የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣  

ካርዲናል ፓሮሊን፣ ቤተክርስቲያን ወንጌል ለመመስከር መተባበር እንዳለባት አሳሰቡ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ከስፔን አውታረ መረብ ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ መልልስ፣ ከክህነት ጥሪያቸው አንስቶ እስከ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ድረስ ያላቸው የሐዋርያዊ አገልግሎት ግንኙነት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚታዩ ልዩነቶች እና በቻይና ስለምትገኝ ቤተ ክርስቲያን በማንሳት ሰፋ ያለ ውይይት አካሂደዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“አንድነትን የሚያሳድጉ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን በማቅረብ ላይ እንገኛለ” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን የቤተ ክርስቲያን እና የሐይማኖት ነጻነትን እንዲሁም የዓለማችንን ሰላም ለማስከበር ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረው፣ በሕዝቦች መካከል ሰላም እንዲነግሥ ቤተ ክርስቲያን የምታደርገው ከፍተኛ ጥረት የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲ አቋም መሆኑን “COPE” ከተሰኘ የስፔን አውታረ መረብ ሬዲዮ ዳይሬክተር ከሆኑት ከአቶ ሆሴ ሉዊስ ሬስታን ጋር ባደረጉት ቃለ መልልስ ገልጸዋል።

ዘርፈ ብዙ አቅጣጫዎችን የዳሰሰው የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ የብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ቃለ ምልልስ፣ የጽሕፈት ቤታቸው ሚና ከር. ሊ. ጳጳሳት ጋር በመተባበር በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ ተሃድሶን ማምጣት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማቃለል የሚያግዙ መንገዶችን ፈልጎ ማግኘት፣ በቻይና ያለች ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የምትገኝበትን ሁኔታ መከታተል፣ ቅዱስነታቸው ወደ ኢራቅ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ፍሬያማ እንዲሆን መንገድ ማመቻቸት እና በአውሮፓ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮን መከታተል መሆኑን ገልጸዋል።

በቅድስት መንበር እና በየአገራቱ ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ትስስርን ማጠናከር

በመላው ዓለም የሚትገኝ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሕይወት በሚገባ የሚያውቁት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ስለ ክህነት ጥሪያቸው ሲናገሩ፣ ር. ሊ. ጳጳሳትን ማገልገል የሚያስችላቸው ዕድል ከአርባ ዓመታት በፊት የተሰጣቸው መሆኑን አስታውሰዋል። መሠረታዊው ጥሪያቸው ክህነታዊ ገልግሎት መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ በዚህ ጥሪ አማካይነት ቤተክርስቲያንን ለማገልገል መጠራታቸውን አስረድተው፣ የክህነት አገልግሎትን የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ መንገዶች መኖራቸውን ገልጸው ከእነዚህም መካከል አንዱ የቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት መሆኑን አስረድተዋል። የክህነት ሕይወት እና የቤተ ክርስቲያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚገለጡባቸው የተለያዩ መንገዶች መኖራቸውን የገለጹት ብጹዕ  ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በእነዚህ ሁለት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች መካከል መልካም ግንኙነቶች መኖራቸውን አስረድተው፣ በተለይም ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ወዲህ የቅድስት መንበር እንደራሴ ተግባር በቅድስት መንበር እና በየአገራቱ በሚገኙ ቤተክርስቲያናት መካከል ያለውን ሐዋርያዊ ግንኙነት ማሳደግ መሆኑን አስረድተዋል።

የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤቶችን ማሻሻል

“ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያካሄዱት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቶች ተሃድሶ ቢገባደድም የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ተግባር አንድ ነው” ያሉት ካርዲናል ፓሮሊን፣ “Praedicate Evangelium” ወይም “ወንጌልን ስበኩ” በሚል ርዕስ ለመጀመሪያ ጊዜ የጸደቀው የቅድስት መንበር አዲስ ሐዋርያዊ ህግ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያለውን ሕግ ሊተካው እንደሚችል ገልጸዋል። ቢሆንም የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ተባብሮ በመሥራት፣ በውስጡ በሚገኙት መምሪያዎች አማካይነት ጠቅላላ ጉዳይን፣ የመንግሥታት ግንኙነትን እና ዲፕሎማሲያዊ የሰው ኃይልን ማስተባበር መሆኑን ገልጸዋል።

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር አብሮ መሥራት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከስምንት ዓመት በፊት የመላዋ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪ ሆነው በተመረጡ በሁለት ወራት፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ሆነው እንዲያገለግሉ በቅዱስነታቸው መጠየቃቸውን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ገልጸው በሁለቱ መካከል ያለው የባህሪይ ልዩነት ለሐዋርያዊ አገልግሎት የጠቀማቸው መሆኑን አስታውሰዋል። “በሰዎች መካከል የሚታዩ ልዩነቶች ዓለምን ወደ መልካም ጎዳና ማድረስ ያስፈልጋል” የሚለውን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ንግግር ጠቅሰው፣ የባሕርይ ልዩነቶች እንቅፋት የሚፈጥር ሳይሆን አመለካከትን፣ ስሜትን እና ዝግጁነትን በማሳደግ፣ ባህላዊ እና መንፈሳዊ ኅብረትን በመፍጠር አብሮ ለመሥራት የሚያግዝ መሆን አለበት ብለዋል።

በስብከተ ወንጌል እምነት የሚጣልባት ቤተክርስቲያን

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር አብሮ ስለ መሥራት ሲናገሩ፣ ቅዱስነታቸው ራስን ዝቅ አድርገው መቅረባቸው ያስደነቃቸው መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ገልጸዋል። አክለውም ከቅዱስነታቸው ጋር ተቀራርበው ሲሰሩ እጅግ የዋህ መሆናቸውን እና ከሌሎች ሰዎች ጋር ስላላቸው ግንኙነት የሚጨነቁ እና ሁል ጊዜ ከሰዎች ጋር ለመገናኘት ፍላጎት ያላቸው እና ቤተ ክርስቲያን በስብከተ ወንጌል አገልግሎቷ እምነት የሚጣልባት እንድትሆን ለማድረግ የሚጥሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በቤተክርስቲያን ውስጥ ስለሚታየው መከፋፈል አሳሳቢነት

በቤተክርስቲያን በሚገኙ አጥባቂ ወገን እና ተራማጅ ክንፍ መካከል ልዩነት መኖሩን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ይህ ሁኔታ በቤተክርስቲያን ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት አፅንዖትን ሰጥተው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን አንድነት መጸለዩን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት ብለው የተለያዩ የተሃድሶ ሥራዎችን መሥራታቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ይህም በርካታ አለመግባባቶችን ማስከተሉን ተናግረዋል። የቤተ ክርስቲያን አወቃቀር እንደማይለወጥ፣ የእምነት መሠረት እንደማይለወጥ፣ ቅዱሳት ምጢራት እና የቤተክርስቲያን አገልግሎቶች የማይለወጡ መሆናቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ለውጥ የሚያስፈልግባቸው ቦታዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ ድክመቶች የሚታይበት ሕይወት ያለ ማቋረጥ መታደስ አለበት ብለዋል። አንዳንድ ጊዜ በእነዚህ ክፍፍሎች መካከል የሚታየውን ግራ መጋባት እና ተቃውሞን በመለየት “አስፈላጊ እና መሻሻል ያለበት፣ የቅዱስ ወንጌልን መንፈስ መሠረት ያደረገ ለውጥ ሊኖር እንደሚገባ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ገልጸዋል።   

በቻይና ያለች ቤተክርስቲያን ተስፋ

በቻይና ያለች ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ቅድስት መንበር የቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ አመለካከት የምታከብር መሆኗን ገልጸው፣ በቻይና ያለች ቤተ ክርስቲያንን በርካታ ስቃዮች ቢደርስባትም ቅድስት መንበር በተስፋ የምትመለከተው መሆኑን አስረድተዋል። በሁለቱ መንግሥታት መካከል የተደረሱ ስምምነቶች ወደ እርቅ ጎዳና የሚያደርሱ ትክክለኛ አቅጣጫዎች መሆናቸውን ገልጸው፣ አሁን ያሉት ችግሮች ሁሉ መፍትሄ ባያገኙም ከጊዜ በኋላ ሊፈቱ ይችላሉ ብለዋል። “ከኢራቅ ምዕመናን ጋር ከተደረገው መንፈሳዊ ግንኝነት ብዙ መማር ያቻላል” ያሉት ካርዲናል ፓሮሊን፣ የኢራቅ ክርስቲያን ከሁሉም በላይ የእምነት ምስክርነት ያላቸው እና ይህ የእምነት ምስክርነት እስከ ሰማዕትነት ያደረሳቸው መሆኑን ገልጸዋል።  

በአውሮፓ ውስጥ የእምነት መቀዝቀዝ

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ስለ አውሮፓ ክርስቲያናዊ መሠረቶች እና እየራቁ ባሉ የሥነ ምግባር ጉዳዮች ላይ አዲስ ሕገ-ረቂቅ እንዲረቅ ሃሳብ መቅረቡን አስታውሰው፣ በተግባር እየተከናወኑ ባሉ የሥነ-ሰብአዊ ለውጦች መካከል “የእምነት መጥፋት” መታየቱን ገልጸዋል። በአውሮፓ ውስጥ ከእምነት ማጣት ይልቅ የሰብዓዊ ማንነት ማጣት” ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ በአውሮፓ ውስጥ የእምነት፣ የተስፋ እና የቸርነት ምስክሮች ሊኖሩ ይገባል ብለዋል።

የጸሎት አስፈላጊነት

በዛሬው ዓለም ለወንጌል ምስክርነት ተልእኮ እና ጠንካራ የቤተክርስቲያን አባልነት ጌታ እንዲረዳን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መጸለይ እንደሚያስፈልግ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አሳስበው፣ “COPE” ከተሰኘ የስፔን አውታረ መረብ ሬዲዮ ዳይሬክተር ከሆኑት ከአቶ ሆሴ ሉዊስ ሬስታን ጋር ያደረጉትን ቃለ መልልስ ደምድመዋል።

06 April 2021, 23:55