ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ ውስጥ የጋራ ውይይት እና መልሶ ግንባታ እንዲደረግ መልዕክት ያቀርባሉ ተባለ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ ውስጥ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ. ም. ድረስ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ አገሪቱን የሚጠቅሙ መልዕክቶችን ይዘው እንደሚሄዱ፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አስታወቁ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢራቅ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ ለብዙ ዓመታት በጦርነት እና በአመጽ ለተሰቃየው የኢራቅ ሕዝብ መጽናናትን እንደሚያመጡ ሲነገር በአገሪቱ ውስጥ የመልሶ ግንባታ፣ የወንድማማችነት እና የውይይት ተግባራት እየታካሄዱ መሆናቸው ተነግሯል። ይህችን አገር አንድ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ሲጎበኟት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል። ኢራቅ የእምነታችን አባት የሆነው የአብርሐም አገር በመሆኗ፣ እጅግ ጥንታዊ የሆነ የክርስቲያን ማኅበረሰብ የሚኖርበት መሆኑ ታውቋል። በኢራቅ ጦርነት ያስከተለው ጥፋት ዛሬም በግልጽ የሚታይ ሲሆን ይህን ተከትሎ ድህነት፣ የአሸባሪነት ወንጀል እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በስፋት የሚታይበት መሆኑ ታውቋል። በቫቲካን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ጉብኝት አስፈላጊነትን እና በኢራቅ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን በኅብረት በማስወገድ አዲስ የዕድገት ጎዳናን መጀመር የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ኢራቅ ለማድረግ ያሰቡትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያዘገዩት መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ከመጋቢት 26-29/2013 ዓ. ም. ድረስ በኢራቅ ውስጥ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፣ አገሪቱን ሲያሰቃይ በቆየው ጦርነት፣ የአሸባሪነት ወንጀል እና አመጽ ላይ ትኩረት በማድረግ፣ ለኢራቅ ሕዝብ ያላቸውን ወዳጅነት ለማሳየት ጥልቅ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል። የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ዋና ዓላማ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ በመግባት ለረጅም ዓመታት በመከራ ለኖረ የኢራቅ ሕዝብ ጠቃሚ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ እና አገሪቱን በኅብረት መልሶ በመገንባት ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስረድተዋል።

ከሦስት ዓመታት በፊት በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን አድርገው የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት ዋዜማ ምሽት፣ በባግዳድ በሚገኝ የከለዳዊያን ካቴድራል ውስጥ ተገኝተው ደስታቸውን በዜማ እና በደማቅ ብርሃን መግለጻቸውን አስታውሰዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በንግግራቸው ወቅት “ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” የሚለውን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት መሪ ቃልን አስታውሰዋል። ይህ ወንድማማችነት የሚመነጨው የኢራቅ ምድር ሰው የሆነው የአንዱ የአብርሃም ልጆች ከመሆናቸው የተነሳ ነው በማለት አስረድተዋል። ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥሪ የደረሰውም አብርሃም በኢራቅ ምድር ሳለ በመሆኑ እና ሁለቱ ሐይማኖቶች፣ ክርስትና እና እስልምና ይህን እውነት በጋራ የሚጠቅሱ መሆኑን አስታውሰው፣ ይህ እውነት በሁለቱም በኩል በተግባር መተርጎም አለበት ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በማከልም በአገሪቱ የሚታየውን ጨለማ ለማብራት፣ ሁለቱም ወገኖች ብርሃናቸውን እንዲያበሩ እና በርካታ ችግሮችን ለማቃለል በሂደት ላይ ያሉትን ጥረቶችን መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አገሪቱን ወደ ፊት የሚጠቅሙ መልዕክቶችን ማስተላለፍ እንደሚፈልጉ የገለጹት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በኢራቅ ውስጥ የስደት እና የሰማዕትነት ገድል እንደነበር አስታውሰው፣ ቤተክርስቲያን የዚህ መከራ እና ስደት ቀማሽ እንደመሆኗ፣ ከዚህ ለመውጣት በሐይማኖት ተቋማት መካከል የጋራ ውይይት ባሕልን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተናግረው፣ ከዚህ በፊት ያጋጠሙትን ችግሮች ወደፊት ለሚሠሩ ጠቃሚ ሥራዎች እንቅፋት እንዳይሆኑ በማገድ እና ተስፋን በመሰነቅ ኢራቅን መልሶ ለመገንባት በቆራጥነት መቆም እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በኢራቅ፣ ናይፍ ከተማ የሚገኙት ታላቁ አያቶላ ሰይድ አሊ አል ሁሴን አል ሲስታኒ በሺአ እስልምና እምነት ተከታይ ዘንድ ከፍተኛ ክብር የሚሰጣቸው መሆኑን የገለጹት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ አል ሲስታኒ በኢራቅ ውስጥ የሚገኙ የበርካታ ጎሳ አባላት እና የተለያዩ እምነት ተከታዮች በሰላም አብረው እንዲኖሩ በማለት መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። ይህ መልዕክታቸው በኢራቅ ውስጥ በሚገኙ የክርስቲያን እና ሙስሊም ማኅበረሰብ መካከል ወንድማማችነትን ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸውው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዚህ ወቅት በኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እጅግ አስፈላጊ እና ከፍተኛ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን አስረድተዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በኢራቅ ውስጥ የሚገኝ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብን ጨምሮ መላው ክርስቲያን ማኅበረሰብ የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ጉብኝት በናፍቆት የሚጠብቁ መሆኑን ገልጸዋል። በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኝ ክርስቲያን ማኅበረሰብ፣ ክርስቲያናዊ ጥሪውን በተግባር መግለጽ እንዲችል ብርታትን እና መጽናናትን የሚሰጥ መልዕክት የሚያስፈልገው በመሆኑ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለአገሩ ክርስቲያን ማኅበረሰብ የሚያስተላልፉት ሐዋርያዊ መልዕክት፣ ምዕመናኑ በሚገኙበት አካባቢ እንዲጸና እና ለእምነቱ የሚሰጠውን ምስክርነት እንዲቀጥል የሚያበረታታ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ተናግረው፣ አክለውም በመካከለኛው ምስራቅ አግሮች የክርስቲያኖች መገኘት አስፈላጊ እንደሆነ ብዙ ጊዜ መናገራቸውን አስታውሰዋል።

የኢራቅ መንግሥት እና መላው የኢራቅ ሕዝብ ከረጅም ጊዜ አስከፊ ጦርነት እና አመጽ በኋላ በሰላም አብሮ መኖርን፣ የጋራ ውይይቶችንርም ማድረግ እንደሚገልግ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ በኢራቅ ውስጥ ኅብረት ሊኖር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። እርስ በእርስ ለመተጋገዝ የሚያስችል አንድነትን ለመፍጠር ይቅር መባባል እና ከአክራሪነት ባሕልም መላቀቅ አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በመጨረሻም በኢራቅ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለኢራቅ ሕዝብ አዲስ ኤኮኖሚያዊ እና መንፈሳዊ ለውጥን እንዲያመጣ ተመኝተው፣ ለውጥን ለሚሹት የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሕዝቦች የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት የወንድማማችነት ምሳሌ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

03 March 2021, 15:26