“አማዞን፣ የቤተክርስቲያን አዳዲስ እርምጃዎች ለተቀናጀ ስነ-ምዕዳር” ቅዱስ ሲኖዶስ በቫቲካን “አማዞን፣ የቤተክርስቲያን አዳዲስ እርምጃዎች ለተቀናጀ ስነ-ምዕዳር” ቅዱስ ሲኖዶስ በቫቲካን  

“አማዞን፣ የቤተክርስቲያን አዳዲስ እርምጃዎች ለተቀናጀ ስነ-ምዕዳር” ቅዱስ ሲኖዶስ

ከባለፈው መስከረም 25- ጥቅምት 16/2012 ዓ.ም ድረስ “አማዞን፣ የቤተክርስቲያን አዳዲስ እርምጃዎች ለተቀናጀ ስነ-ምዕዳር”  በሚል መሪ ቃል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት ሲኖዶስ በቫቲካን በመካሄድ ላይ ይገኛል። ይህ ሲኖዶስ “የዓለማችን ሳንባ” በመባል የሚታወቀውና 7.8 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎሜትር በሚሸፍነው የአማዞን ደን ክልል አዋሳኝ አገሮች ማለትም በብራዚል፣ በቦሊቪያ፣ በፔሩ፣ በኤኳዶር፣ በኮሎንቢያ፣ በቬንዙዌላ፣ በጉያና እና በሱሪናም አከባቢ የሚኖሩ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ትኩረት ባደረገ መልኩ እና የቤተክርስቲያኗን ዓለማቀፋዊነት በሚያንጸባርቅ መልኩ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተውጣጡ የካቶሊክ ቤተክርቲያን ብጹዐን ጳጳሳትን ባካተተ መልኩ ቅዱስ ሲኖዶስ በመካሄድ ላይ እንደ ሚገኝ ቀደም ባሉ ዘገባዎቻችን መግለጻችን ይታወሳል።

የእዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የአማዞን ደን አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል

ይህ የአማዞን ደን በአሁኑ ወቅት በምድራችን ላይ ከሚገኙ ደኖች መካከል 40% የሚሆነው የደን ሽፋን ይዞ እንደ ሚገኝ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ቅዱስ ሲኖዶስ በአሁኑ ወቅት በአማዞን ደን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተቃጣ የሚገኘው ጭፍጨፋ እና ውድመት 40% የሚሆነውን የምድራችን ጥቅጥቅ ደን የሚገኝበትን ይህንን አከባቢ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ውድመት እየቀየረው በመገኘቱ የተነሳና በእዚህም ሰበብ በአማዞን ደን ላይ ሕይወታቸው የተመሰረት በርካታ ሕዝቦች የኑሮዋቸው ዋስትና አደጋ ላይ መውደቁን በሰፊው በመዳሰስ በአማዞን ደን ላይ ሕይወታቸው የተመሰረተ ሕዝቦች ሕልውና ተጠብቆ ይቀጥል ዘንድ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ፣ ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ በተመለከተ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የራሷን በጎ የሆነ አስተዋጾ ለማስቀመጥ ታስቦ በመከናውን ላይ የሚገኝ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው።

“የአማዞን ሕዝቦች ድምጽ”

“የአማዞን ሕዝቦች ድምጽ” ለዓለም ለማሰማት ታስቦ በመከናውን ላይ የሚገኘው ይህ ቅዱስ ሲኖዶስ በአማዞን ደን ውስጥ እና በመዳረሻዎቹ ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች የስቃይ ድምጽ ለዓለም ማሰማት ይቻል ዘንድ የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን የራሷን አስተዋጾ ለማደረግ በማሰብ የምታደርገው ቅዱስ ሲኖዶስ ሲሆን የአማዞን ሕዝብ ከደኑ ከሚወጣው ውኃው፣ እንዲሁም ከፍጥረታትና የእንስሳት ዝርያዎች፣ ከሚፈሱት ታላላቅ ወንዞች ጋር ሕዝቡ ያለውን የጠበቀ የሕይወት፣ የባህል እና መንፈሳዊ ውህደት እና ትስስር፣ እንዲሁም እነዚህ ነገሮች በሕዝቡ ሕይወት ላይ ያላቸው አዎንታዊ ተፅዕኖ፣ በአማዞን ደን ዙሪያ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ቀደምት ሕዝቦች ዘር ከደኑ ጋር ያላቸው የጠበቀ ትስስር፣ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች፣ በአማዞን ዙሪያ በሚገኙ ወንዞች ላይ ኑሮዋቸውን የመሰረቱ ሕዝቦች አጠቃላይ የስቃይ ድምጽ የሚያስተጋባ ቅዱስ ሲኖዶስ ሲሆን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለእዚህ አሳሳቢ ችግር መፍትሄ ይሆን ዘንድ የራሷን አዎንታዊ አስተዋጾ ለማበርከት በማሰብ የሚደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው።

በአማዞን ደን ውስጥ እና አቅራቢያ የሚገኙትን ቀደምት ሕዝቦች ከቦታቸው ለማፈናቀል በተቀናጀ መልኩ ወንጀሎች እንደ ሚፈጸሙ፣ በእዚህም የተነሳ የሰዎች መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶቻቸው እየተጣሱ እንደ ሚገኙ በተለይም ደግሞ የዓለማችን ሐብት የሆኑት እስከ ዛሬ ድረስ ከሰዎች ጋር ተቀላቅለው የማያውቁ በደኑ ውስጥ የሚኖሩ ቀደምት ሕዝቦች ሕይወት አደጋ ላይ እየወደቀ ስለሚገኝ ለችግሩ ወቅታዊ የሆነ መፍትሄ በመፈለግ በአማዞን ደን አቅራቢያ እና በአዋሳኝ ዙሪያዎቹ አከባቢ የሚኖሩትን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን እና እንዲሁም መላውን የሰው ልጅ ለመታደግ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማቅረብ በማሰብ የሚደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው።

ምድራችንን ከጥፋት እንከላከል

ይህ “አማዞን፣ የቤተክርስቲያን አዳዲስ እርምጃዎች ለተቀናጀ ስነ-ምዕዳር” በሚል መሪ ቃል በመካሄድ ላይ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዐን ጳጳሳት ሲኖዶስ “የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን ከጥፋት እንዴት መከላከል እንደ ምንችል” ግንዛቤ ማስጨበጥ የሚችሉ ዝግጅቶች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ውስጥ በምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አማካይነት ቅድመ ዝግጅቶች ከተከናወኑ በኋላ እነዚህን ከዓለም ዙሪያ የተገኙትን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መልካም ተሞክሮዎችን እንደ ግብዐት በመጠቀም በአማዞን አከባቢ የሚኖሩ ሕዝቦችን ወቅታዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ባስገባ መልኩ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ በትጋት እየሠራ የሚገኝ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው።

ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ሁነኛ አስተዋጾ ያላደረጉ አገራት ተጎጂ ናቸው!

በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በቀዳሚነት ተጎጂ የሚሆኑት ደግሞ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ክስተት ሁነኛ አስተዋጾ ያላደረጉ በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን በተለይም ደግሞ የአማዞን ሕዝቦች ለብዙ አመታት ያህል ተገለው የኖሩ፣ እንዲሁም በከፍተኛ የድኽነት አረንቋ ስር የሚገኙ፣ በአከባቢያቸው የሚገኘው እና ለብዙ ሺህ አመታት ለእነዚህ ለአማዞን ሕዝቦች እና ለዘር ማንዘራቸው በመጠልያነት፣ የምግብ ምንጭ በመሆን በአጠቃላይ የሕይወታቸው ሕልውና የሆነው የአማዞን ጥቅጥቅ ደን በሕገወጥ እና ሕጋዊ በሆነ መንገድ እየተጨፈጨፈ ለተወሰኑ ሰዎች ከፍተኛ የገንዝብ ማግኛ ምንጭ ቢሆንም እነዚህ የአማዞን ሕዝቦች ግን በከፍተኛ የድኽነት አርቋ ሥር ሰለሚገኙ፣ የመኖር ሕልዋናቸው አደጋ ላይ በመውደቁም ጭምር፣ እንዲሁም የአማዞን ደን “የዓለማችን ሳንባ” በመባል የሚታወቅ በመሆኑ የእዚህ ደን አደጋ ላይ መውደቅ የአማዞን ሕዝቦች የመኖር ሕልውናቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ብቻ ሳይሆን የዓለም ሕዝቦች ሁሉ የመኖር ያለመኖር ህልውናቸው እና ዋስትናቸው በመሆኑ ጭምር “የጋራ መኖሪያ ቤታችንን እንከባከብ” በማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “የዓለማችን ሳንባ” በመባል የሚታወቀውን የአማዞን ደን እና እንዲሁም በዓለም ደረጃ በተመሳሳይ መልኩ የሚደረጉ የደን ጭፍጨፋዎችን እና በምድራችን ላይ የሚቃጣውን ማነኛውም አደጋ መከላከል ይቻል ዘንድ ለዓለም ድምጻቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።

በአማዞን ጉዳይ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ማድረግ ለምን አስፈለገ?

የአማዞን ሕዝቦች በአከባቢያቸው ላይ በከፍተኛ ደረጃ እየደረሰ የሚገኘውን የደን ጭፍጨፋ ለማስቆም በርካታ ጥረቶችን ማደረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ነገር ግን አከባቢያቸውን እና ደናቸውን እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ ለመታደግ ባለመቻላቸው የአማዞን ሕዝቦች የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እገዛ የጠየቁ ሲሆን ቤተክርስቲያን ኢየሱስ ወደ ዓለም በመጣበት ወቅት የሰው ልጆች ሁሉ በተለይም ድሆች ምልአት ያለው ሕይወት እንዲኖሩ ለማደረግ ወደ እዚህ ምድር እንደ መጣ ሁሉ ቤተክርስቲያን ይህንን የኢየሱስ ክርስቶስን ተልዕኮ የማስቀጠል ኃላፊነት ስለተጣለባት በእዚህ ረገድ  የአማዞን ሕዝቦች የሕይወት የኑሮ ዋስትና የሆነው የአማዞን ደን ላይ እየደረሰ የሚገኘው ከፍተኛ ውድመት ይቆም ዘንድ ቤተክርስቲያን የበኩሉዋን አስተዋጾ እንድታደርግ ጥሪ በማቅረባቸው የተነሳ በመካሄድ ላይ የሚገኝ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው።

“የዓለማችን ሳንባ” በመባል የሚታወቀው የአማዞን ደን 7.8 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎሜትር የሚሸፍን ክልል ሲሆን ብራዚል፣ ቦሊቪያ፣ ፔሩ፣ ኤኳዶር፣ ኮሎንቢያ፣ ቬንዙዌላ፣ ጉያና እና ሱሪናም የሚዋሰኑበት ስፊ ግዛት አቅፎ የያዘ ነው። ይህ የአማዞን ደን በአሁኑ ወቅት በምድራችን ላይ ከሚገኙ ደኖች መካከል 40% የሚሆነው የደን ሽፋን አቅፎ የያዘ አከባቢ እንደ ሆነም ይገለጻል።

የአማዞን ደን የያዘውን በርካታ የተፈጥሮ ሃብት ነዳጅ፣ የተፈጥሮ ጋዝ፣ ወርቅ እና ዛፎችም ላይ ብዙዎች እጃቸውን አስገብተዋል። በቦታው የሚኖሩ ሕዝቦች ሕይወት ያላገናዘበ የመንግሥት የተፈጥሮ ጥበቃ ፖሊሲዎች በነዋሪው ላይ ችግር እያስከተለ ይገኛል” በእዚህም የተነሳ መንግሥት ለእዚህ አንገብጋቢ ጥያቄዎች የአማዞን ደን የሚዋሰኑ አገራት መንግሥታት ለችግሩ ተገቢውን ምላሽ ይሰጡ ዘንድ ጥሪ የሚያቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 October 2019, 15:33