ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ 

ካርዲናል ታርክሰን፣ “እውነተኛ ለውጥ፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር በመቀበል ነው”።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን ሰኞ የካቲት 16/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት በሕይወታችን ውስጥ እውነተኛ ለውጥ ማምጣት የምንችለው የእግዚአብሔርን ፍቅር ስንቀበል ነው ብለዋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር መሠረት፣ የላቲን ሥርዓተ አምልኮን ለምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምእመናን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያስተላለፉትን የ2020 ዓ. ም. የዐብይ ጾም መልእክት በማስመልከት፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን ባደረጉት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲሁም ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ፍሬያማ ውይይት ሊደረግ የሚችለው በጸሎት እና ምሕረትን በማድረግ መሆኑን አስገንዝበዋል። የብርሃነ ትንሳኤውን ክብረ በዓል ለማክበር ልብን ማደስ፣ ትንሳኤውን ምስጢር በልባችን በማሰላሰል እና ለኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ዜና ምላሽ በመስጠት መሆኑን በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን አስረድተዋል።

ግልጽ እና ፍሬያማ ውይይት ሊኖር ይገባል፣

በሕይወት መካከል ለውጥ የሚመጣው ከእግዚአብሔር በጸሎት በመገናኘት፣ የእርሱን ፍቅር በመረዳት፣ ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ታማኝ፣ ግልጽ እና ፍሬያማ ውይይትን በማድረግ ነው ብለዋል። ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነትን ማበጀት የሚቻለው በጸሎት እንደተሆነ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን፣ በዓለማችን ውስጥ በስቃይ ውስጥ ለሚገኙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ምልክት የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ስቃይ ምስጢር በማስታወስ፣ እንዲሁም እርስ በርስ ይቅርታን መደራረግ እና ምሕረትን በማድረግ መሆኑን አስረድተዋል። ለሌሎች መጨነቅ ማለት ይቅርታን ማድረግ፣ የራስን እና የሌላውን ድክመት መቀበል መሆኑን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን፣ በዛሬው ማሕበረሰባችን መካከል የብቸኝነት ሕይወት የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱ በሰዎች መካከል ሊኖር የሚገባውን የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት ሕይወት እያዳከመ መምጣቱን አስታውሰዋል።              

የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ስቃይ መመልከት፣

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ክርስቶስ ሕያው ነው” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በማስታወስ ዘንድሮ ባስተላለፉት የዓቢይ ጾም ወቅት መልዕክት፣ ምዕመናን ዓይኖቻቸውን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በመመለስ፣ ከእርሱ የሚገኘውን ድነት መቀበል ያስፈልጋል ማለታቸውን የጠቀሱት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት ክቡር አባ ብሩኖ ማርያ ዱፌ በበኩላቸው ቅዱስ መስቀልን መመልከት የእግዚአብሔርን ምሕረት፣ ትዕግስት እና ርህራሄን እንደሚያስታውሰን ገልጸው ፣ እኛም የሌሎች ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ስቃይ በመገንዘብ ፣ ምሕረትን፣ ይቅርታን እና ርህራሄን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።      

ሃብትን መጋራት፣

በሕጻኑ ኢየሱስ ስም የሚጠራ የሕጻናት ሆስፕታል ፕሬዚደንት ወይዘሮ ማሪዬላ ኤኖክ የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን የዓብይ ጾም መልዕክት በሠረት በማድረግ እንዳስረዱት፣ የመልዕክታቸው ሌላው ጭብጥ፣ ሰዎች ያላቸውን የሃብት እና የእውቀት ጸጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በማከማቸት ላይ ብቻ ከማትኮር በድህነት ሕይወት ውስጥ ከሚገኙ የዓለማችን ሰዎች ጋር መካፈል ወይም መጋራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ይህም እርሳቸው ለሚሰሩበት ሆስፒታል ሁለት ከፍተኛ ስጦታዎችን ያስገኛል ብለው የመጀመሪያው በከባድ ሕመም ለሚሰቃዩ በቂ እና ፍሬያማ የሕክምና አገልግሎት ማቅረብ የሚያስችል ሳይንሳዊ ዕውቀትን ማበርከት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የህን የዕውቀት ጸጋን ለሕጻናት እና ለወላጆቻቸው በተግባር ማዳረስ መቻል ነው ብለዋል። ቀጣይነት ያላቸውን ሳይንሳዊ ምርምሮች ማካሄድ ማለት ከምርምር የሚገኙ ውጤቶችን በተለያዩ ማሕበራዊ መገናኛዎች አሳውቆ ማብቃት ሳይሆን፣ የተገኘውን መልካም ውጤት ወደ ሌሎች ማዳረስ እና ከሕመማቸው መፈወስ መሆኑን ወይዘሮ ኤኖክ አስረድተዋል።

በሮም የሕጻናት ሆስፕታል ፕሬዚደንት የሆኑት ወይዘሮ ማሪዬላ ኤኖክ ከዚህም ጋር በማያያዝ፣ በጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር መሠረት፣ የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዛሬ ርቡዕ የካቲት 18/2012 ዓ. ም. የሚፈጸመውን የዓብይ ጾም መግቢያን የሚያስታውስ የአመድ መቀባት ሥነ ሥርዓት፣ ሮም ከተማ አቅራቢያ ለሚገኙ መንደሮች የሚያዳርስ የሕክምና ባለሞያ የተላከ መሆኑን አስታውቀዋል። ዓላማውም ሥነ ሥርዓቱን መፈጸም ብቻ ሳይሆን ከማሕበረሰቡ ጋር አብሮ ማደግን እና የምሕረት ጸጋን ከሌሎች ወንድሞች እና እህቶች ጋር መጋራት መሆኑን አስረድተዋል። ባሁኑ ወቅት በሮም እና በሌሎችም የጣሊያን ክፍላተ ሃገራት በሚገኙት የሕጻኑ ኢየሱስ ሆስፒታል ቀዳሚ ተግባር፣ የዓለማችን ስጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለማስቆም በመደረግ ላይ የሚገኝ ጥረት ነው ብለዋል። በሕጻናት ሆስፒታል እስካሁን የበሽታው ምልክት ያልታየ ቢሆንም፣ ሆስፒታሉ የበሽታው ምልክት የታየባቸውን ሕጻናት፣ በሀገሪቱ ወደሚገኝ የተላላፊ በሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ለማዛወር ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።

ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመግታት የሚያደርገው ጥረት፣

የኮሮና ቫይረ ስርጭትን ለመቆጣጠር የሚደረግ ጥረት ለማገዝ ጽሕፈት ቤታቸው ዝግጁ መሆኑን የገለጹት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ በሕክምና አሰጣጥ ሥርዓት ደካማ የሆኑ አገሮች መኖራቸውን አስታውሰዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን በማከልም በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገር ስብከቶች መካከል አንዳንዶቹ የመስዋዕተ ቅዳሴን ሥነ ሥርዓት ለተወሰነ ጊዜ ለማቋረጥ ቢገደዱም ይህም ኮሮና ቫይረስን የመሰሉ አስጊ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ ከሚወሰዱ እርምጃዎች መካከል አንዱ እና የተለመደ መሆኑን አስረድተዋል። ከመፍትሄውች መካከልም አንዱ በርካታ ምዕመናን በሚሰበሰቡበት ሀገረ ስብከቶች፣ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ በአንድ ጊዜ የሚሰበሰበውን በርካታ የምዕመናን ቁጥር መቀነስ መሆኑን አስረድተው ሕዝብን በማስተባበር እና የተለያዩ በረጃዎችን በማዳረስ የብዙሃን መገናኛዎች ሚና ከፍተኛ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
26 February 2020, 18:40