ፈልግ

በጎዳና ላይ የሚኖሩ ሰዎች በቫቲካን ጸረ ኮቪድ ክትባት እየተከተቡ እንደ ሚገኙ ተገለጸ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመኖሪያ ቤት ለሌላቸው እና በጎዳና ላይ ለሚኖሩ ሰዎች በቅድስት መንበር ተቋማት ለሚደገፉ ድሆች ጽረ ኮቪድ -19 ክትባት እንዲከተቡ እድል እንዲያገኙ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የቅድስት መንበር ፕሬስ ጽ / ቤት ረቡዕ ዕለት ጥር 12/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ 24 ቤት-አልባ ሰዎች ጸረ ኮቪድ 19 ክትባት መከተባቸውን ገልጿል።

የቅድስት መንበር ፕሬስ ጽ /ቤት ዳይሬክተር ማቲዎ ብሩኒ ረቡዕ ጠዋት የተከተቡት ሰዎች ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የበጎ አድራጎት ጽ / ቤት አዘውትረው እርዳታ የሚያገኙ የሰዎች ቡድን አካል ናቸው ብለዋል። በሚቀጥሉት ቀናት ሌሎች ድሆች ክትባቱን እንደሚወስዱ አክለው ገልጸዋል።

“ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስን እናመሰግናለን!”

የመጀመሪያ ክትባቱን ከተቀበሉ መካከል አንዱ ማሪዮ ሲሆን ለቫቲካን ኒውስ በሰጠው ቃል እንደ ገለጸው አሁን “ተጨማሪ ደህንነት” እንዳገኘው ይሰማኛል ብሏል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ለክትባት ዘመቻ ከሚቀርቡት ክትባቶች አንድ ክፍል በጣም ለሚያስፈልጋቸው እንዲሰጥ ፍላጎታቸውን አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም የቅድስት መንበር ፕሬስ ጽ / ቤት ዳይሬክተር ማቲዎ ብሩኒ ረቡዕ ጠዋት ጽረ ኮቪድ 19 ክትባት የተከተቡ 24 ሰዎችን በመወከል እንደ ተናገሩት በእነዚህ 24 ሰዎች ስም “ለዚህ ስጦታ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን እናመሰግናለን” ብለዋል።

ይህ እድል የተሰጣቸው ሰዎች በቫቲካን አቅራቢያ በሚገኙ የተለያዩ ቤተክርስቲያን በሚተዳደሩባቸው ተቋማት መጠለያ እና ድጋፍ የሚያገኙ ሰዎች ናቸው። እነሱ ዕድሜያቸው ከ 60 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች እና ሴቶች ናቸው ፣ የጣሊያን ዜጎችም ሆኑ የውጭ አገር ዜጎች ፣ ብዙዎች ከከባድ የጤና ችግሮች ጋር የሚታገሉ ሰዎች ናቸው።

"ማንም ብቻውን አይድንም"

ተነሳሽነቱን የሚያስተባብረው የቅዱስ ኢጂዲዮ ማህበረሰብ ባልደረባ የሆኑት ካርሎ ሳንቶሮ በበኩላቸው “ማንም ሰው ብቻውን አይድንም” ከሚለው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ  እምነት ጋር እንደሚስማሙ ተናግረዋል።

መቀመጫውን ሮም ያደረገው የቅዱስ ኢጂዲዮ ማህበረሰብ ለድሆች አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በድሆች ላይ የደረሱ በርካታ ተጨማሪ ችግሮች ይቀረፉ ዘንድ  በቅድሚያ እጃቸውን ከዘረጉ ማሕበራት መካከል የሚገኝ ማሕበር ነው።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጽ / ቤት ሚና

በቫቲካን ክትባት እየተከተቡ ያሉትን ሰዎችን አጅበው በስፍራው የተገኙት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጽ / ቤት ዋና ኃላፊ የሆኑት ካርዲናል ኮንራድ ክራቭስኪ የተመራ ቡድን ሲሆን ይህ ጽህፈት ቤት ወረርሽኙ መከሰት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን እርዳታ ለተቸገሩ እና ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች እያቀረበ ይገኛል ፡፡ ባሳለፍነው የገና ወቅት በሮም ከተማ የሚገኙ 4000 በላይ ድሃ የሆኑ ሰዎች የቪድ -19 ቫይረስ ምርመራ እንደ ተደረገላቸው የተገለጸ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩም በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ድሃ የተባሉ አገራት ውስጥ ለሚኖሩ አቅመ ደካማ ሰዎች መድኃኒቶች ፣ ጭምብሎች እና የመተንፈሻ መሳሪያዎች  በዓለም ዙሪያ እንዲከፋፈሉ እንደ ተደረገ ይታወቃል።

21 January 2021, 12:48