ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኢራቅ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚደረግ ዝግጅት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኢራቅ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚደረግ ዝግጅት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ ውስጥ ለነነዌ ክርስቲያን ማኅበረሰብ የገንዘብ ዕርዳታ አድርገዋል

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በኢራቁ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት ክፉኛ የተጎዳውን የነነዌ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ለማቋቋም የሚያግዝ የገንዘብ እርዳታ ማድረጋቸው ተገለጸ። ለነነዌ ክርስቲያኖች መቋቋሚያ እንዲሆን የተሰበሰበው ዕርዳታ፣ ከዚህ በፊት ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስጦታ የቀረበላቸው መኪና በጨረታ ተሽጦ የተገኘ ገንዘብ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመጪው መጋቢት 26-29/2013 ዓ. ም. ድረስ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የኢራቅ ሕዝብ በናፍቆት የሚጠባበቅ መሆኑ ታውቋል። በኢራቅ በተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ከፍተኛ ጥፋት ደርሶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች በኩል በተሰነዘረ ጥቃት በርካታ የነነዌ ክርስቲያኖች መኖሪያ አካባቢያቸውን ለቅቀው መሰደዳቸው ይታወሳል። የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የገንዘብ ዕርዳታን ለነነዌ ክርስቲያን ማኅበረሰብ የሚያደርስ እና ዋና ጽሕፈት ቤቱን ሮም ላይ ያደረገ አንድ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽ መሆኑ ታውቋል። ፋውንዲሽኑ ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኩል ለተገኘ የ200 ሺህ ዩሮ የገንዘብ ዕርዳታ ቅዱስነታቸውን አመስግኖ፣ በዚህ ዕርዳታ በመታገዝ የነነዌ ክርስቲያን ማኅበረሰብን መልሶ ለማቋቋም ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል የሁለት ፕሮጄክቶች ጥናት መጠናቀቁን አስውቋል።

ሕጻናትን ጨምሮ ሌሎችንም መደገፍ ያስፈልጋል

በኢራቅ በተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን የነነዌ ቤተክርስቲያን መልሶ ለማቋቋም የሚውል የገንዘብ ዕርዳታ በአካባቢው ሁለት ፕሮጄክቶችን ሰርቶ ለመጨረስ የሚያግዝ መሆኑ ታውቋል። የመጀመሪያው እና በባሺቃ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም የሚገነባ አንድ ሁለገብ አዳራሽ እና አንድ መዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤት መሆኑ ታውቋል። በጣሊያን ሮም ከተማ የሚገኝ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አቶ አሌሳንድሮ ሞንቴዱሮ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ በኢራቅ ውስጥ በነነዌ ክፍለ ሀገር የሶርያ ስርዓት አምልኮን ለምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የተላከው የመጀመሪያ ዙር የገንዘብ ዕርዳታ መጠን 166 ሺህ ዩሮ መሆኑን እና በሁለተኛው ዙር የተላከው የገንዘብ ዕርዳታ መጠን 124 ሽህ፣ በድምሩ 290 መሆኑን አስረድተው ከዚህ ዕርዳታ መካከል 200 ሺህ ዩሮን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መለገሳቸውን ገልጸው፣ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ በበኩሉ 34 ሺህ ዩሮ መለገሱስ አስታውቀዋል። ለነነዌ ክፍለ ሀገር ክርስቲያኖች የሚውል ፕሮጀክት ባሁኑ ጊዜ ተሰርቶ መጠናቀቁን ያስታወቁት የጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ዳይሬክተር ክቡር አቶ አሌሳንድሮ ሞንቴዱሮ፣ ከአገልግሎት ምስጫ ማዕከላት አንዱ የሆነው እና በቁጥር ወደ 70 የሚሆኑ ሕጻናት ገብተው የሚማሩበት የመዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት አገልግሎት መስጠት አለመጀመሩን ገልጸዋል። በሁለቱ ፕሮጄክቶች በኩል ጉዳት የደረሰበን የነነዌ ቤተክርስቲያን ለመርዳት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ላደረጉት ዕርዳታ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ ምስጋና ማቅረቡን የጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ዳይሬክተር ክቡር አቶ አሌሳንድሮ ሞንቴዱሮ ገልጸዋል።

የነነዌ ማኅበረሰብ ዕረፍት እንዲያገኝ ማድረግ

የነነዌ ክርስቲያን ማኅበረሰብ በሁለቱ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ የተሰማውን ደስታ ገልጾ፣ በባሺቃ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም በተገናባው የመዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤት ሕጻናት ተመልሰው ትምህርታቸውን መከታተል መቻላቸው ሕጻናቱን የሚያበረታታ መሆኑን የሞሱል ከተማ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሐና ቡትሮስ ሙኬ እና በሞሱል የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቁምስና መሪ ካህን ክቡር አባ ሬዝቃላ አልሲማኒ ተናግረዋል። በኢራቅ የነነዌ ክፍል ሀገር ውስጥ ከሚገኙት ነዋሪዎች መካከል 45 ከመቶ የሚሆኑ ቤተሰቦች የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች ባደረሱባቸው ጥቃት ቄያቸውን ለቅቀው መሰደዳቸውን ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ እ. አ. አ. በጥር 12/2021 ዓ. ም. ባቀረበው ሪፖርት አስታውቋል። ታጣቂ ቡድኑ በአካባቢው ባደረሰው ጥቃት 57 ከመቶ ውድመት የደረሰበት መሆኑን ፋውንዴሽኑ ገልጾ፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በተገነው ድጋፍ መኖሪያ ቤቶች በመገንባታቸው በሰደት ላይ የቆዩት ቤተሰቦች ወደ አካባቢያቸው በመመለስ ላይ መሆናቸውን ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ አክሎ አስታውቋል።

27 February 2021, 13:35