ፈልግ

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ  

ፍቅር በቤተሰ ውስጥ

ምሥጢረ ተክሊል

“መጽሐፍ ቅዱስና ትውፊት በቤተሰብ ባህርያት ስለ ተገለጠው ስለ ቅድስት ሥላሴ ምስጢር እንድናውቅ ይረዱናል፡፡ ቤተሰብ የአካላት ሱታፌ የሆነው የእግዚአብሔር አምሳል ነው፡፡ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ፣ ኢየሱስን የሚወደው ልጁ እንደ ሆነና በዚህም ፍቅር መንፈስ ቅዱስን እንደምናውቅ የተናገረው የአብ ድምጽ ተሰማ (ንጽ. ማር. 1፡ 10-11)፡፡ ሁሉን ነገር ከራሱ ጋር ያስታረቀውና እኛንም ከኃጢአት ያዳነን ኢየሱስ፣ ጋብቻንና ቤተሰብን ወደ ጥንቱ ቅርጻቸው መመለስ ብቻ ሳይሆን፣ ጋብቻን እርሱ ለቤተክርስቲያን ያለው የፍቅሩ ምሥጢራዊ ምልክት ወደ መሆን ደረጃ ከፍ አደረገው (ንጽ. ማቴ. 19፡ 1-12፤ ማር. 10፡ 1-12፤ ኤፌ. 5፡ 21-32)።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ቤተሰብ ውስጥ የቅድስት ሥላሴ ‹መልክና አምሳል› (ንጽ. ዘፍጥ. 1፡ 26) እንደገና ታደሰ፡፡ እርሱም እውነተኛ ፍቅር ሁሉ የሚመነጭበት ምሥጢር ነው፡፡ በቤተክርስቲያን አማካይነት ጋብቻና ቤተሰብ የእግዚአብሔርን የፍቅር ወንጌል ለመመስከር ይችል ዘንድ ከክርስቶስ እጅ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ይቀበላል››፡፡  

ምሥጢረ ተክሊል ማኅበራዊ ስምምነት፣ ባዶ ሥነ ሥርዓት ወይም የፈቃደኝነት ውጫዊ ምልክት ብቻ አይደለም፡፡ ምሥጢረ ተክሊል ለባልና ሚስት ቅድስናና ድኅነት የተሰጠ ስጦታ ነው፣ ምክንያቱም ‹‹ የእነርሱ የእርስ በርሳቸው መሆን፣ በምሥጢራዊ ምልክት አማካይነት፣ በክርስቶስና በቤተክርስቲያን መካከል ያለው ተመሳሳይ ግንኙነት ተጨባጭ ምሳሌ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ባለ ትዳር ጥንዶች በመስቀል ላይ የተፈጸመውን ነገር ለቤተክርስቲያን የሚዘክሩ kሚ መታሰቢያ ናቸው፡፡ እነርሱ ለእርስ በርሳቸውና ለልጆቻቸው በምሥጢሩ አማካይነት ለሚጋሩት ድኅነት ምሥክሮች ናቸው››፡፡ ጋብቻ የጋብቻ ፍቅርን ለመለማመድ የቀረበ ልዩ ጥሪ ነው፤ ይህም  በክርስቶስና በቤተክርስቲያን መካከል ያለውን ፍቅር የሚገልጽ ፍጹም ያልሆነ ምልክት ነው፡፡ በመሆኑም፣ የማግባትና ቤተሰብ የማፍራት ውሳኔ ጥሪን ለይቶ የማወቅ ሂደት ውጤት ነው፡፡

‹‹በምሥጢረ ተክሊል አማካይነት ራስን ለእርስ በርስ መሰጣጣት፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ እያንዳንዱ ሰው ከክርስቶስ ጋር መሠረታዊ ኪዳን በሚያቆምበት በጥምቀት ጸጋ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ጥንዶች እርስ በርስ በመቀባበልና በክርስቶስ ጸጋ በመደገፍ፣  ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለእርስ በርሳቸው ለመሰጣጣት፣ ለመተማመንና ለአዲስ ሕይወት ክፍት ለመሆን ቃል ይገባባሉ፡፡ ጥንዶቹ እነዚህን መሠረታዊ ነገሮች የጋብቻ አካልና እግዚአብሔር የሰጣቸው ስጦታ መሆናቸውን ተገንዝበው፣ በእግዚአብሔር ስምና በቤተክርስቲያን ፊት ለእርስ በርሳቸው ቃል ይገባባሉ፡፡ በእምነት ኃይልም የጋብቻን ሀብት በምሥጢረ ተክሊል ጸጋና ረድኤት በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ ቃል ኪዳን ይገባሉ፡፡

 በመሆኑም፣ ቤተክርስቲያን ባለ ትዳር ጥንዶችን እንደ መላ የቤተ ሰብ ልብ አድርጋ ትመለከታቸዋለች ፣ ቤተሰብ ደግሞ ወደ ኢየሱስ ይመለከታል››፡፡  ምሥጢረ ተክሊል ‹‹ዕቃ›› ወይም ‹‹ኃይል›› አይደለም፤ ምክንያቱም በምሥጢረ ተክሊል አማካይነት ክርስቶስ ራሱ ‹‹አሁን ከክርስቲያን ጥንዶች ጋር ይገናኛል… ከእነርሱም ጋር ይኖራል፣ መስቀሎቻቸውንም ተሸክመው እርሱን እንዲከተሉ፣ ከወደቁ እንዲነሡ፣ እርስ በርስ ይቅር እንዲባባሉ፣ የእርስ በርሳቸውን ሸክም እንዲሸከሙ ብርታትን ይሰጣቸዋል››፡፡ ክርስቲያናዊ ጋብቻ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በታተመው ቃል ኪዳን ቤተክርስቲያኑን ምን ያህል እንደ ወደደና ይህም ፍቅር በባልና ሚስት ሱታፌ እንዴት እንደሚገኝ የሚያሳይ ምልክት ነው፡፡ ባልና ሚስት አንድ ሥጋ በመሆናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጅ ሰብአዊ ባሕርያችንን መቀበሉን ያመለክታሉ፡፡ ለዚህም ነው ክርስቶስ ‹‹በፍቅራቸው ደስታና በቤተሰብ ሕይወታቸው ውስጥ ገና  በዚች ምድር ላይ ሳሉ የበጉን የሰርግ ግብዣ ተምሳሌት የሚሰጣቸው››፡፡ በባልና በሚስት፣ በክርስቶስና በቤተክርስቲያኑ መካከል ያለው ንጽጽር ‹‹ፍጹም ባይሆንም››፣ በእያንዳንዱ ባለ ትዳር ላይ መለኮታዊ ፍቅሩን እንዲያፈስ ጌታን እንድንለምነው ያነሣሣናል፡፡

በምሥጢረ ተክሊል የተቀደሰውና በፍቅር የሚፈጸም ወሲባዊ ግንኙነት ለባለ ትዳሮች በጸጋ ሕይወት ለማደግ መንገድ ይከፍታል፡፡ እርሱም ‹‹የጋብቻ ምሥጢር›› ነው። የእነርሱ የአካላዊ አንድነት ትርጉምና እሴት የሚገለጸው፣ ሕይወታቸውን ሙሉ ለሙሉ መጋራት ያስችላቸው ዘንድ፣ እርስ በርስ ለመቀባበላቸውና ለመሰጣጣታቸው በሚገቡአቸው የስምምነት ቃላት ነው፡፡ እነዚያ ቃላት ለወሲባዊ ግንኙነት ትርጉም ይሰጣሉ፣ ከአሻሚነትም ነጻ ያደርጉታል፡፡ በአጠቃላይ፣ የባልና ሚስት የጋራ ሕይወትና ከልጆቻቸውና በዙሪያቸው ካለው ዓለም ጋር የሚኖራቸው መላው የግንኙነት መረብ በምሥጢረ ተክሊል ጸጋ ክብርን ይጎናጸፋል፣ ይጠነክራል፡፡ ምክንያቱም፣ ምሥጢረ ተክሊል የሚመነጨው  እግዚአብሔር ከእኛ ጋር በመሆን የፍቅሩን ሙላት ለሰው ዘር ካሳየበት  ከክርስቶስ ሥጋ መልበስና ከፋሲካ ምሥጢር ነውና፡፡ በመንገዳቸው ላይ የሚገጥሙአቸውን ተግዳሮቶች ሁሉ ብቻውን የሚሸከም በባለ ትዳሮች መካከል አንድም  የለም፡፡ ሁለቱም በቁርጠኝነት፣ በፈጠራ፣ በጽናትና በዕለት ተዕለት ጥረት ለእግዚአብሔር ስጦታ ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሚገጥማቸው አዳዲስ ሁኔታ ውስጥ የእርሱ ጸጋ ይሰማ ዘንድ፣ አንድነታቸውን የቀደሰውን የመንፈስ ቅዱስን ረድኤት ምን ጊዜም መለመን ይችላሉ፡፡

በቤተክርስቲያን በላቲን ሥርዓት መሠረት፣ የምሥጢረ ተክሊል አገልጋዮች ተጋቢዎቹ ወንድና ሴት ናቸው፤ እነርሱም ስምምነታቸውን በመግለጽና በተጨባጭ በግብር በማሳየት ትልቅ ጸጋን ይቀበላሉ፡፡ የእነርሱ ስምምነትና አካላዊ አንድነት ‹‹አንድ ሥጋ›› የሚሆኑበት እግዚአብሔር የቀደሳቸው መንገዶች ናቸው፡፡ በጥምቀታቸው የጌታ አገልጋዮች ለመሆንና ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሽ ለመስጠት በጋብቻ ለመተሳሰር ችለዋል፡፡ ስለዚህ፣ ሁለት ክርስቲያን ያልሆኑ ጥንዶች ሲጠመቁ፣ የጋብቻ ቃለ መሓላቸውን ማደስ አያስፈልጋቸውም፤ ጥምቀትን በመቀበላቸው የእነርሱ አንድነት ወዲያውኑ ስለሚቀደስ ቃል ኪዳናቸውን ብቻ መተው አይገባቸውም፡፡ የቀኖና ሕግ ደግሞ ካህን አገልጋይ በሌለበት የሚፈጸሙ የአንዳንድ ጋብቻዎችን ሕጋዊነት ይቀበላል፡፡  የተፈጥሮ ሥርዐት በኢየሱስ አዳኝ ጸጋ የተሞላ በመሆኑ፣ ‹‹ ከዚህም የተነሣ ምሥጢር ሳይሆን በተጠመቁ ሰዎች መካከል  ዋጋ ያለው  የጋብቻ ስምምነት ሊኖር አይችልም››፡፡ ጋብቻ በይፋ፣ በምሥክሮች ፊት እንዲሁም ሌሎች በጊዜ  ሂደት የተለወጡ ሁኔታዎች ባሉበት እንዲከበር ቤተክርስቲያን ልትጠይቅ ትችላለች፤ ሆኖም ይህ ሁኔታ እጮኛሞቹን የምሥጢሩ አገልጋዮች ከመሆን አያስቀራቸውም፡፡ እንዲሁም በራሱ ምሥጢራዊ ትስስርን የሚመሠርተውን በወንድና በሴት መካከል የሚደረገውን የስምምነት ማዕከልነትንም አይነካውም፡፡ ነገሩ እንዲህ ከሆነ፣ በጋብቻ ሥርዓት ውስጥ የእግዚአብሔርን ሥራ ይበልጥ ማሰላሰል ያስፈልጋል፡፡ ይህም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ምልክት ይሆን ዘንድ ተጋቢዎቹ  ቡራኬ መቀበል አለባቸው በሚለው  በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓተ አምልኮ  በግልጽ ታይቶአል፡፡

27 February 2021, 11:06