ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር፣ ምን ጊዜም የማይገረሰስ የሰው ልጅ መብት ሊከበር ይገባል አሉ

በቫቲካን የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር፣ የካቲት 16/2013 ዓ. ም. ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክታቸው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል የተወሰዱ አንዳንድ እርምጃዎች ቢኖሩም, ምን ጊዜም ቢሆን የማይገረሰስ የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብቶች መከበር እንዳለባቸው ገለጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር፣ ሰኞ የካቲት 15/2013 ዓ. ም. በጄኔቭ ስዊዘርላንድ ለ46ኛ ጊዜ በተከፈተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰብ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በተጨባጭ ለመተግበር በቅድሚያ የሰብዓዊ መብቶች መሠረት በሚገባ መታወቅ አለበት ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር በመልዕክታቸው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከአንድ ዓመት በላይ በሚሆን ጊዜ ውስጥ ሁሉንም የማኅበራዊ ሕይወት ዘርፎችን የዳሰሰ፣ ለበርካታ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ በኤኮኖሚያዊ ማኅበራዊ እና የጤና ሥርዓቶችም ጥርጣሬን ያስከተለ መሆኑን ገልጸው፣ በተጨማሪም ጠቅላላ ሰብዓዊ መብቶችን ከጥቃት ተከላክሎ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የተጀመረው ጥረት ፈተና ላይ መጣሉን አስረድተዋል። “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለውን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፣ ለዘመናችን እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር፣ የእያንዳንዱን ሰው ክቡር በመገንዘብ፣ ለወንድማማችነት ያለን ምኞት እንደገና እንዲወለድ አስተዋፅዖ ማበርከት እንችላለን ብለዋል።

ለሰብአዊ መብቶች ቅድመ ሁኔታን ማስቀመጥ አያስፈልግም

“የሰብዓዊ ቤተሰብ ተፈጥሮአዊ ክብር፣ እኩልነት እና የማይገረሰሱ መብቶች ዕውቅና የነፃነት ፣ የፍትህ እና የሰላም መሠረት ነው” የሚለውን የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር፣ እንደዚሁም የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር “በመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች፣ በሰው ልጅ ክብር፣ በወንዶች እና ሴቶች እኩልነት፣ በሃያላን እና በማደግ ላይ ባሉት ሀገሮች እኩል መብቶች ላይ እምነት እንዳለው” የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል። እነዚህ ሁለት ሰነዶች፣ እያንዳንዱ የሰው ልጅ በተፈጥሮ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰብዓዊ ክብር እንድተሰጠው በተጨባጭ የሚያረጋግጡ መሆኑን ገልጸው፣ ሰብዓዊ ክብር የጊዜ ፣ የቦታ ፣ የባህል ወይም የአውድ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠለት አለመሆኑን አስረድተዋል። እነዚህን መልካም ሃሳቦች በቃላት መግለጹ ቀላል ቢሆንም ወደ ተግባር መለወጡ ከባድ ሆኖ መቆየቱን ገልጸው፣ ወደ ተግባር ከመለወጥ አስቀድሞ በሁሉም ዘንድ በውል ሊታወቁ፣ ሊከበሩ፣ ሊጠበቁ እና ሊያድጉ እንደሚገባ አስረድተዋል። 

ሰብዓዊ መብቶች ከዓለም አቀፍ እሴቶች የተለዩ አይደሉም

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጋላገር በመቀጠል እውነተኛ የመሠረታዊ መብቶች መጎልበት የሚወሰነው መሠረታቸው ሲረጋገጥ ወይም ሲታወቅ መሆኑን ተናግረው፣ ሰብዓዊ መብቶችን አስቀድመው ከነበሩበት ሁለንተናዊ እሴቶች መለየት እንቅፋትን ከመፍጠር በተጨማሪ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ለተሳሳቱ ራዕዮች እና ርዕዮተ ዓለም ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ብለዋል። መልካም እሴቶችን የማያካትቱ ሰብዓዊ መብቶች ለተለያዩ ግዴታዎች እና ቅጣቶች በመጋለጥ፣ የቆሙለትን ተልዕኮ ሳያሳኩ እርስ በእርስ በሚጋጩ የመንግሥት ደንቦች የመደናቀፍ ዕድል እንደሚያጋጥማቸው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር አስረድተው፣ ትክክለኛ መሠረት የሌላቸውን አዳዲስ መብቶችን በመፍጠር፣ ለሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር የሚሰጥ አገልግሎት እንዳይኖር ያደርጋሉ ብለዋል።

የሕይወት መብት

ሰብዓዊ መብቶች ከእሴቶች የማይነጣጠሉ መሆናቸውን የሕይወት መብትን ምሳሌ በማድረግ ያስረዱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጋላገር፣ የስቃይ ድርጊቶችን በመቃወም ፣ የመሰወር እና የሞት ቅጣትን በመከላከል” የተወሰደውን እርምጃ አድንቀው፣ እንዲሁም አዛውንቶችን ፣ ስደተኞችን ፣ ሕጻናትን እና እናቶችን ከአደጋ ለመከላከል” የተደረጉ ተግባራትን አስታውሰዋል። እነዚህ መልካም ተግባራት የሕይወት መብትን የሚያስጠብቁ የመሠረታዊ መብት ግኝቶች መሆናቸውን ገልጸው፣ በሕይወት መኖር መብት ከመሆኑ በፊት እንክብካቤ እና ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል ብለው፣ ለመብት የሚሰጠው ዋጋ በከንቱ እንዳይጠፋ ለማድረግ ከዋናው መሠረታዊ መብት ተለይቶ እንዳታይ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ኮቪድ-19 እርምጃዎች እና ሰብአዊ መብቶች

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት፣ የሕዝብን ጤና ለመታደግ እየተባለ በመንግሥት ባለስልጣናት በኩል የሚወሰዱ አንዳንድ እርምጃዎች በሰብዓዊ መብቶች ላይ ችግርን እያስከተሉ እንደሆነ የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር፣ የህዝብ ጤና ጥበቃን በተመለከተ፣ በሰብአዊ መብቶች አጠቃቀም ላይ ያሉ ውስንነቶች የግድ አስፈላጊ ከሆኑ ሁኔታዎች የሚመነጩ መሆን አለባቸው ብለው፣ ምክንያቱን ሲያስረዱ አቅም የሚያንሳቸው አረጋዊያን፣ ስደተኞች ፣ የአካባቢው ነባር ተወላጆች ፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ዜጎች እና ሕፃናት፣ አሁን በተፈጠረው ችግር ያለመጠን የተጎዱ መሆናቸውን አስረድተዋል። ብጹዕ አቡነ ጋላገር አክለውም፣ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረጉ እርዳታዎችን የሚጫኑ ማናቸውም ገደቦች “ከሁኔታው ጋር ተመጣጣኝ መሆን እንዳለባቸው አሳስበው፣ አድሎአዊ ባልሆነ መንገድ የሚተገበሩ እና ሌሎች አማራጭ መንገዶች በማይኖሩበት ጊዜ ብቻ መተግበር እናዳለባቸው አሳስበዋል።

የሐይማኖት ነፃነት

የሃሳብ፣ የህሊና እና የሐይማኖት ነጻነት ሊከበር ይገባል ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጋላገር፣ እምነትን እና ሃሳብን መግለጽ፣ የሰብዓዊ ክብር መሠረት መሆኑን ገልጸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሐይማኖት ነጻነት መጣሱን ገሃድ አድርጓል ብለው፣ የቅድስት መንበርን አቋም በማንጸባረቅ እንደተናገሩት፣ የሐይማኖት ነጻነት ሰብዓዊ መብቶች የሚያካተቱባቸውን የሕዝብ ምስክርነትን፣ በግል ሆነ በጋራ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን፣ አምልኮን እና አስተምህሮችን የመካፈል መብቶችን የሚያስከብር መሆኑን አስረድተዋል። እነዚህን መብቶች ለማስከበር የፖለቲካ ባለስልጣናት፣ የሐይማኖት መሪዎች እና የሲቪል ማኅበረሰብ መሪዎች የሐይማኖት እና የሕሊና ነጻነቶችን ለማስከበር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሰብዓዊ ወንድማማችነት ፣ አንድነት

አሁን የምንገኝበት ችግር ሁለገብ ዘርፎችን እንድንመለከት ያስገድደናል ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር፣ ሁለገብ ዘርፎች የምንላቸውም፣ አዲስ አመለካከት ያላቸው ዓለም አቀፍ ሃላፊነቶች፣ እግዚአብሔር ለዓለም ባቀደው መሠረት በፍትህ፣ በሰላም እና በአንድነት ላይ የተገነቡ ሰብዓዊ ቤተሰብን ማደራጀት መሆኑን አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ባሉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ ዓለም አቀፍ ወንድማማችነትን ለማምጣት የእያንዳንዱ ሰው ክብር እንዲጠበቅ፣ በሰዎች መካከል የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በአሸናፊነት ለመወጣት እና አሁን የደረሱብንን የተለያዩ ችግሮች ለማስወገድ መተባበር ያስፈልጋል በማለት ያቀረቡትን ግብዣ፣ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር በመልዕክታቸው አስታውሰዋል።          

24 February 2021, 13:37