ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል አዩሶ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል አዩሶ፣ 

ካርዲናል አዩሶ ዓለም ከወረርሽኙ በፊት ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ የለበትም ማለታቸው ተገለጸ።

በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል አዩሶ፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቪዲዮ ምስል አማካይነት ባሰሙት ንግግር፣ ዓለም ከወረርሽኙ በፊት ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ የለበትም ማለታቸው ታውቋል። የማኅበረሰባችን ሕይወት ከሌላው ማኅበረሰብ ሕይወት ተነጥሎ ሊታይ እንደማይቻል ተገንዝበናል ብለዋል። እርስ በእርስ ተጋግዞ መኖር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ግንቦት 6/2012 ዓ. ም. በሚደርግ ዓለም አቀፍ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ የልዩ ልዩ ሐይማኖቶች ምዕመናን እንዲሳተፉ ግብዣቸውን አቅርበዋል።

የቫቲካን ዜና፤

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን እያስጨነቀ ባለበት ባሁኑ ጊዜ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጋቢት 18/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ጸሎታቸውን ባቀረቡበት ወቅት አደባባዩ ባዶ እንደነበር ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል አዩሶ አስታውሰዋል።

“የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ሚና” በሚል ርዕሥ ንግግር ያደረጉት ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጋቢት 18/2012 ዓ. ም. በመሩት ጸሎት፣ ሁላችንም በአንድ ጀልባ ውስጥ የተሳፈርን፣ ለጥቃትም የተጋለጥን፣ የምናደርገውን አጥተን ግራ የተጋባን ብንሆንም በጋራ ሆነን፣ በመተጋገዝ የደረሰብንን መከራ ለማሸነፍ የጋራ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ማለታቸውን አስታውሰዋል። በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል ኣንገል ኣዩሶ፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባሰሙት ንግግር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን ያመጣውን መከራ ለመመከት ሦስት መሠረታዊ ርዕሠ ጉዳዮችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለው እነርሱም ሕብረትን፣ መተጋገዝን እና ወንድማማችነትን ማሳደግ ነው ብለዋል።

ሕብረት፣

የሕብረታችን እና የጋራ ውይይታችን ዋና መሠረቱ የጋራ ስብዕናችን ነው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ፣ ሁላችንም የአንድ ቤተሰብ አባል መሆናችንን ማስታወስ ይኖርብናል ብለዋል። የእያንዳንዳችን ሕይወት፣ የማኅበረሰቦቻችን ሕይወት የተገናኘ መሆኑን በመገንዘብ ከምን ጊዜም በላይ አንድነታችንን አጠናክረናል ብለው፣ ከእንግዲህ ወዲህ መለያየት የማንችል፣ አንዱ ለሌላው አስፈላጊ ነን ብለዋል። አንድነታችን የተመሠረተ በሥልጣን ወይም በገንዘብ ላይ ሳይሆን፣ ደካሞች እና በአደጋ በቀላሉ የምንጠቃ በመሆናችን በእርስ በእርስ በመተጋገዝ የተመሠረተ ነው ብለዋል።

መተጋገዝ፣

የኮሮርና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው የመከራ ጊዜ በማኅበረሰባችን መካከል መተጋገዝ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያስረዱት ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ፣ በተለይም የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች በመተባበር በችግር ውስጥ ለሚገኝ ማኅበረሰባችን እርዳታን ማድረግ ያስፈልጋል ብለው የምንገኝበት ጊዜ አንዱ ማኅበረሰብ ከሌላው ማኅበረሰብ ተነጥሎ የማይታይበት፣ ራስ ወዳድነትን እና ልዩነትን አስወግደን፣ በስቃይ ውስጥ የሚገኘውን ማኅበረሰባችንን ለመርዳት መተባበር ይኖርብናል ብለዋል። ለዚህም ትክክለኛው መንገድ በድፍረት ተነሳስተን አዲስ የእርዳታ መድረክን ማበጀት ነው ብለዋል። በዚህ መንገድ ማንም ወደ ጎን መባል የለበትም ያሉት ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ፣ ይህን ወረርሽኝ ለመከላከል ከሚደረግ ከፍተኛ የጤና አገልግሎት እና የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ማኅበረሰባችንን ያስጨነቁትን ማንኛውንም ዓይነት ኢፍትሃዊነትና ያልተመጣጠነ የሃብት ክፍፍል ለማስወገድ የሚያስችል አዲስ መሠረት መጣል ያስፈልጋል ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ ከዚህም ጋር በማያያዝ ዓለማችን ከእንግዲህ ወዲህ ከወረርሽኙ በፊት ወደ ነበረበት ሁኔታ መመልስ የለበትም ብለው አዲስና የተሻለን ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መጠቀም የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል።

ወንድማማችነት፣

የፍርሃት እና የድንቁርና ግድግዳን ማፍረስ እንድንድችል ወንድማማቾች እና እህትማማቾች መሆናችንን ማወቅ የመጀመሪያ እርምጃ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ፣ ያጋጠመን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም ለሰው ልጅ የጋራ ደህንነት መሠረታዊ የሆኑ የወዳጅነት እና የወንድማማችነት ድልድይ ለመገንባት መልካም አጋጣሚን ፈጥሮልናል ብለዋል። አንድ የሚያደርገን የወንድማማችነት መንፈስ አሁን ያጋጠመንን ችግር ለማለፍ ያግዘናል ብለዋል። ወንድማማችነትን የምንመሠርተው ከራሳችን ማኅበረሰብ፣ ከባሕላችን እና ከሐይማኖታችን ጋር ብቻ ሳይሆን ሌላውንም የሚያካትት መሆን አለበት ብለዋል።

ግንቦት 6/2012 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የጸሎት ቀን ነው፣

እርግጠኞች ባልሆንንበት ባሁኑ ጊዜ ዋናው ተልዕኮአችን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በብርሃነ ትንሳኤው መልዕክታቸው ለሮም ከተማ እና ለዓለም ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ሁሉ፣ ለዓለም በሙሉ ተስፋን ማዳረስ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ አስታውቀው፣ ለመንፈሳዊ እሴቶቻችን ምስጋና ይግባቸውና፣ የሐይማኖት መሪዎች በመተባበር ክፉኛ የተጎዳው ስብዕናችን ተመልሶ እንዲያብብ የበኩላችንን አስተዋጽዖ ማበርከት እንችላለን ብለዋል። በመሆኑም በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል አዩሶ፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባሰሙት የቪዲዮ መልዕክታቸው፣ የልዩ ልዩ ሐይማኖት ተከታዮች ግንቦት 6/2012 ዓ. ም. በሚደረግ ዓለም አቀፍ የጾም እና የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲተባበሩ ጠይቀው፣ በሰው ልጆች ላይ የደረሰውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እግዚአብሔር በሃይሉ እንዲያስወግደው ጸሎታችንን እናቀርባለን ብለዋል። አሁን የምንገኝበትን እና ወደ ፊት የሚያጋጥሙንን ችግሮች በጋራ ሆነን መከላከል እንድንችል የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች አንድነታችንን፣ መተጋገዝን እና ወንድማማችነትን በማጠንከር፣ በጋራ ለመጸለይ ተጠርተናል በማለት፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል አዩሶ መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል።

ይህን ዜና በድምጽ ማድመጥ ከፈለጉ የተጫወት ምልክትን ይጫኑ፣
13 May 2020, 13:44