ብጹዕ ካርዲናል ሎሬንዞ ባልዲሴሪ ለጉባኤው ተካፋዮች ንግግር ሲያደርጉ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሎሬንዞ ባልዲሴሪ ለጉባኤው ተካፋዮች ንግግር ሲያደርጉ፣ 

ብጹዕ ካርዲናል ሎሬንዞ ባልዳሴሪ፥ “በመንፈስ ቅዱስ በመመራት በአዲስ ጎዳና እንራመዳለን”።

የመላዋ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሎሬንዞ ባልዲሴሪ ዛሬ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ ለተጀመረው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ባደረጉት ንግግር፣ በመንፈስ ቅዱስ በመታገዝ ቤተክርስቲያን የምትጓዝባቸውን አዳዲስ መንገዶችን ማግኘት እንፈልጋለን ብለዋል።

በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሁለት ዓላማ አለው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሎሬንዞ ባልዲሴሪ በአካባቢው አገሮች የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአካባቢ አገሮች ባሕልን ያማከለ የወንጌል ተልዕኮን በፍሬያማነት የምትፈጽምበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሆነ ገልጸው በሁለተኛ ጎኑ ሲኖዶሱ የተፈጥሮ መዛባት በአካባቢ አገሮች ላይ እያስከተለ ያለውን አደጋ ምላሽ ለመስጠት ስነ ምሕዳራዊ  መፍትሄዎችን ማፈላለግ እንደሆነ አስረድተዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ሎሬንዞ ባልዲሴሪ፥ ለረጅም ዘመናት ተረስቶ ለቆየው እና ያለ ምንም የወደፊት ዓላማ እየኖረ ለሚገኝ የአማዞን አካባቢ አገሮች የእግዚአብሔር ሕዝብ በተለይም ነባር የአካባቢው ሕዝብ የወንጌልን መልካም ዜና ለማዳረስ እና እነዚህ ሕዝቦች በሚኖሩበት አካባቢ ደኖች ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለመከላከል እና ይህ አካባቢ ለምንኖርባት ምድራችን እያበረከተ ያለውን ጠቀሜታ ለሌላው ዓለምም ለማስገንዘብ መሆኑን አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ሎሬንዞ ባልዲሴሪ በማከልም የአማዞን ደን አካባቢ አገሮች የተወሰነውን አካባቢ ብቻ የሚያካልል ቢሆንም በቫቲካን በመካሄድ ላይ የሚገኘው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን የሚመለከት ነው ብለው፣ በመሆኑም በመላው ደቡብ አሜሪካ አገሮች የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት፣ በአህጉሩ የሚገኙ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮችም የሚካፈሉበት ነው ብለዋል። ካርዲናል ባልዳሰሪ በማከልም መላዋ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን በአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ እና ችግር የራሷ አድርጋ በመቁጠር የሚጠበቅባትን እርዳታ ለማድረግ ትፈልጋለች ብለዋል። 

ብጹዕ ካርዲናል ሎሬንዞ ባልዲሴሪ ለጉባኤው ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር ጉባኤውን የሚካፈሉ አባላትን ቁጥር ሲያስታውሱን 185 የሲኖዶሱ አባቶች፣ 6 የሌሎች ሐይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ 12 ሲኖዶሱን እንዲካፈሉ ልዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ 25 የስነ ምሕዳር ጠበብት፣ 55 ጉባኤውን በአድማጭነት የሚሳተፉ እና በተለያዩ የአማዞን ግዛቶች ውስጥ በሐዋርያዊ እረኝነት አገልግሎት የተሰማሩ እንግዶች፣ ከእነዚህም መካከል 16 በአካባቢው አገሮች የሚገኙ የተለያዩ ሕዝቦች እና ባሕሎች የሚወክሉ ጎሳ መሪዎች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥቅምት 5/2010 ዓ. ም. ባደረጉት ውሳኔ መሠረት መሆኑን ገልጸው ወይይት የሚደረጉባቸው በርካታ ርዕሠ ጉዳዮች የሚያፈልቁት ጠቃሚ ሃሳቦችን መሠረት በማድረግ ይፋ በሚደረገው ጠቅላላ ሰንድ ዝግጅት የሚጠቃለል መሆኑን አስታውቀዋል።

ሲኖዶሱ የተለመደውን የሲኖዶስ አካሄድ የተከተለ የጠቅላላ ምክር ቤት ጉባኤዎች የሚኖሩት መሆኑን የገለጹት የመላዋ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሎሬንዞ ባልዲሴሪ፣ ከዚህም በተጨማሪ ሃሳቦች የምንሸራሸሩባቸው መለስተኛ የቡድን ውይይቶች ከመስከረም 29 ጀምሮ የሚኖሩ መሆናቸው አስረድተዋል። በእነዚህ የውይይት መድረኮች ላይ ከተለያዩ የሲኖዶሱ ተካፋዮች የሚቀርቡ ገንቢ ሃሳቦች ተሰባስበው አንድ ጠቅላላ ሰነድ ሰኞ ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ. ም. ይፋ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል። ቅዳሜ ጥቅምት 15/2012 ዓ. ም. በቀረበው ስነድ ላይ ድምጽ የሚሰጥበት እና የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ መዝጊያ ስነ ስርዓት የሚካሄድ መሆኑን አስረድተዋል። 

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ሎሬንዞ ባልዲሴሪ አክለውም የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ እና የቅድስት መንበት ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ የሲኖዶሱን ሂደት በመከታተል እለታዊ  መግለጫዎችን የሚሰጡ መሆናቸውንም ገልጸዋል። በእነዚህ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ የጉባኤው ተካፋይ አባቶች እና ሌሎች ተሳታፊዎችም የሚገኙ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ከዚህም በተጨማሪ የሲኖዶሱ አባቶች ከጉባኤው ማዕከል ውጭ ከተለያዩ ብዙሃን መገናኛ ተቋማት ጋር ቃለ ምልልስ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ሎሬንዞ ባልዲሴሪ አክለውም በጉባኤው ወቅት የጉባኤው ተሳታፊዎች ምንም ዓይነት የላስቲክ ውጤቶችን እንደ መገልገያ የማይጠቀሙ መሆናቸውን ገልጸው የሚጠቀሟቸው ቁሳቁሶች በሙሉ ከአፈር ጋር በቀላሉ ሊዋሃዱ የሚችሉ መሆናቸውን አስረድተው ይህም ለምንኖርባት የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን ከውድመት ለማዳን ተብሎ የሚካሄደውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ቀዳሚ ዓላማን ለማንጸባረቅ ተብሎ የተደረገ ነው ብለዋል።               

07 October 2019, 18:22