ፈልግ

ብጹዕ አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ ብጹዕ አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ  

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመዋጋት ከክትባት በተጨማሪ አንድነት እና ወንድማማችነት ሊኖር ይገባል ተባለ

በቅድስት መንበር የአውሮፓ ደህንነት እና የተቋማት ትብብር ቋሚ ተጠሪ፣ ብጹዕ አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ ከፍተኛ ጉዳትን በማስከተል ላይ የሚገኘውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል እንዲቻል አንድነትን፣ ለሰው ልጅ እድገት የሚያግዙ የኤኮኖሚ ሞዴሎችን ተግባራዊ በማድረግ የመከላከያ ክትባት ለሁሉ እንዲደርስ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አቡነ ጄነሽ አክለውም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በዓለም አቀፍ አንድነት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ሥነ ምግባራዊ ማዕቀፍ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው፣ ከዚህም በተጨማሪ የመከላከያ ክትባት ስርጭትን በሰዎች መካከል ልዩነትን ሳይፈጥሩ ለሁሉም መድረሱን ማረጋግጥ ያስፈልጋል ብለዋል። በቅድስት መንበር የአውሮፓ ደህንነት እና የተቋማት ትብብር ቋሚ ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ ይህን ያስታወቁት ያለፈው ሰኞ መጋቢት 6/2013 ዓ. ም. ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለማገገም እና የአውሮፓ አገሮች ደህንነት እና ኅብረት ለማጠናከር የሚያስችሉ መንገዶችን ለመፈለግ በተቀመጠው ስብሰባ ላይ መሆኑ ታውቋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ውጤቶች

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአንድ ጊዜ በርካታ ችግሮችን አስከትሏል ያሉት አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ፣ በብሔራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ በጤና፣ በኤኮኖሚ እና በማኅበርዊ ሕይወት ላይ ቀውስን በማስከተል ከዚህ በፊት በተዘረጉ ሞዴሎች ላይ አደጋ ማስከተሉን አስረድተዋል። አስቀድመው የነበሩ የምግብ እጥረት፣ የስደት እና የኤኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲባባስ ከማድረግ በተጨማሪ በሰዎች መካከል መለያየት እና እምነት ማጣት እንዲጨምር ዕድል መፍጠሩን፣ በመንግሥታት መካከል የነበረው ግንኙነት እንዲቀዘቅዝ ማድረጉን አስታውሰዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በአንድ ወቅት ንግግራቸው፣ ወረርሽኙ ካስከተለብን ቀውስ ስንውጣ የሚኖረን ዕድል የተሻለ ወይም ካልሆነ የከፋ  ይሆናል ማለታቸውን ያስታወሱት አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ፣ አሁን ያለንበትን ሁኔታ ስንመለከተው በሁሉም ዘንድ የሚታየውን አቅመ ደካማነት በመገንዘብ የጋራ መፍትሄዎችን እየፈለግን ወደ ፊት ከመጓዝ በስተቀር ሌላ ምርጫ የለንም ብለዋል።

ኮቪድ -19: የውጥ እድልን አመቻችቷል

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ መካከል ተጨባጭ የሆነ የለውጥ ዕድል መኖሩን የገለጹት አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ፣ ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት ክፍፍል በድሃ እና ሃብታም መካከል ልዩነቶችን መፍጠሩን ተመልክተን የኑሮ ልማዶቻችንን፣ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሥርዓታችንን እንደገና ማጤን ያስፈልጋል ብለው፣ ይህን ማድረግ የሚቻለው የበለጠ ጠንካራ ሥነ-ምግባር ማዕቀፍ የመፍጠር አቅማችንን በማወቅ ዓለም አቀፍ  አንድነትን ስናሳድግ እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን አስፈላጊ እንክብካቤን እና ጥበቃን ስናደርግ ነው ብለዋል። የዚህ ሁሉ እቅድ መሠረታዊ ዋና ዓላማ ሁለንተናዊ የጤና እንክብካቤ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ፣ በተለይም የክትባት መርሃ ግብርን ፍትሃዊነት ባለው መንገድ ለሁሉ እንዲደርስ ለማድረግ መሆኑን ብጹዕ አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ አስረድተዋል። አክለውም የኮቪድ-19 ክትባት ወረርሽኙን ለመከላከል ቢያግዘንም ነገር ግን የኑሮ አለ መመጣጠንን እና ግዴለሽነትን ጨምሮ ለረጅም ዓመታት ከቆዩ ማህበራዊ ችግሮች ሊያድነን አይችልም ብለዋል።

ሰብአዊ ኢኮኖሚ ሞዴል መገንባት

ማህበራዊ ችግሮች ለመዋጋት፣ አንድነትን እና ኤኮኖሚያዊ ዕድገትን የሚያግዙ፣ ሁሉን አቀፍ ሰብዓዊ እና ኤኮኖሚያዊ ሞዴሎችን በመዘርጋት በግለ ሰቦች እና በኤኮኖሚ መካከል ግንኙነትን በመፍጠር፣ አካባቢያዊ ማህበረሰቦችን በሚጠቅም የትምህርት እና መሠረተ ልማት ዘርፍ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ እንደሚያስፈልግ ብጹዕ አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ አሳስበዋል። አክለውም ኤኮኖሚው በእርግጥ ለሰው ልጅ ልማት በሚውልበት ጊዜ፣ በሰው ልጆች ማኅበራዊ ግንኙነቶች መካከል እምነትን በመፍጠር፣ በአውሮፓ አገሮች መካከል እና በሌሎች አካባቢዎችም ደህንነትን እና ትብብርን የሚያጠናክሩ የጋራ ውይይቶች እንዲኖሩ ያደርጋል ብለዋል።

በቅድስት መንበር የአውሮፓ ደህንነት እና ተቋማት ትብብር ቋሚ ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጄነሽ አርባንቺክ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ እንደተናገሩት፣ ቅድስት መንበር በአውሮፓ ደህንነት እና ተቋማት ትብብር ላይ ያላት እምነት የሚጨምረው ዓለም አቀፋዊ አደጋዎች ሲገጥሙን ሁላችንም በጋራ እርምጃ ስንወስድ እንደሆነ ገልጸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ጎን ለጎን ወንድማማችነትን ማሳደግ እና ተስፋን መያዝ ለዛሬዋ ዓለም አስፈላጊ መድኃኒቶች ናቸው” ማለታቸውን አስታውሰዋል።  

17 March 2021, 15:20