በሀገረ ስብከት ደረጃ የሚከበረው ብሔራዊ የወጣቶች ፌስቲቫል ሐዋርያዊ መርሃ ግብር ይፋ በሆነበት ወቅት በሀገረ ስብከት ደረጃ የሚከበረው ብሔራዊ የወጣቶች ፌስቲቫል ሐዋርያዊ መርሃ ግብር ይፋ በሆነበት ወቅት  

የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ከወጣቶች ጋር በኅብረት መከናወን እንዳለበት ተጠቆመ

ግንቦት 10/2013 ዓ. ም የቀረበው እና በየሀገረ ስብከቱ በሚገኙ ቁምስናዎች የሚከበሩ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ሐዋርያዊ መርሃ ግብር የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ከወጣቶች ጋር በኅብረት የሚከናወን መሆን እንዳለበት አስታወቀ። ማስታወቂያው በማከልም ሐዋርያዊ መርሃ ግብሩ በየዓመቱ ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፈስቲቫል ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው መልካም ወቅት መሆኑንም አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በወጣቶች ላይ እምነትን በመጣል፣ ዛሬም ሆነ ነገ ለሚቀርበው የቅዱስ ወንጌል ምስክርነት ዕድልን መስጠት ቤተክርስቲያን በዛሬው ዘመን እንደ ትልቅ እሴት የምትመለከው ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል። ግንቦት 10/2013 ዓ. ም ከቫቲካን የወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ በየሀገረ ስብከቶች የሚከበሩ ዓመታዊ የወጣቶች ፌስቲቫልን በማስመልከት እንደገለጸው በየሦስት ዓመታት ከሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ጎን ለጎን የተለያዩ ዝግጅቶችን በማቅረብ በድምቀት ሊከበር ኡየሚችል መሆኑን አስረድቷል። ከ35 ዓመታት በፊት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ያስጀመሩት ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ከእርሳቸው ቀጥለው በመጡት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እና አሁን በሐዋርያዊ መንበር በሚገኙት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ድጋፍን በማግኘት፣ የዓለም ወጣቶች የእምነታቸውን ልምድ በተግባር እና በጋራ ለመኖር ዕድልን ያገኙበት ብቻ ሳይሆን ጥሪያቸውን ተገንዝበው ሕያው የሚያደርጉበት መሆኑ ተገልጿል።

ፌስቲቫሉ ብዙዎች ወደ ጸጋ የሚሸጋገሩበት ነው

በየሀገረ ስብከቱ የሚከበረው የወጣቶች ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል ሐዋርያዊ መርሃ ግብር እንዲዘጋጅ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልካም ፈቃድ መሆኑ ሲነገር፣ ይህ ታላቅ የወጣቶች በዓል ከዚህ በፊት እሑድ ዕለት ከሚከበርበት ከሆሳዕና ክብረ በዓለ ወደ እሑድ የክርስቶስ ንጉሥ በዓል ዕለት እንዲዛወር ያደረጉትም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መሆናቸውን በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አባ አሌሳንደር አዊ ሚሎ አስታውቀዋል።

የወጣቶች ሐዋርያዊ መርሃ ግብሩ በመሪ ካህናት በኩል ለሚቀርቡት ሐዋርያዊ አገልግሎቶች ትልቅ እገዛ እንደሚሰጥ እና ወጣቶች በየቁምስናዎቻቸው ለሚኖሯቸው መንፈሳዊ ሕይወት ልምድም አስተዋጽኦን የሚያደግላቸው መሆኑ ተገልጿል። ከ35 ዓመታት በፊት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ያስጀመሩት ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫሉ ለብዙ ወጣቶች ወደ ጸጋ በረከት የሚሸጋገሩበት ድልድይ መሆኑ ተገልጿል። ባለፉት ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ዓመታት ውስጥ በርካታ የሕይወት ለውጦች እና ጥሪዎች መገኘታቸውን ክቡር አባ አሌሳንደር ገልጸዋል። ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫሉ በርካታ ወጣቶች ለደካማ እምነታቸው ብርታትን ያገኙበት የቤተክርስቲያን ጸጋ መሆኑን የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ መናገራቸው ሲታወስ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስም እንደዚሁ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ለመላዋ ቤተክርስቲያን የወንጌል ተልዕኮ ጉልበትን የጨመረ በተለይም ወጣቶችን ያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።            

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አስተያየታቸውን እንደገለጹት ሁሉ፣ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ለመላው ክርስቲያን ማኅበረሰብ ትልቅ ስጦታመሆኑን በጳጳስዊ ምክር ቤት የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ተጠሪ የሆኑት ክቡር አባ ዮዋዎ ቻጋስ ገልጸው፣ በሀገረ ስብከት ደረጃ የሚከበረው ብሔራዊ የወጣቶች ፌስቲቫል እሑድ ዕለት በሚከበረው የክርስቶስ ንጉሥ በዓል ዕለት መሆኑ ተመራጭ መሆኑን ገልጸዋል።  

በወጣቶች ላይ እምነትን በመጣል ዋና ተዋናይ ማድረግ ያስፈልጋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለወጣቶች ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክት፣ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ለወጣቶች መንፈሳዊ አቅጣጫ ጠቋሚ ነው ብለው፣ አክለውም በወጣቶች ላይ እምነትን በመጣል በወንጌል ምስክርነት ዋና ተዋናይ ማድረግ ያስፈልጋል ማለታቸው ይታወሳል። በወጣቶች ላይ እምነት በሚጣልበት ጊዜ ውጤት ይኖረዋል ያሉት፣ በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተወካይ መሆናቸው ታውቋል።

ፌስቲቫሉ የአገልግሎት ጥሪ ምንጭ ነው

በሮም ከተማ ቀኖናዊ ሥነ-መለኮት ትምህርት ተከታታይ የዘርዓ ክህነት ተማሪ ፌርናንዶ አጉስቶ ዲኒስ፣ በሀገረ ስብከት ደረጃ የሚከበረው የወጣቶች ፌስቲቫል ወጣቶችን በማሳተፍ ለተለያዩ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ጥሪ ያዘጋጇቸው መሆኑን አስረድቷል። ክርስትያናዊ ሕይወቱን በቅርብ የተከታተሉት ሰዎች ድጋፍ የዘርዓ ክህነት ተማሪ እንዲሆን ያገዘው መሆኑን በሮም ቀኖናዊ ሥነ-መለኮት ተማሪ የሆነው ፌርናንዶ አጉስቶ ዲኒስ የግል ሕይወቱን መሠረት በማድረግ አስረድቷል።

በመሆኑም ቤተክርስቲያን ለወጣቶች በምትሰጠው ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ ትኩረት በማድረግ፣ ዘወትር በመጸለይ፣ በአገልግሎት ላይ በማሳተፍ፣ ኢየሱስም እንደሚወዳቸው እና የቤተክርስቲያን ውድ ልጆች መሆናቸውን መናገር እንደሚያስፈልግ የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት መርሃ ግብሩ አመልክቷል።

20 May 2021, 14:46