“አማዞን፣ የቤተክርስቲያን አዳዲስ እርምጃዎች ለተቀናጀ ስነ-ምዕዳር” በሚል መሪ ቃል ሲኖዶስ ሊካሄድ

በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የአየር ንብረት ለውጥ እየተከሰተ እንደ ሚገኝ ይታወቃል።  በላቲን ቋንቋ “Laudato si” በአማርኛው ውዳሴ ለአንተ ይሁን በሚል አርዕስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በግንቦት 24/2011 ዓ.ም ለንባብ ያበቁ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ የሆነበት 4ኛው ዓመት በኢትዮጲያ የቀን አቆጣጠር ባለፈው ግንቦት 16/2011 ዓ.ም ተዘከሮ አልፉዋል። በዚህ ሐዋርያዊ መልእክታቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን እንከባከብ” በሚል ጭብጥ ዙሪያ ላይ የዛሬ 4 አመት ገደማ ያፋ ያደርጉት ሐዋርያዊ መልእክት ሲሆን በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ በዓለማችን ላይ የሚታየው የአየር ንብረት ለውጥ መንስሄ ምድራችንን ያለ አግባቡ በመበዝበዛችን፣ ከባቢ አየርን ሊበክሉ የሚችሉ ንጥረ ነገሮችን፣ ጋዞችን ወደ ከባቢ በመልቀቃችን በመሳሰሉ ጉዳዮች የተከሰተ እና የጋራ የመኖርያ ቤታችንን አደጋ ላይ የጣለ ክስተት በመሆኑ ክስተቱን ለመግታት ባለድርሻ አካላት የራስቸውን ሚና መጫወት ይገባቸዋል የሚል ጭብጥ ያለው ሐዋርያዊ መልእክት እንደ ሆነ ይታወሳል።

የእህዚ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በላቲን ቋንቋ “Laudato si” በአማርኛው ውዳሴ ለአንተ ይሁን በሚል አርዕስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በግንቦት 24/2011 ዓ.ም ለንባብ ያበቁ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ የሆነበት 4ኛው ዓመት በኢትዮጲያ የቀን አቆጣጠር ባለፈው ግንቦት 16/2011 ዓ.ም ተከብሮ ባለፈበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት “ምድራችን በልቅሶ ላይ ናት” በሚልው ንዑስ አርእስት ስር የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈው እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ እንዲህ ብለው ነበር . . .

“በእዚህ መልእክቴ ቀደም ሲል ያደረኩትን ንግግር በድጋሜ በማስታወስ “በእዚህ ምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በመክራ ውስጥ የሚገኙ ድሆችን እና በአከባቢ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን በድጋሜ ማስታወስ እፈልጋለሁኝ”። እግዚኣብሔር የተትረፈረፈ የአትክልት ሥፍራን ሰጠን ነገር ግን እኛ ወደ ባድማነት እና የትርኪሚርኪ መጣያ፣ ወደ ተበከለ የቆሻሻ መጣያ ሥፍራነት ቀየርናት”። በምድራችን ስነ-ምዕዳር እና የተመጋጋቢነት ሂደት ላይ ኋላፊነት በጎደለው መልኩ እና በእራስ ወዳድነት መንፈስ እየደረሰ የሚገኘውን ውድመት በግድየለሽነት ስሜት ወይም በዝምታ መመልከት አይኖርብንም። “ምክንያቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዝርያዎች እየጠፉ በሚመጡበት ወቅት በመኖራቸው ምክንያት እነርሱን በማየት ለፈጣሪ የምንሰጠው ምስጋና እየቀነሰ ስለ ሚመጣ እና ይህንን የማድረግ መብትም ስለሌለን ጭምር ነው።

በዓለማችን ድርቅ፣ ጎርፍ፣ እሳት እና ያልተለመደ የአየር ንብረት ለውጥ እዲኖር እያደረገ ይገኛል። የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ለስደተኞች ፍሰት ቀውስ ከፍተኛ የሆነ ድርሻ አበርክቱኋል። በዓለም ውስጥ የሚኖሩ ድሆች ኋላፊነት በማይሰማቸው ሰዎች አማካይነት ድህነት ከደቀንባቸው መከራ ባሻገር በአለም የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከድጥ ወደ ማጡ እየወረዱ ይገኛሉ።

 የተመጣጠን የስነ-ምዕዳር ሂደት እንደ ሚያሳየው የሰው ልጆ ከተፈጥሮ ጋር ጥብቅ የሆነ ግንኙነት እንዳለው ነው። ስለእዚህም ተፈጥሮን መበደል ማለት የሰው ልጆችን መበደል ማለት ነው። በተመሳሳይ መልኩ እያንዳንዱ ፍጥረት የራሱ የሆነ ተፈጥሮኋዊ እሴቶች አሉት ይህም ሊከበር ይገባዋል። “ምድራችን እና ድሆች እያሰሙ የሚገኙትን ለቅሶ ችላ አንበል” ተገቢ እና ወቅታዊ ምላሽ እንዲገኝ የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል።

በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በቀዳሚነት ተጎጂ የሚሆኑት ደግሞ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ክስተት ሁነኛ አስተዋጾ ያላደረጉ በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን በተለይም ደግሞ የአማዞን ሕዝቦች ለብዙ አመታት ያህል ተገለው የኖሩ፣ እንዲሁም በከፍተኛ የድኽነት አረንቋ ስር የሚገኙ፣ በአከባቢያቸው የሚገኘው እና ለብዙ ሺ አመታት ለእነዚህ ለአማዞን ሕዝቦች እና ለዘር ማንዘራቸው በመጠለያነት፣ የምግብ ምንጭ በመሆን በአጠቃላይ የሕይወታቸው ሕልውና የሆነው የአማዞን ጥቅጥቅ ደን በሕገወጥ እና ሕጋዊ በሆነ መንገድ እየተጨፈጨፈ ለተወሰኑ ሰዎች ከፍተኛ የገንዝብ ማግኛ ምንጭ ቢሆንም እነዚህ የአማዞን ሕዝቦች ግን በከፍተኛ የድኽነት አርቋ ሥር ሰለሚገኙ፣ የመኖር ሕልዋናቸው አደጋ ላይ በመውደቁም ጭምር፣ እንዲሁም የአማዞን ደን “የዓለማችን ሳንባ” በመባል የሚታወቅ በመሆኑ የእዚህ ደን አደጋ ላይ መውደቅ የአማዞን ሕዝቦች የመኖር ሕልውናቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ብቻ ሳይሆን የዓለም ሕዝቦች ሁሉ የመኖር ያለመኖር ህልውናቸው እና ዋስትናቸው በመሆኑ ጭምር “የጋራ መኖሪያ ቤታችንን እንከባከብ” በማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “የዓለማችን ሳንባ” በመባል የሚታወቀውን የአማዞን ደን እና እንዲሁም በዓለም ደረጃ በተመሳሳይ መልኩ የሚደረጉ የድን ጭፍጨፋዎችን እና በምድራችን ላይ የሚቃጣውን ማነኛውም አደጋ መከላከል ይቻል ዘንድ ለዓለም ድምጻቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።

በቅርቡ በከፍተኛ ደረጃ በአደጋ ላይ የሚገኙትን የአማዞን ሕዝቦች እና መልካ ምድራቸው ከተጋረጠበት ከፍተኛ አደጋ ለመታደግ በማሰብ አማዞንን የተመለከተ አንድ ሲኖዶስ እንደ ሚዘጋጅ የተገለጸ ሲሆን ለእዚህ ሲኖዶስ አገልግሎት የሚውል ቅድመ ጥናቶች በመደረግ ላይ እንደ ሚገኙ ለቫቲካን ሬዲዮ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ከቤተክርስቲያን ጋር በመሆን በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦችን ጩኸት እናዳምጥ በሚል መርህ ዙሪያ የቅድመ ዝግጅት ውይይት በቫቲካን በመካሄድ ላይ ይገኛል። የአማዞን ሕዝቦች በአከባቢያቸው ላይ በከፍተኛ ደረጃ እየደረሰ የሚገኘውን የደን ጭፍጨፋ ለማስቆም በርካታ ጥረቶችን ማደረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ነገር ግን አከባቢያቸውን እና ደናቸውን እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ ለመታደግ ባለመቻላቸው የአማዞን ሕዝቦች የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እገዛ የጠየቁ ሲሆን ቤተክርስቲያን ኢየሱስ ወደ ዓለም በመጣበት ወቅት የሰው ልጆች ሁሉ በተለይም ድሆች ምልአት ያለው ሕይወት እንዲኖሩ ለማደረግ ወደ እዚህ ምድር እንደ መጣ ሁሉ ቤተክርስቲያን ይህንን የኢየሱስ ስክርስቶስን ተልእኮ የማስቀጠል ኃላፊነት ስለተጣለባት በእዚህ ረገድ  የአማዞን ሕዝቦች የሕይወት የኑሮ ዋስትና የሆነው የአማዞን ደን ላይ እየደረሰ የሚገኘው ከፍተኛ ውድመት ይቆም ዘንድ ቤተክርስቲያን የበኩሉዋን አስተዋጾ እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል። በእዚህም መሰረት በእዚህ ጉዳይ ዙሪያ በቅርቡ “አማዞን፣ የቤተክርስቲያን አዳዲስ እርምጃዎች ለተቀናጀ ስነ-ምዕዳር”  በሚል መሪ ቃል ለሚደርገው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዐን ጳጳሳት ሲኖዶስ ግብዐት ይሆን ዘንድ ቅድመ ዝግጅት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በቅርቡ የአማዞን ሕዝቦችን እና የአማዞን ድን በተመለከተ ለሚደረገው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዐን ጳጳሳት ሲኖዶስ የሚያገለግል የቅድመ ዝግጅት ሰነድ በሰኔ 10/2011 ዓ.ም በቫቲካን ይፋ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይህ የቅድመ ዝግጅት ሰነድ ርዕሰ ሊቃን ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ከጥር 10-13/2010 ዓ.ም. በፔሩ አድርገውት በነበረው 22ኛው ሐዋሪያዊ ግብኝት ከአማዞን ሕዝቦች ጋር በተገናኙበት ወቅት . . .

“የአማዞን መሬት ለያዘው ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት እና ሕዝብ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ከአመታት ወዲህ የአማዞን ሕዝብ ሸክም ከባድ እየሆነ መምጣቱ የሚታይ ነው። ወደዚህ ሥፍራ እንድመጣ ከገፋፉኝ ምክንያቶች አንዱም ይህ ስለሆነ ሸክማችሁን ለመጋራት፣ ችግራችሁን በማዳመጥ፣ በአካባቢያችሁ፣ በሕይወታችሁና በባሕላችሁ ላይ የሚመጣውን ጥቃት ከመላዋ ቤተክስቲያን ጋር ሆነን ለመመከት ያለኝን ልባዊ ፍላጎቴን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። በአማዞን ሕዝብ ታሪክ ውስጥ፣ ሕዝቡ የዛሬን ያህል የከፋ ጊዜ ገጥሞት አያውቅም። የአማዞን ግዛት በተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቃት እየደረሰበት እንደሆነ ይስተዋላል።

በወቅቱ ቅዱስነታቸው በስፍራው ተገኝተው የሁኔታውን አሰክፊነት በዓይናቸው በማየታቸው የተነሳ ይህ የቅድመ ዝግጅት ሰነድ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር እና እንዲሁም የአማዞን ደን የሚያዋስናቸው አገራት ሕዝቦች ጋር በተደጋጋሚ ጉዳዩን በተመለከተ ውይይት ከተደረገ በኋላ ይፋ የሆነ የቅድመ ዝግጅት ሰነድ እንደ ሆነ በመግለጫው ተጠቅሱዋል።

“የዓለማችን ሳንባ” በመባል የሚታወቀው የአማዞን ደን 7.8 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎሜትር የሚሸፍን ክልል ሲሆን ብራዚል፣ ቦሊቪያ፣ ፔሩ፣ ኤኳዶር፣ ኮሎንቢያ፣ ቬንዙዌላ፣ ጉያና እና ሱሪናም የሚዋሰኑበት ስፊ ግዛት አቅፎ የያዘ ነው። ይህ የአማዞን ደን በአሁኑ ወቅት በምድራችን ላይ ከሚገኙ ደኖች መካከል 40% የሚሆነው የደን ሽፋን በአማዞን የተያዘ ነው።

የአማዞን ሕዝቦች ድምጽ

የእዚህ የቅድመ ዝግጅት ሰንድ የመጀምሪያ ክፍል “የአማዞን ሕዝቦች ድምጽ” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲሆን በአማዞን ደን ውስጥ እና በመዳረሻዎቹ ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች የስቃይ ድምጽ አካቶ የያዘ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የአማዞን ሕዝብ ከደኑ ከሚወጣው ውኃው እና እንዲሁም ከፍጥረታትና የእንስሳት ዝርያዎች፣ ከሚፈሱት ትላልቅ ወንዞች ጋር ሕዝቡ ያለውን የጠበቀ የሕይወት፣ የባህል እና መንፈሳዊ ውህደት እና ትስስር፣ እንዲሁም እነዚህ ነገሮች በሕዝቡ ሕይወት ላይ ያላቸው አዎንታዊ ተፅዕኖዎች፣ በአማዞን ደን ዙሪያ የሚኖሩ በሽዎች የሚቆጠሩ ቀድምት ሕዝቦች ዘር ከደኑ ጋር ያላቸው የጠበቀ ትስስር፣ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አድሮች፣ በአማዞን ዙሪያ በሚገኙ ወንዞች ላይ ኑሮዋቸውን የመሰረቱ ሕዝቦች አጠቃላይ የስቃይ ድምጽ የሚያስተጋባ የሰነዱ የመጀርያ ክፍል ነው።

በአደጋ ላይ ያለ ሕይወት

በአማዞን ደን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተቃጣ የሚገኘው ጭፍጨፋ እና ውድመት 40% የሚሆነውን የምድራችን ጥቅጥቅ ደን የሚገኝበትን ይህንን አከባቢ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ውድመት እየቀየረው እንደ ሚገኝ የሚያወሳው ሰንዱ በእዚህም የተነሳ በአማዞን ድን ላይ ሕይወታቸው የተመሰረት በርካታ ሕዝቦች የኑሮዋቸው ዋስትና አደጋ ላይ መውደቁን በሰፊው በሰነዱ ውስጥ ተካቶ ይገኛል። በአማዞን ደን ውስጥ የሚገኙትን ቀደም ሕዝቦች ከቦታቸው ለማፈናቀል በተቀናጀ መልኩ ወንጀሎች እንደ ሚፈጸሙ የሚያወሳው ሰንዱ በእዚህም የተነሳ የሰዎች መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶቻቸው እየተጣሱ እንደ ሚገኙ በተለይም ደግሞ የዓለማችን ሐብት የሆኑት እስከ ዛሬ ድረስ ከሰዎች ጋር ተቀላቅለው የማያውቁ በደኑ ውስጥ የሚኖሩ ቀድምት ሕዝቦች ሕይወት አደጋ ላይ እየወደቀ እንደ ሚገኝ በሰፊው የሚዘረዝር ሰነድ ነው።

የምድራችን እና የድሆች ጩኸት

የቅድመ ሰነዱ ሁለተኛ ክፍል ውስጥ ደግሞ በምድራችን ላይ በተቃጣው ከፍተኛ አደጋ የተነሳ ምድራችን እና ሕዝቦቿ በመጮኽ ላይ ይገኛሉ የሚል እንድምታን ያዘለ ሰነድ ሲሆን ይህንን ችግር ከተቻለ ለማስወገድ ካልሆነ ለመቀነስ ይችላ ዘንድ የሚረዱ አንዳንድ አስተያየቶችን አቅፎ የያዘ የሰነዱ ክፍል ነው። በእዚህም መሰረት የምድራችንን እና የሕዝቦቿን በተለይም የድሆን ጩኸት ለመቀነስ ይቻል ዘንድ የተቀናጀ የስነ-ምዕዳር አሰራሮችን መከተል እንደ ሚገባ የሚያትት የሰነዱ ክፍል የሚገኝበት ነው።

የአማዞን መሬት የያዘውን በርካታ የተፈጥሮ ሃብት ነዳጅ፣ የተፈጥሮ ጋዝ፣ ወርቅ እና ዛፎችም ላይ ብዙዎች እጃቸውን አስገብተዋል። የቦታውን ሕዝቦች ሕይወት ያላገናዘበ የመንግሥት የተፈጥሮ ጥበቃ ፖሊሲዎች በነዋሪው ላይ ችግር እያስከተለ ይገኛል” በእዚህም የተነሳ መንግሥት ለእዚህ አንገብጋቢ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይገባዋል የሚል አንቀጾች የተካተቱበት የሰነዱ ክፍል ነው።

19 June 2019, 15:10