እህት ኑሪያ ኮልዳች ቤነጄስ እህት ኑሪያ ኮልዳች ቤነጄስ 

በቫቲካን ለመጽሐፍ ቅዱስ ኮሚሽን፣ የመጀመሪያዋ ሴት ዋና ጸሐፊ ሆነው ተሾሙ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የካቲት 30/2013 ዓ. ም. የስፔን ተወላጅ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ የሆኑትን እህት ኑሪያ ኮልዳች ቤነጄስን የጳጳሳዊ መጽሐፍ ቅዱስ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ አድረገው መሾማቸው ታውቋል። እህት ኑሪያ ኮልዳች ቤነጄስ የተሰማቸውን ደስታ ከቫቲካን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ምስጋናቸውን በማቅረብ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እህት ኑሪያ ለመጽሐፍ ቅዱስ ባደረባቸው ፍቅር የተነሳ ለበርካታ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ያሳለፉ መሆኑ ታውቋል። ባሁኑ ጊዜ ሮም ከተማ በሚገኝ የግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ መምህር እና የቅዱሳት መጽሐፍት ሊቅ መሆናቸው ታውቋል። በስፔን የባርሴሎና ከተማ ነዋሪ የሆኑት እህት ኑሪያ፣ የናዝሬቱ ቅድስት ቤተሰብ ሚሲዮናዊያን የሴቶች ማህበር አባል መሆናቸው ታውቋል። እህት ኑሪያ ከዚህም በተጨማሪ ለሴቶች የሚሰጥ የድቁና ማዕረግ ሥርዓትን የሚያጠና ምክር ቤትን ተቀላቅለው እ. አ. አ ከ2016-2019 ዓ. ም. መሥራታቸው ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የካቲት 30/2013 ዓ. ም. የጳጳሳዊ መጽሐፍ ቅዱስ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ አድረገው የመሾሟቸው እህት ኑሪያ እ. አ. አ. ከ2014 ዓ. ም. ጀምሮ የኮሚሽኑ አባል ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ኮሚሽኑን በዋና ጸሐፊነት እንዲያገለግሉ መሾማቸው ታውቋል።

እህት ኑሪያ ተጋባዥ ፕሮፌሰር ሆነው ሮም ከተማ በሚገኝ ጳጳሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቋም ውስጥ በመምህርነት የሚሠሩ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪም የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ፌዴሬሽን ተባባሪ መሆናቸው ታውቋል። እህት ኑሪያ የበርካታ ታዋቂ የሆኑ ሳይንሳዊ መጽሔቶች አዘጋጅ ኮሚቴ አባል ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ እ. አ. አ በ2008 ዓ. ም. “እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን ሕይወት እና ተልእኮ ውስጥ” በሚል ርዕስ ላይ በተወያየ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንደ ባለሙያ መሳተፋቸው ይታወሳል።

“ለዚህ ሃላፊነት እደርሳለሁ ብዬ አልገመትኩም” ያሉት እህት ኑሪያ፣ በእርሳቸው ላይ እምነትን በመጣል ለሃላፊነት ያበቁትን ሰዎች በሙሉ አመስግነዋቸዋል። እህት ኑሪያ አክለውም፣ በሌሎች ምክር ቤቶች እንደሚታየው ሁሉ በጳጳሳዊ መጽሐፍ ቅዱስ ኮሚሽን ውስጥ ሴቶች መሳተፋቸው ቤተክርስቲያን ከምን ጊዜም በላይ አድማሷን እየከፈተች መምጣቷን የሚገልጽ አዎንታዊ እና አስፈላጊ አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል።

ለሦስት ዓመታት ማለትም እ. አ. አ ከ2016-2019 ዓ. ም. ድረስ ከሌሎች አባላት ጋር ሆነው ለሴቶች የሚሰጥ የድቁና ማዕረግ ሥርዓትን ከሚያጠና ምክር ቤት ጋር መሥራታቸውን ያስታወሱት እህት ኑሪያ፣ በወቅቱ ያገኙት ልምድ ከአዕምሯዊ ክህሎት እና ከቤተ ክርስቲያን እይታ እንዲሁም በሰብዓዊ አመለካከት አንፃር ያሳደጋቸው መሆኑን ገልጸው፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀ የወዳጅነት እና የትብብር ግንኙነቶች እንዲኖሩ አግዞናል ብለዋል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ወይም የእግዚአብሔር ቃል ጥናት የሴቶችን እውቀት፣ ምኞታቸውን እና የወደፊት ህልማቸውን ገሃድ ማድረጉን ያስረዱት እህት ኑሪያ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት የሴቶች ታሪኮች  የእነርሱ ትረካዎች ፣ የሴቶች ዘይቤያዊ አነጋገር አጠቃቀም ፣ የሴትነት ትርጉም እና ሌሎች በርካታ ገጽታዎች ወደ እግዚአብሔር ቃል ጥናት የሚያመጡ መሆናቸውን አስረድተዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ ሴት መኖሯ ተሰምቶ ከማይታወቅበት ከአርባ ዓመታት በፊት፣ ሴቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ስለ መሳተፍ ብዙም እውቅና አይሰጥም ነበር ያሉት እህት ኑሪያ፣ ዛሬ ግን በሁሉም ዘንድ አድናቆትን በማግኘት፣ ከወንዶች ጋር እኩል አመለካከትን በማግኘት በበርካታ ስነ ጽሑፎች ላይ የሚጠቀሱ መሇቸውን ገልጸዋል።

በአንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አገላለጾች ላይ በተለይም በእስራኤል ታሪክ ውስጥ ሴቶች እውነተኛ ተዋንያን ሆነው በመቅረብ ሌሎች ሰዎችን በመወከ አስፈላጊ ተልዕኮን ሲፈጽሙ መታየታቸውን እህት ኑሪያ አስታውሰዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ሴቶች በወንዶች ሥልጣን ሥር በመሆን ስማቸው እንዳይነሳ ሲደረግ፣ በሌላ ወገንም በደራሲያን ዘንድም ታሪካቸው ሳይገለጽ መቆየቱን አስረድተው፣ ታሪካቸው ስላልተነገረላቸው ድምጻቸውም እንደዚሁ አልተሰማም ብለዋል። ትልቁ የሴቶች ችግር ይህ ነው ያሉት እህት ኑሪያ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች፣ ሴቶች በእያንዳንዱ ዘመን ቅርሶች መሠረት የሚገለፁባቸው እና እንደ ደራሲያን መሠረታዊ አመለካከት የሚገለጹ እጅግ ጥንታዊ ጽሑፎች መሆናቸውን ልንዘነጋው አንችልም በማለት ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ደምድመዋል።

17 March 2021, 15:16