በቫቲካን ብክነትን እና እምነት ማጉደልን ለማስቀረት የሚያግዝ ደንብ መውጣቱ ተነገረ።

በሮም የቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አማራር አባል እና የዓለም አቀፍ ሕግ ሊቅ የሆኑት ፕሮፌሰር ቪንቼንሶ ቡዎኖሞ ከቫቲካን ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በቫቲካን ውስጥ ብክነትን እና እምነት ማጉደልን ለማስቀረት የወጣው ደንብ የሰው አቅም እና የአገሪቱን ሃብት በተሻለ መንገድ ለመጠቀም የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በዘረጉት የተሃድሶ እቅድ መሠረት ተዘጋጅቶ የወጣው ደንብ ጥንቃቄ የተሞላበት የአራት ዓመት የሥራ ውጤት መሆኑን ፕሮፌሰር ቪንቼንሶ ገልጸው ዓላማውም የቅድስት መንበርን እና የቫቲካን መንግሥት የኤኮኖሚ ዘርፍን ዓለም አቀፍ የተግባር መመሪያዎችን በመከተል የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እና አላስፈላጊ ወጭዎችን ለማስቀረት ያለመ መሆኑን አስረድተዋል። በቅድስት መንበር ሥር የሚገኙ ጳጳሳዊ ምክር ቤቶች በተሰጣቸው ደንብ እና ሕግ በመመራት ራሳቸውን በመቻል በየፊናቸው አገልግሎታቸውን የሚያሳድጉበት መንገድ መሆኑን ፕሮፌሰር ቪንቼንሶ አክለው አስረድተዋል። የኤኮኖሚ አጠቃቀምን ጨምሮ በሌሎች በርካታ የአገልግሎት ዘርፎች የሚከናወኑት ሐዋርያዊ ተግባራት ግልጽነት እንዲኖራቸው እና ለቁጥጥር እንዲያመች በተዘጋጀላቸው መንገድ በመጓዝ የቅድስት መንበርን የሰው አቅም እና ንብረት አስተዳደር በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑ ታውቋል። የዚህ ደንብ ዋና ዓላማ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሚመሩት የተሃድሶ እቅድ ጋር አንድ በመሆን ቅድስት መንበር ለምታበረክተው ሐዋርያዊ ተልዕኮ አጋዥ እንዲሆን እና መልካም አስተዳደርን ለመዘርጋት ጠቃሚ ትምህርት ለማስጨበጥ የታሰበ መሆኑ ታውቋል።     

አዲሱን ደንብ ማውጣት ያስፈለገበት ምክንያት የቅድስት መንበርን እና የቫቲካን መንግሥት ሐዋርያዊ መመሪያዎች ከዓለም አቀፍ ግዴታዎች ጋር ተመሳሳይነት እንዲኖረው ለማድረግ መሆኑ ታውቋል። እምነት ማጉደልን ለማስቀረት በሚል ዓላማ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያጸደቀውን የሜሪዳ ውል ቅድስት መንበር እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር መስከረም 16/2016 ዓ. ም. መፈረሟ የሚታወስ ሲሆን፣ ውሉ ከዚህ በተጨማሪ የተደራጀ አገር ተሻጋሪ ወንጀልን ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑ ታውቋል።  ዓለም አቀፍ ደንቦች እና የመልካም አገልግሎት ደንቦች ሁለቱም መሠረታዊ በሆነው ኤኮናሚያዊ ርዕሠ ጉዳይ ላይ በማትኮር እና የቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮን በመከተል፣ ክርስቲያናዊ መልዕክቶች ከኤኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ጋር የሚገናኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው ተብሏል።

አዲሱ ደንብ መሠረቱን ያደረገው በቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ላይ መሆኑን ያስረዱት ፕሮፌሰር ቪንቼንሶ፣ በዚህ የተነሳ ለከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለማቃለል እንደ መሣሪያነት የሚያገልግል መሆኑን ገልጸዋል።   

04 June 2020, 19:14