የአማዞን ደን ውስጥ ነዋሪዎች፣ የአማዞን ደን ውስጥ ነዋሪዎች፣ 

ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ ሕዝቦች ያለ ልዩነት አብረው መጓዝ እንዳለባቸው አሳሰቡ።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ በቫቲካን ውስጥ ከመስከረም 26/2012 ዓ. ም. ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘውን የአማዞን አካባቢ አገሮች ልዩ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት በማሕበራዊ ሕይወት መካከል ማንንም ማግለል ወይም ወደኋላ መተው እንደማያስፈልግ አሳስበዋል። ካርዲናል ታርክሰን ይህን መልዕክት ያስተላለፉት በቫቲካን በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአማዞን አካባቢ አገሮች ልዩ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የሕዝቦችን ሁለንተናዊ እድገት በሚመለከቱ ርዕሰ ጉድዮች ላይ ውይይት በጀመረበት ጊዜ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ2009 ዓ. ም. የአማዞን አካባቢ አገሮችን የሚያሳትፍ የጳጳሳት ሲኖዶስ እንዲካሄድ በማለት ሃሳብ ባቀረቡበት ወቅት ዋና ዓላማቸው ሰፊው የአማዞን ደን በሚያካልላቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የተቀናጀ የወንጌል አገልግሎትን ለማዳረስ እና በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኘው ደን ላይ እየደረሰ ያለውን ውድመት በመከላከል ለአካባቢው ነዋሪ ሕዝብ እና ለመላው ዓለም የጤናማ ሕይወት ተስፋን ለመስጠት በመፈለጋቸው መሆኑ ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን ለቫቲካን ሬዲዮ እንዳስረዱት አሁን በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የአማዞን አካባቢ አገሮች የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስን ዕቅድ እና እንቅስቃሴን ጽሕፈት ቤታቸው ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ሲከታተለው የቆየ መሆኑን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ከአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ጋር ሲያደርጉ የነበሩትን ውይይቶች ጽሕፈት ቤታቸው ከመጀመሪያው ጀምሮ በቅርብ ሲከታተል መቆየቱን ካርዲናል ፒተር ታርክሰን ተናግረዋል።

ከአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ጋር የተደረጉት ውይይቶች በሦስት አበይት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን እነርሱም የመሬት ባለቤትነት፣ የመኖሪያ ቤት እና የሥራ ዕድል መሆናቸውን ገልጸዋል። በቫቲካን በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስም በይፋ የሚወያይባቸው ርዕሠ ጉዳዮች፣ ብዙን ጊዜ በአማዞን ደን ውስጥ ተረስተው ለቀሩት ቀደምት ነዋሪዎች ሊደረግላቸው ስለሚገባ ሐዋርያዊ እና ማሕበራዊ አገልግሎቶች እንደሆነ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን ገልጸው፣ የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች የሚፈልጉትም የመሬት ባለቤትነት ዋስትና፣ የሥራ ዕድል እና ሰቦኣዊ ክብራቸውን ማስጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል። እነዚህ ርዕሠ ጉዳዮችን በተመለከተ የቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት በአማዞን አካባቢ አገሮች ከሚገኙ ዘጠኝ አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመተባበር ሲሰሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል።

ከእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ጋር የተደረገ የጋራ አገልግሎት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከፍተኛ ድጋፍ እና ብርታት የተሰጠው መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን ገልጸዋል። በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የዘላቂ ሂደት አካል ነው ብለው ሲኖዶሱ ሂደቱን እየተከተለ መሆኑን እና እስከ ዛሬ ድረስ ለታዩት እድገቶች ከፍተኛ ፍላጎት እንዳደረባቸው ገልጸው ሲኖዶሱ መካሄዱ የመጨረሻ ግብ እንዳልሆነ አሳስበዋል።

በቫቲካን በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በበርካታ ሐዋርያዊ እና ማሕበራዊ አገልግሎቶች ላይ ሰፊ ውይይቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤታቸው የሐዋርያዊ አገልግሎት ጥያቄያቸውን ለመመለስ ጥረት ያደረገ ቢሆንም ሌሎች ፍላጎቶቻቸውንም መረዳት አስፈላጊ መሆኑን ተናገረዋል። ካርዲናል ፒተር ታርክሰን በማከልም የአማዞን አካባቢ አገሮች ቀደምት ነዋሪዎች ባህላቸውን እና ቅርሶቻቸውን መጠበቅ እና መንከባከብ መልካም ቢሆንም የአማዞን ክልል እንደ ሙዝየም ሊቆጠር አይገባም ብለው የአማዞን አካባቢ ሕዝቦች ከሌላው ዓለም ጋር እንዲገናኝ  መርዳት ያስፈልጋል ብለዋል።

በማሕበራዊ ሕይወት ማንም መገለል የለበትም፣

በላቲን አሜሪካ የአማዞን ደን በሚያካልላቸው በብራዚል፣ በቦሊቪያ፣ በፔሩ፣ በኤኳዶር፣ በኮሎምቢያ፣ በቬነዙዌላ፣ በጉያና እና በሱሪናም ግዛቶችን የሚኖሩ ሕዝቦችን ወደ ዘመናዊነት ብልጽግና ማሸጋገር ያስፈልጋል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን የአማዞን አካባቢ ሕዝቦች ከዓለም አቀፍ የዕድገት ጎዳና ተለይተው ብቻቸውን መቅረት የለባቸውም ብለው ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለአካባቢው ሕዝቦች ለማቅረብ የወጠነችው የሐዋርያዊ አገልግሎት ንድፍ የሕዝቦችን ማሕበራዊ እና ቁሳዊ ዕድገቶችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ወደ ዘመናዊነት ለማሸጋገር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን ይህን በተመለከተ ባሁኑ ጊዜ የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች የፀሐይ ኃይልን እና ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ምርጫ መኖሩን ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የአማዞን አካባቢ ሕዝቦች ባሕል ባከበረ መልኩ እድገትን እና ማሕበራዊ ጥቅምን እንዲጋሩ የሚያደርጉ የእድገት አቅጣጫዎችን በማስተዋወቅ ሕዝቡን ከችግር፣ ከድህነት እና ከድንቁርና ማውጣት የሚቻል መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
15 October 2019, 17:44