በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣              በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣  

ፓውሎ ሩፊኒ፣ ማኅበራዊ መገናኛዎች በሕዝቦች መካከል ወዳጅነትን ሊዘሩ የሚችሉ መሆኑን አስታወቁ።

የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ ማኅበራዊ መገናኛዎች እና የመረጃ አገልግሎቶች ሰብዓዊ ወንድማማችነትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተቃጽዖን ሊያበረክቱ የሚችሉ መሆኑን አስታወቁ። ክቡር አቶ ሩፊኒ ይህን ያስታወቁት ሰኞ ጥር 25/2012 ዓ. ም. በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ አቡ ዳቢ ከተማ ከጸደቀ አንደኛ ዓመቱን ያስቆጠረውን የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ መታሰቢያን አስመልክቶ በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሕዝቦች መካከል የሰላምን እና አብሮ የመኖርን ባሕል ለማሳደግ የሚያግዙ ሃሳቦችን የያዘው የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ የጸደቀው፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በአቡ ዳቢ ከተማ የዓለም ልዩ ልዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች በተገኙበት ጉባኤ ላይ፣ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም በሆኑት በአህመድ አል ጣይብ መካከል በተደረገው ስምምነት መሆኑ ይታወሳል።

የብዙሃን መገናኛ ተጠቃሚ ዋና ተግባር ሰላም፣ ፍትሕን እና ማሕበራዊ ደህንነትን ለማሳደግ የሚያግዙ እሴቶችን ተንከባክቦ በማቆየት ወደ ሌሎች ሰዎች ዘንድ ማዳረስ ነው በማለት ክቡር አቶ ሩፊኒ አስረድተዋል። ወንድማማችነት ትጋትን እና ድፍረትን ይጠይቃል ያሉት ክቡር አቶ ሩፊኒ በሕዝቦች መካከል የሚታዩትን ልዩነቶች መቀበልን ይጠይቃል ብለዋል። አቶ ሩፊኒ በማከልም ወንድማማችነትን መገንባት ፍጥረትን ከጉዳት በመከላከል የተፈጥሮ ሃብትን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለተጠቃሚ ማሕበረሰብ ማዳረስን ይጠቃል ብለው፣ ሕይወትን ከተወለደበት ዕለት አንስቶ እስከ ዕለተ ህልፈቱ ድረስ አስፈላጊውን ክብር ጥበቃን እና እንክብካቤ ማድረግን ይጠይቃል ብለዋል። አቶ ሩፊኒ ከዚህ ጋር በማያያዝ ሐይማኖትን እንደ አመጽ እና ጥላቻ መቀስቀሻ መሣሪያነት መጠቀም መወገዝ አለበት ብለዋል።

ሰላማዊ ዓለምን ለመገንባት ማሕበራዊ መገናኛ ወሳኝ ነው፣

በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በአቡ ዳቢ ከተማ የተዘጋጀው ጉባኤ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም በሆኑት በአህመድ አል ጣይብ መካከል የተፈረመውን የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ አንደኛ ዓመት ለማስታወስ ብቻ ሳይሆን በሰብዓዊ ወንድማማችነት ላይ ሃሳባቸውን የሚያካፍሉ እና ምስክርነትን የሚሰጡ ግለ ሰቦች እና ዳኞች መገኘታቸውን የገለጹት አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ በፓክስታን የአነስተኛ ብድር ተቋም ልኡክ የሆኑን ሞሐመድ ሳኪብ እንደ ምሳሌ ጠቅሰው ግለሰቡ በአገራቸው ውስጥ በድህነት ሕይወት ለሚገኙ ዜጎች የብድር ተቋሙ የሚያዘጋጀውን መልካም ዕድል አስታውሰዋል። በጉባኤው ላይ ምስክርነታቸውን የሰጡትን ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ቤርተለሜዎስን ጨምሮ ከተለያዩ ሰዎች በኩል የቀረቡት ምስክርነቶች የሚያስረዱት የሰብዓዊ ወንድማማችነት ዓላማ አንድ ግዙፍ የሐኃይማኖት ተቋምን ለመመስረት ሳይሆን የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት የራሳቸውን የማንነት መገለጫዎች በመጠበቅ የጋራ ውይይቶችን ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

ከአረብ አገሮች የተወጣጡ የማኅበራዊ መገናኛ ተቋማት ጋዜጠኞችን ያሳተፈው ጉባኤ አዲስ አንቀጽን ማውጣቱን የተናገሩት ክቡር አቶ ፖውሎ ሩፊኒ፣ አንቀጹ የእያንዳንዱን አገር የጋዜጠኛ መመሪያ ደንብን፣ ሐይማኖትን እና እምነትን የሚያገናዝብ ነው ብለዋል። ይህም አንድ ጋዘጤኛ የሚሰበስባቸው መረጃዎች በእውነት ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ለማድረግ እና በማሕበርሰብ መካከል ሊቀሰቀስ የሚችለውን አምጽ እና ጦርነት ለማስወገድ ያግዛል ብለው፣ ይህ በመረጃ ስርጭት ላይ የሚደረግ ጥንቃቄ ወይም የመገናኛ ዘዴ ሰላማዊ ዓለምን ለመገንባት፣ በሕዝቦች መካከል እውነተኛ የጋራ ውይይት እንዲኖር የሚያግዝ መሆኑን አቶ ፓውሎ ሩፊኒ አስረድተዋል።

ለጉባኤው ባሰሙበት ንግግር የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን መልዕክት ያስታወሱት ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ ቅዱስነታቸው ለሌሎች የምናስተላልፈው መልዕክት የቀድሞ አባቶቻችን የተናገሩትን፣ አያቶቻችን እና ወላጆቻችን ያስተማሩትን የባሕል እሴቶች ስለሆነ ለሌሎችም እንድናካፍል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አደራ ማለታቸውን አስታውሰዋል። ነገር ግን ዛሬ ላይ ከማሕበራዊ መገናኛ መሣሪያዎች የምንሰማቸው፣ የምናነባቸው እና ለሌሎች የምናወራቸው ወሬዎች ግላዊ ሳይሆን ማህበራዊ ማንነት የሚፈጥሩብን መሆኑን አስረድተው፣ በመሆኑን ከማህበራዊ መገናኛ መሣሪያዎች ለምናገኘው ዘገባ ወይም መረጃ እውነተኛነቱን ፈልገን ማግኘት ይኖርብናል በማለት የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ አሳስበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
05 February 2020, 14:57