ፈልግ

በሰሜን ጣሊያን፣ በሚላኖ ከተማ የሚገኝ የሕዝብ መናፈሻ በሰሜን ጣሊያን፣ በሚላኖ ከተማ የሚገኝ የሕዝብ መናፈሻ 

የአውሮፓ አዛውንቶች ለአህጉሪቱ የነገ ተስፋዎች መሆናቸው ተገለጸ

“አዛውንቶች እና የአውሮፓ የነገ ዕድል” በሚል ርዕስ፣ ትናንት የካቲት 22/2013 ዓ. ም. የአውሮፓ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት እና የአውሮፓ ካቶሊካዊ ቤተሰብ ማኅበራት ፌዴሬሽን በጋራ ሆነው አንድ አውደ ጥናት ማዘጋጀታቸው ታውቋል። በአውታረ መረብ አማካይነት የተካሄደው የዚህ አውደ ጥናት ዋና ዓላማ፣ በኅብረሰባችን ውስጥ አቅመ ደካማ የሆኑንትን እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እጅግ የተጎዱ የዕድሜ ባለጸጎችን በማስታወስ መሆኑ ታውቋል። በዚህ ዙሪያ አስተያየታቸውን ያካፈሉት፣ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪክ እና ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት አረጋዊያን፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጊዜም ቢሆን በአውሮፓ ውስጥ ለወጣቱ ማኅበረሰብ የተስፋ ምንጭ መሆናቸው ታውቋል። የአውሮፓ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት እና የአውሮፓ ካቶሊካዊ ቤተሰብ ማኅበራት ፌዴሬሽን በአውታረ መረብ አማካይነት በጋራ ባካሄዱት አውደ ጥናት፣ የአውሮፓ አረጋዊያንን የውይይታቸው ማዕከል ማድረጋቸው ታውቋል። የአውሮፓ አረጋዊያንን በማስመልከት ለተካሄደው አውደ ጥናቱ ዋና መነሻ፣ “አዛውንቶች በሰብዓዊነታቸው የነገዋ አውሮፓ ተስፋዎች ናቸው” በሚል ርዕሥ፣ እ. አ. አ. በታኅሳስ 3/2020 ዓ. ም. ይፋ የተደረገ ሰነድ መሆኑ ታውቋል። የስነ-ሕዝብ ለውጦችን እና የዕድሜ ባለጸግነትን በስፋት የተመለከተው ሰነዱ፣ የዕድሜ ባለጸግነት በመዋዕለ ነዋይ ላይ የሚያስከትለውን ጫና እና በኅብረተሰብ ዘንድም ያለውን ፋይዳ በግልጽ ያስቀመጠ መሆኑ ታውቋል።

 

በዕድሜ እየገፉ የመጣ ሕዝብ

በቅርቡ የወጡት የጥናት ውጤቶች ይፋ እንዳደረጉት፣ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት በአውሮፓ ውስጥ ዕድሜያቸው ከስልሳ አምስት ዓመት በላይ የሆናቸው አረጋዊያን ቁጥር 20 ከመቶ የሚጨምር መሆኑን አስታውቆ፣ እ. አ. አ እስከ 2070 ዓ. ም. ድረስ ይህ ቁጥር 30 ከመቶ የሚጨምር መሆኑን አስረድቷል። የጥናቱ የትንበያ ውጤት በማከልም፣ በአውሮፓ ውስጥ የረጅም ጊዜ ድጋፍ የሚያስፈልገው የአዛውንት ቁጥር፣ እ. አ. አ. በ2016 ዓ. ም. 19. 5 ሚሊዮን ከነበረው፣ እ. አ. አ በ2030 ዓ. ም. ወደ 23. 6 ሚሊዮን ከፍ የሚል መሆኑን አስታውቋል። ይህም ማለት እ. አ. አ በ2050 ዓ. ም. የረጅም ጊዜ ድጋፍ የሚያስፈልገው የአዛውንት ቁጥር፣ ወደ 30. 5 ሚሊዮን የሚደርስ መሆኑን አስረድቷል።

በኤኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ወቅት ሰዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል

የአውሮፓ አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪክ፣ በአውታረ መረብ አማካይነት የተጀመረውን አውደ ጥናት ዛሬ የደመደሙት ሲሆን፣ ከአውደ ጥናቱ ለማወቅ እንደተቻለው፣ አውሮፓ በርካታ የዕድሜ ባለጸጎች የሚገኙባት ብትሆንም፣ አዛውንት ለአህጉሪቱ ተስፋን የሚሰጡ በመሆናቸው፣ የሚሰጣቸው ትኩረትም ሊያድግ እና ዋጋ ሊሰጠው ይገባል ተብሏል።

ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪክ በንግግራቸው፣ ያለ አረጋዊያን ተሳትፎ ሰብዕናን ማቆየት አይቻልም ብለው፣ የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት የኅብረተሰብ ክፍል በአውሮፓ ውስጥ ከፍተኛ ሚናን የሚቻወቱ መሆናቸውን ከገለጹ በኋላ፣ ድክመት ሲታይበት የቆየው የአዛውትን እንክብካቤ ከፍተኛ ዋጋ ተሰጥቶት መጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል። እስከ ዛሬ ድረስ የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑ አረጋዊያንን በመንከባከቢያ ማዕከላት ውስጥ ተጠብቀው መቆየታቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪክ፣ ለሕጻናት የበለጠ እንክብካቤ የሚሰጠው በመዋዕለ ንዋይ ዕድገት ከፍተኛ ተሳትፎ ይኖራቸዋል በሚል እሳቤ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ አስተሳሰብ ሊታረም እንደሚገባ ተናግረው፣ በመዋዕለ ንዋይ እድገት አስተሳሰባችን ስብዕናን ማካተት ያስፈልጋል ብለዋል። በሕይወታቸው መካከል የአያቶችን ድጋፍ ያስፈልገናል ከሚሉ በርካታ ወጣቶች ጋር መነጋገራቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪክ፣ የወላጅ ቤተሰብ ፍቅር ምን ጊዜም ቢሆን ሃያል መሆኑን አስረድተው፣ በመሆኑም ወጣቶች አያቶቻቸውን ማድመጥ እንዳለባቸው፣ አያቶችም ቢሆኑ በልጅ ልጆቻቸው እና በትውልዶች መካከል ዘወትር የተወደዱ መሆናቸውን ሊረዱ ይገባል ብለው፣ ዛሬ ለአዛውንት እንክብካቤ ካልተደረገላቸው ወጣቶቻች መልካም የወደፊት ዕድል አይኖራቸውም ብለዋል።

“የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በርካታ ጥረቶችን ያደረገን ማኅበረሰብ መውቀስ አስቸጋሪ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪክ፣ ወረርሽኙ ከተዛመተ ከአንድ ዓመት በኋላ አንዳንድ የተሳሳቱ አስተያየቶችን መግለጽ ያስፈልጋል ብለው፣ ከእነዚህ አስተያየቶች መካከል አንዱ፣ አዛውንቶችን ማግለል የሚል መሆኑን ገልጸው፣ ይህም የጭካኔ ተግባር መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ሆለሪክ አስረድተዋል። አንድ ሰው በስብዕናው ሊወደድ፣ በድረ ገጽ ሳይሆን ፊት ለፊት በሚገለጹ ቃላት አማካይነት መገናኘት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ይህም የአውታረ መረብ አጠቃቀም የማይችሉ አዛውንትን ከማግለል ለመከላከል ያግዛል ብለዋል። ፈጣን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምርመራ ውጤቶችን ማየት የምንችልባው መንገዶች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ አዛውንት ተለይተው ከሚኖሩበት ወጥተው ከማኅበረሰባቸው ጋር መገናኘት የሚችሉባቸውን በርካታ መንገዶች ለይተን ማወቅ ያስፈልጋል በማለት ብጹዕ ካርዲናል ሆለሪክ አስተያየታቸውን አካፍለው፣ በእነዚህ ውጤታማ መንገዶች አማካይነት አዛውንትን ከማኅበረሰባቸው ሳይለዩ እንክብካቤን መስጠት የምንችልበትን መንገድ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

ረጅም ዕድሜ መኖር መልካም ዜና ነው

በአውታረ መረብ አማካይነት የተካሄደውን አውደ ጥናት የተካፈሉት፣ በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ፕሬዚደንት የሆኑት፣ ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ፣ በአውሮፓ ውስጥ የአዛውንትን እንክብካቤ በተመለከተ የቅድስት መንበር ሚና ምን እንደሆነ ሲያስረዱ፣ በአውሮፓ ኅብረት ተዘጋጅቶ የቀረበው የፖሊሲ ሰነድ፣ ከዚህ በፊት ከቤተክርስቲያን በኩል ተዘጋጅቶ የሚወጣውን ሐዋርያዊ አገልግሎት ዘርፍ ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ፓለቲካዊ አስተሳሰቦች ያሉበት እና እምነት ለባሕል እና ለፖለቲካ አስተሳሰብ ትልቅ እገዛን ማድረግ እንደሚችል የተገለጸበት ሰነድ መሆኑን አስረድተዋል። ሰነዱ ከዚህም በተጨማሪ የቤተሰብን ሕይወት የሚመለከት የቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮን ያካተተ በመሆኑ፣ የሰነዱን መታተም በደስታ የተቀበሉት መሆኑን አስረድተዋል። “ረጅም ዕድሜ መኖር መልካም ዜና ነው” ያሉት በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ፕሬዚደንት ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ፣ የዕድሜ ባለጸግነት ጸጋ እንጂ ማንኛውንም ማኅበረሰብ ችግር ውስጥ የሚጥል ባለመሆኑ፣ ለአዛውንት የሚደረግ ማኅበራዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጥል ይኖርበታል ብለዋል። ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ በማከልም የማኅበረሰባች ዘላቂነት የሚረጋገጠው አምራች በሆነው ወጣቱ ማኅበረሰብ እና በአዛውንት ማኅበረሰብ መካከል ያለውን ግንኙነት በማስተካከል እንደሆነ አስረድተዋል። “ሁላችን ወንድማማቾች ነን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “በዕድሜ ባለ ጸግነት እና በስነ-ሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት በሚገባ ማወቅ ስንችል ችግሮችን ማቃለል እንችላለን” ያሉትን አስታውሰው፣ ውጤቱን ለማየት ተጋግዘን መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። በዕድሜ ባለጸጎች እና በወጣቶች መካከል ያለው ግንኙነት ማደግ እንደሚገባ ያስተወሱት ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ፣ ወጣቶች ከአዛውትን ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማሳደግ ለውይይት እንዲዘጋጁ ማበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል። በቅርቡ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ታሪኳን ለመስማት ብለው በናዚዎች ማጎሪያ ካምፕ ቆይታ የወጣች ኤዲት ብሩክን መጎብኘታቸውን ያስታወሱት ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ፣ በከንቱ መረሳት የሌለባቸው በርካታ ታሪኮች መኖራቸውን ገልጸው፣ በወጣቶች እና በአዛውንት መካከል ያለው ግንኙነት መቋረጥ እንደሌለበት አሳስበዋል። አክለውም በቤተሰብ መካከል እና በሐዋርያዊ አገልግሎት ወቅትም ቢሆን የውይይት ባሕልን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በበረታበት በዚህ ወቅት አጋዥ አጥተው ብቻቸው ከቀሩት አዛውንት ጋር በቅርብ በመወያየት ምክራቸውን ማድመጥ ያስፈልጋል ብለዋል። ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀንን ለማክበር ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ያስታወቁት ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የአውሮፓውያኑ 2021 ዓ. ም. የቤተሰብ ዓመት እንዲሆን ማወጃቸውን አስታውሰው፣ በዚህ የቤተሰብ ዓመት አዛውንትን ጨምሮ ለቤተሰብ በሙሉ ልዩ ሐዋርያዊ እንክብካቤ የሚደረግበት ዓመት መሆኑን አስታውቀዋል።

02 March 2021, 12:57