በእሳት ቃጠሎ ጉዳት የደረሰበት የፓሪስ ከተማ ካቴድራል፣ በእሳት ቃጠሎ ጉዳት የደረሰበት የፓሪስ ከተማ ካቴድራል፣ 

“የኖትር ዳም ካቴድራል መልሶ ግንባታ የስርዓት አምልኮ ማዕከላዊ ገጽታ መገለጫ ነው”።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፍራንቸስኮ ፎሎ፣ በፓሪስ ከተማ ኖትር ዳም ካቴድራል ላይ እየተከናወነ ያለው የመልሶ ግንባታ ሥራ የስርዓት አምልኮ ማዕከላዊ ገጽታ መገለጫ ነው ማለታቸው ታውቋል። ብጹዕ አቡነ ፍራንቸስኮ ፎሎ ለካቴድራሉ መልሶ ግንባታ እስካሁን 38 ሚሊዮን ዩሮ መሰብሰቡን እና ይህም 10 ከመቶ ብቻ መሁኑን አስታውቀዋል። የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፎሎ ፎሎ ይህን ያስታወቁት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የኖትር ዳም ካቴድራልን መልሶ የመገንባት ሥራን በበላይነት እንዲከታተል ለተሰየመው ለ “ዩኔስኮ” በላኩት መልዕክት መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የስርዓት አምልኮ ማዕከላዊ ገጽታ፣

በአዘርባጃን፣ ባኩ ከተማ ላይ ባሕላዊ እና የተፈጥሮ ቅርሶች አጠባበቅን አስመልክቶ በተደረገው ስብሰባ ላይ የተገኙት ብጹዕ አቡነ ፍራንቸስኮ ፎሎ የኖትር ዳም ካቴድራልን መልሶ ግንባታን በማስመልከት እንደተናገሩት ካቴድራሉ ለሚያምኑት፣ ለማያምኑት እንዲሁም በአጠቃላይ ለወደ ፊት ትውልድ በሙሉ ባሕላዊ ሃብት መሆኑን ገልጸው፣ የስርዓተ አምልኮ ማዕከላዊ ገጽታ መገለጫም ነው ብለዋል።

ካቴድራሉ የቤተ ክርስቲያን፣ የፓሪስ የሰው ልጅ ሁሉ ሃብት ነው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለፓሪስ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት በላኩት መልዕክታቸው በመልሶ ግንባታ ሥራ አማካይነት በእሳት ቃጠሎ ጉዳት የደረሰበት የፓሪስ ከተማ ካቴድራል ወደ ቀድሞ ስፍራው በመመለስ ለእናት ቤተ ክርስቲያን፣ ለፓሪስ ሀገረ ስብከት ለፈረንሳይ ሕዝብ እና ለሰው ልጅ በሙሉ የእምነት ምልክት ነው ማለታቸውን ብጹዕ አቡነ ፍራንቸስኮ ፎሎ አስታውሰዋል።

የካቴድራሉን ስም ለረጅም ዘመናት ማቆየት ያስፈልጋል፣

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፍራንችስኮ ፎሎ የካቴድራሉን የመልሶ ግንባታ ሂደት አስመልክተው ባደረጉት ንግግር የካቴድራሉ መንፈሳዊ ስፍራነቱ እና የስርዓተ አምልኮ ማዕከላዊ ገጽታ መገለጫነቱ ተጠብቆ ይኖራል ብለው በመሆኑም በካቴድራሉ የሚፈጸም የአምልኮ ሥርዓት ቀጣይነት ይኖረዋል፣ ካቴድራሉ ይዞት የዘለቀው መንፈሳዊ ቅርስነት እንደነበረ ሆኖ እንዲቆይ ለማድረግ መልሶ መገንባቱ መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።

የዕርዳታ ማሰባሰብ ሥራ ጥሩ እየተከናወነ ነው፣

የእርዳታ ማሰባሰብ ሥራው በጥሩ ሁኔታ መቀጠሉን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ፍራንቸስኮ ፎሎ፣ ካቴድራሉን መልሶ ለመገንባት ከታሰበው የገንዘብ መጠን፣ እንደ ፓሪስ ከተማ ሊቀ ጳጳሳስ ገለጻ መሠረት 38 ሚሊዮን ዩሮ የተሰበሰበ መሆኑን ገልጸው 850 ሚሊዮን ዩሮ ደግሞ ቃል የተገባለት መሆኑን አሳታውቀዋል። የገንዘብ እርዳታዎችን ለመቀበል ረጅም ሂደቶች ቢኖሩም ካቴራሉን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል በቂ የገንዘብ መጠን እንደሚገኝ የፓሪስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኡፔቲት መናገራቸው ታውቋል።

በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ውስጥ የሚገኝ የኖትር ዳም ካቴድራል በዓለም ታዋቂ የአምልኮ ሥፍራ፣ እ. አ. አ 1991 ዓ. ም. እንደ ታሪካዊ ቅርስነት በዩኔስኮ የተመዘገበ ሕጋዊ የፈረንሳይ መንግሥት ንብረት መሆኑ ይታወቃል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
10 July 2019, 15:34