜጣዊ መግለጫ አሳስበዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሄደው የከባቢ አየር ሙቀትን መገደብ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀው፣ ይህ ካልተደረገ በሰው እና በተፈጥሮ ላይ የሚደርስ አደጋ ከፍተኛ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለግላስጎው ጉባኤ ተጋብዘዋል

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቪዲዮ አማካይነት ባስተላለፉት መልዕክት፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከጥፋት ለማትረፍ የጋራ ጥረትን ማድረግ እና ለመጭው ትውልድ ፍትሃዊነት እና ዘላቂነት ያለውን የመኖሪያ ሥፍራን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ማስሰባቸው ይታወሳል። በዚህ አሳሳቢ ወቅት የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ድምጽ ተደማጭነት ያለው መሆኑን በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ሐላፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን አስረድተው፣ በሚቀጥለው ዓመት ኅዳር ወር ላይ በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ ሊካሄድ በታቀደው “Cop26” በተባለ ጉባኤ ላይ ቅዱስነታቸው እንዲገኙ ግብዣ የተላከላቸው መሆኑን አስታውቀዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በጉባኤው ላይ መገኘት ለጉባኤው ተካፋዮች እጅግ ውሳኝ እና ጠቃሚ እንደሚሆን ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን ገልጸው፣ የተለያዩ አገራት መንግሥታት ሥነ-ምሕዳራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን በቫቲካን የዜና አገልግሎት በኩል አስረድተዋል። እ. አ. አ በ2015 ዓ. ም በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ከተካሄደው የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ ወዲህ አገራት ለተፈጥሮ የሚያደርጉትን እንክብካቤ እና ጥበቃ ማጠናከራቸውን ብጹዕ ካዲናል ታርክሰን ገልጸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በውዳሴ ላንተ ይሁን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው በአንቀጽ ቁ. 19 ላይ፣ መረጃዎችን መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን የድሆችን ጭንቀት እና መከራን መጋራት ያስፈልጋል ማለታቸውን አስታውሰዋል።

በመስፋፋት ላይ የሚገኘውን በረሃማነት መቀነስ

የተሳሳተ የኑሮ ወገን ማስወገድ እንደሚገባ ያሳሰቡት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ አዳዲስ የኑሮ ሥርዓቶችን በማግኘት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ለተግባራዊነቱ እያንዳንዱ ሰው የግል ሚናውን ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቅበታል ብለው፣ በዓለማችን ውስጥ በሰዎች ላይ የሚደርስ ስቃይ ማብቃት እንዳለበት ተናግረዋል። በባንግላዲሽ ውስጥ ቤተክርስቲያን በዓመት 700 ሺህ የዛፍ ችግኞችን መትከሏን ገልጸው፣ ቪቪያን ሃር የተባለች ወጣት እየሰፋ የሚሄደውን የሰሃራ በረሃን ለመግታት የሚያግዝ አንድ ሚሊዮን ዶላር በዕርዳታ መለገሷን ብጹዕነታቸው አስታውሰዋል።

የዓለምን ተጨባጭ ሁኔታ የሚገልጽ መጽሐፍ

የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ዓመትን ለማክበር በርካታ የተግባር ውጥኖች መጀመራቸውን ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን አስታውቀው ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መቋረጣቸውን ገልጸዋል። የ “‘ውዳሴ ላንተ ይሁን’ ዓመት በርካታ አመርቂ ውጤቶችን እና ልምዶችን እንድንመለከት አድርጎናል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ በአምስቱም አህጉራት የሚኖሩ ሰዎች ልምድ የተካተተበት መጽሐፍ በሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤታቸው በኩል መታተሙን ገልጸዋል።

በሰባት ዓመት ውስጥ ተግባራዊ የሚሆኑ ሰባት ዓላማዎች

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የሥነ ምሕዳር እና ተፈጥሮ እንክብካቤ መምሪያ ተጠሪ የሆኑት ክቡር አባ ይስሐቅ ኩሪታዳም፣ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሰባት ዓመት የተግባር መርሃ ግብር የሚካሄድበትን መንገድ ሲገልጹ፣ የመጀመሪያው ዓመት በሥራ ላይ የሚሰማሩ ማኅበራት ተዋቅረው መረጃዎችን የሚለዋወጡበት፣ ጥናት የሚያደርጉበት እና የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” መመሪያዎችን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ሂደት መሆኑን አስረድተዋል።

የወጣቶች ድምጽ

በካቶሊክ ቤተክርስቲያ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ የሚከታተል ተቋም ተወካይ የሆኑት ካሮሊና ቢያንኪ በበኩላቸው፣ በ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሰባት ዓመት የተግባር መርሃ ግብር በመከተል የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከጥፋት ለማዳን ጥረት የሚያደርጉት አዛውንት ብቻ ሳይሆኑ ወጣቱ ትውልድም መሳተፍ እንደሚገባ ገልጸው፣ አስቸኳይ ተግባር በመሆኑ ቀጣዩ ሕይወት ለሁሉም መልካም እንዲሆን፣ ለሥነ ምሕዳር የሚሰጠው ጥበቃ እና እንክብካቤ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።                  

26 May 2021, 14:26