የጋራ ሲምፖዚዬም፤ የጋራ ሲምፖዚዬም፤ 

በቫቲካን የቅድስት መንበር እና የአሜሪካ መንግሥት የጋራ ሲምፖዚዬም ተካሄደ።

ሰብዓዊ ክብርን ለማረጋገጥ የሚያግዙ መንገዶችን የሚያፈላልግ የአንድ ቀን ሲምፖዚዬም በቫቲካን ውስጥ መካሄዱን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል። በመስከረም 21/2012 ዓ. ም. የተካሄደውን ሲምፖዚዬም በሕብረት ሆነው ያዘጋጁት የቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እና በቅድስት መንበር የአሜርካን ኤምባሲ መሆናቸው ታውቋል። ሲምፖዚዬሙ ሰብዓዊ ክብርን ለማረጋገጥ በሚደረግ ጥረት ሐይማኖታዊ ተቋማት ሊያበረክቱት የሚችሉት አስተዋጽዖ ከፍተኛ እንደሆነም አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በ1976 ዓ. ም. በቅድስት መንበር እና በአሜሪካ መንግሥት መካከል መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መመስረታቸው ይታወሳል።

ሲምፖዚዬሙን በንንግር የከፈቱት፣ በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር በሁለቱ መንግሥታት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተመሠረተ 35 ዓመታት መቆጠራቸውንም አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ2007 ዓ. ም. በአሜሪካ ባደረጉት ሐዋርያዊኝታቸው ወቅት የተናገሩትን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር “የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ዓላማ ተቻችሎ እና አብሮ የሚኖር ማሕበረሰብን መገንባት ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

የእምነት ነጻነት፣

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር በንግግራቸው    በተባበሩት አረብ ኤምረቶች፣ በአቡ ዳቢ ከተማ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም አህመድ አል ጣይብ በሕብረት ሆነው “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” የሚል ሰነድ አስድቀው ይፋ ማድረጋቸውን አስታውሰው የጸደቀው ሰነድም ሃይማኖቶች በጭራሽ ጦርነትን ፣ የጥላቻ አመለካከቶችን እና አክራሪነትን ማስነሳት እንደሌለባቸው፣ እነዚህ አሳዛኝ እውነታዎች ከሃይማኖታዊ ትምህርቶች የተለዩ መሆናቸውን የሚጠቅስ መሆኑን ገልጸዋል። ሰነዱ በማከልም በዓለም የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ሕብረት እና በጎ ፈቃድ ባለው ሕዝብ በመታገዝ የመቻቻል፣ የወንድማማችነት እና የብዝሃነት ባሕልን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ማሳሰቡንም ተናግረዋል።  

ሰብዓዊ መብቶችን ማስጠበቅ፣

የእምነት ነጻነት መሠረታዊ ትኩረት ፖለቲካዊ ወይም ርዕዮተ ዓለማዊ አይደለም ያሉት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር ዋና ዓላማው ሰብአዊ መብቶችን እና መሰረታዊ ነፃነቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠበቅ እና በሰላም አብሮ መኖርን እና ሰዎች እምነታቸውን በነፃነት መግለጽ የሚችሉባቸውን ማህበረሰቦች ማጎልበት መሆን አለበት ብለዋል።

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መግታት፣

ቅድስት መንበር እና በቅድስት መንበር የአሜሪካ ኤምባሲ በጋራ ባዘጋጁት ሲምፖዚዬም ላይ የተነሳው ሌላው የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚመለከት ሲሆን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር “በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ውስጥ ከሚታዩ በጣም አስከፊ እውነታዎች መካከል አንዱ ነው” ያሉትን ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መዋጋት የሚቻለው ሐይማኖታዊ ተቋማትን በማሳተፍ ነው ብለዋል። የሲምፖዚዬሙ ተካፋዮችም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑትን መልሶ በማቋቋም፣ ነጻ በማውጣት፣ ወደ ማሕበረሰቡ መካከል ገብተው መደበኛ ኑሮን እንዲጀምሩ በመርዳት ላይ የሚገኙ ካቶሊካዊ ድርጅቶች መሆናቸው ታውቋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር ይህን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመዋጋት እና ከጊዜ በኋላም ለመርታት ተገቢ ውሳኔዎች የሚያደርጉ ቆራጥ መሪዎች እንዲኖሩን ያስፈልጋል ብለዋል።

ሰብዓዊ ክብርን ማስጠበቅ፣

በቫቲካን በተዘጋጀው ሲምፖዚዬም ላይ የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ አቶ ሚካኤል ፖምፔዎ የተገኙ መሆናቸው ታውቋል። ሰብዓዊ ክብርን ማስከበር በማስመልከት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር፣ በዘመናችን ሰብዓዊ ክብርን በማስመልከት የሚነሱ ርዕሠ ጉዳዮች ከቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜም እጅግ ከፍተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ይህም የሆነበት የተለያዩ እና እጅግ በርካታ የሆኑ አመለካከቶች በመኖራቸው ምክንያት ነው ብለዋል። ለምሳሌ ከሃይማኖት ጭቆና መነሻዎች መካከል አንዱ ከራሳቸው ሃይል እና ስልጣን የበለጠ አካል የለም የሚሉ አምባ ገነናዊ መንግሥታት በመኖራቸው ነው ብለዋል። ስለዚህ እነዚህን ሞራላዊ ግዴታዎቻችንን በመጠቀም መዋጋት ያስፈልጋል ብለዋል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ አቶ ሚካኤል ፖምፔዎ አያያዘውም መሠረታዊ ጉዳይ የሚሆነው ሰብአዊ ክብርን እና የሃይማኖት ነፃነት ከዕለታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ በላይ አሻግሮ መመልከት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሐይማኖታዊ ድርጅቶችን ማሳተፍ፣

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በሲምፖዚዬሙ መዝጊያ ላይ ባሰሙት ንግግር፣ የዘመናችን አስከፊ ማሕበራዊ ችግር የሆነውን ሕገ ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀልን በመዋጋት ላይ የሚገኙ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበርን፣ በስደት ላይ ለሚገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍን የሚሰጥ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽንን፣ የአዲያን ፋውንዴሽንን፣ አቪስ ፋውንዴሽን፣ ካሪታስ ኢንተርናሲዮናሊስን እና ታሊታ ኩምን አመስግነዋቸዋል።

ዓለም አቀፍ ፈተናዎች፣

ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በንግግራቸው ሰላም፣ ሰብዓዊ ክብር፣ ማሕበራዊ ፍትህ፣ ድህነትን መዋጋት፣ ዘላቂ ዕድገትን ማምጣት በዘመናችን ያጋጠሙን ችግሮች ናቸው ብለው ለተግባራዊነታቸው መንግሥታት እና ሐይማኖታዊ ድርጅቶች ተባብረው መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። በእምነት ነጻነት እና በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ትኩርትን ሰጥተው የተናገሩት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በማከልም እነዚህም ከታላላቅ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች መካከል ጥቂቶቹ ሆነው የቆዩ ናቸው ብለዋል።

“የሕሊና ነፃነትን መውሰድ የአምልኮ ነፃነትን ለማስወገድ የመጀመሪያው እርምጃ ነው” ያሉትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግር የጠቀሱት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ፈተናዎች በቁጥር በርካታ እና ከባድም መሆናቸውን ገልጸው ግን በእምነት እና በቁርጠኝነት ልንጋፈጣቸው ያስፈልጋል ብለዋል። ሰብዓዊ ክብርን ለማሳደግ ጥረት በምናደርግበት ጊዜ እግዚ አብሔር ከእኛ ጋር እንዳለ እናውቃለን ብለዋል።

የሰብዓዊ ክብር ማረጋገጫ መንገዶች፣

“የሰብዓዊ ክብር ማረጋገጫ መንገዶች” በሚል ርዕስ በቫቲካን በተዘጋጀው ሲምፖዚዬም ላይ ተካፋይ የነበሩት፣ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ጉዳይ ተጠሪ የሆኑት አምባሳደር አቶ ሳም ብራውን ባክ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት የሃይማኖት ነፃነትን ለማስከበር በሚደረግ ጥረት አከባቢያዊ ማህበረሰቦች ሊጫወቱ የሚችሉት ሚና ሰፊ እንደሆነ ገልጸው፣ አንደኛው መንገድ “ሕግ አውጪዎችዎ የሃይማኖት ነፃነትን እንዲደግፉ ማስገደድ ነው” ብለው በማከልም በኢራቅ ውስጥ የወደሙ አብያተ ክርስቲያናትን መልሶ ለመገንባት በቁምስናዎች በኩል የተደረጉ አንዳንድ ጥረቶችን እና መከራ የደረሰባቸውን በቤታቸው ተቀብለው ያደረጉትን መስተንግዶ እንደ አብይ ምሳሌ መውሰድ መልካም ነው ብለዋል።

ሰማይን እና ምድርን የሚያንቀሳቅስ ሃይል፣

አምባሳደር አቶ ሳም ብራውን ባክ “በቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚደት ሮናልድ ሬገን ስምምነት ተመስርቶ በቅድስት መንበር እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ለ35 ዓመታት የዘለቀው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ እነዚህ ሁለቱ መንግሥታት በአንዳንድ አንገብጋቢ በሆኑ ማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ ተባብረው በሚሰሩበት ጊዜ ውጤታማ የሆኑ ሥራዎችን ማከናወን ይችላሉ” ብለዋል።

03 October 2019, 17:25