የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት  

የር. ሊ. ጳ በጎ አድራጎት ጽ/ ቤት እስከ ፋሲካ በዓል ለ 1200 ሰዎች ክትባት እንደሚሰጥ አስታወቀ

በችግር ውስጥ ለሚገኙ ደሃ ማኅበረሰብ በተቻለ መጠን እገዛን ማድረግ ያስፈልጋል በማለት ርዕሠሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን ጥሪ ለማጠናከር የሚያግዝ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት መርሃ ግብርን እስከ ፈረንጆቹ ፋሲካ በዓል ድረስ 1200 ክትባቶችን ለድሆች የሚሰጥ መሆኑን በቫቲካን የሚገኝ የር. ሊ. ጳ በጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። ቅድስት መንበር በግዥ ወደ አገር ውስጥ ያስገባችውን የኮቪድ-19 መከላከያ መድኃኒት የሚያከፋፍለው በሮም የሚገኝ የስፓላንዛኒ ሆስፒታል መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ይበልጥ የተጋለጡ በቁጥር 1200 የሚደርሱ ድሃ ሰዎች ያለፈው ሰኞ በተጀመረው የአውሮፓዊያኑ የሕማማት ሳምንት ወደ ቫቲካን በመምጣት “Pfizer-BioNTech” የተባለ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት በመውሰድ ላይ መሆናቸውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ሁሉም እኩል የክትባቱ ተጠቃሚ ይሁን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ለሁሉም እኩል ተደራሽነት እንዲኖረው በማለት ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረባቸውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤት አስታውሷል። የክትባቱ መርሃ ግብር የሚካሄደው በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ መሆኑን የበጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤቱ አስታውቆ በተጨማሪም ክትባቱን በማዳረስ ላይ የሚገኙ የ“ማድሬ ዲ ሚዜሪኮርዲያ” የሕክምና ማዕከል ሐኪሞች ፣ የጤና ሠራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች ቀደም ሲል ከ 96 አገራት ለመጡት በቁጥር ከ 1200 በላይ ድሃ እና አቅመ አካማ ሰዎች ነጻ የኮቪድ-19 ምርመራ አገልግሎት ማድረጋቸውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።  

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ በድህነት ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ካለን በማካፈል ሕክምናን እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል በማለት ዕርዳታቸውን በአውታረ መረብ አማካይነት ማቅረብ ለሚፈልጉት “www.elemosineria.va” የሚል የበጎ አድራጎት ድረ ገጽ መዘርጋቱን አስታውቋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት በሁሉም አካባቢ እኩል ተደራሽነት እንዲኖር በማለት የቀረቡት ጥያቄዎች በብዙ አገሮች ዘንድ ተሰሚነትን ሳያገኙ በመቅረታቸው ምክንያት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰዎች ሁሉ እኩል መብት እንዳላቸው በማስታወስ፣ “በድህነት ምክንያት ማንም ሰው ሳይገለል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን ማግኘት እንዳለበት በድጋሚ ማሳሰባቸውን የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ አስታውሷል።

በጥር ወር 25 ቤት አልባ ሰዎች ክትባት አግኝተዋል

ባለፈው ጥር ወር ላይ በቫቲካን የክትባት መርሃ ግብር በተጀመረበት ወቅት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ አካባቢ ለሚኖሩ 25 የጎዳና ላይ ተዳድሪዎች የክትባት አገልግሎት የተሰጣቸው ሲሆን በአካባቢው በሚገኙ የር. ሊ. ጳ የበጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤት ብኩል ድጋፍና አቀባበል የተደርጎላቸው መሆኑ ይታወሳል። ዕድሜያቸው ከ 60 ዓመት በላይ የሆናቸው ወንዶች እና ሴቶች ከባድ የአካል ችግር እንዳለባቸ ሲታወቅ ብሔራዊ የጤና ዕርዳታን ለማግኘትም ችግር የሚያጋጥማቸው መሆኑ ታውቋል። ይህን ችግር በመረዳት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መስራጨት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁል ጊዜ በምሬት ፣ በጣሊያን እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሆስፒታሎች የሕክምና መስጫ መሣሪያዎችን እና ሌሎች ቁሳ ቁሶችን በመለገስ እንዲረዱ መጠየቃቸው ይታወሳል።

ኃላፊነትን ለመወጣት መሞከር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከልያ ክትባትን መውሰድ “በሌሎች ላይ ያለንን ኃላፊነት እና የጋራ ደህንነት ማረጋገጥ ነው” በማለት ለመንግሥታት መሪዎች፣ ለንግድ ተቋማት እና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች አፅንዖትን በመስጠት ባስተላለፉት ያለፈው ዓመት የብርሃነ ልደት መልዕክታቸው በመላው ዓለም የገባውን ቀውስ ለመመከት የሚያስችል መፍትሄን ለማግኘት ሁሉም መተባበር እንደሚያስፈልግ ጠይቀው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት ለሁሉም እንዲደርስ፣ ከሁሉም አስቀድሞ ከማኅበረሰቡ ለተገለሉ አቅመ ደካማ ማኅበረሰብ ማቅረብ እንደሚገባ ገልጸው “ድንበር የማያግደውን ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ሳንገድብ "ሁላችንም በአንድ ጀልባ ላይ መሳፈራችንን መዘንጋት የለብንም” በማለት ማሳሰባቸው ይታወሳል።

31 March 2021, 15:48