የደቡብ ሱዳን ተፈናቃዮች፣ የደቡብ ሱዳን ተፈናቃዮች፣ 

በደቡብ ሱዳን ሰላም፣ ሰብዓዊ ክብር እና የወንጌል አገልግሎት ተግባራዊ እንዲሆን ያስፈልጋል።

በደቡብ ሱዳን ሰብዓዊ ክብር ተጠብቆ፣ ሰዎች በሰላም እና በአንድነት መኖራቸውን ማየት የቅድስት መንበር ምኞት እንደሆነ በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር በጁባ ከተማ 1,500 ተማሪዎችን በማስተናገድ ላይ በሚገኝ ካቶሊካዊ ዩኒቨርስቲ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በደቡብ ሱዳን እየተደረገ ያለው የሰላም ጥረት ፍሬያማ እንዲሆን ቅድስት መንበር የበኩሏን እገዛ በማበርከት ላይ መሆኗ ተገለጸ። ከመጋቢት 12 ቀን እስከ መጋቢት 16 ቀን 2011 ዓ. ም. ደቡብ ሱዳንን የጎበኙት በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር እንደገለጹት በደቡብ ሱዳን የሰላም ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ሰብዓዊ ክብር እና የወንጌል አገልግሎት ተግባራዊ እንዲሆን ቅድስት መንበር የበኩሏን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኗን አስታውቀዋል።

የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚደንት ሪክ ማቻር፣

ብጹዕ አቡነ ጋላገር የደቡብ ሱዳን ሕዝቦችን ወደ እርቅ የሚያደርሱ የሰላም ውይይቶች እንደሚያስፈልጉ እና ቅድስት መንበርም በመደረግ ላይ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የራሷን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኗን ኦዝርቫቶሬ ሮማኖ ለተሰኘ የቅድስት መንገር ጋዜጣ ተናግረዋል። የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ በያዝነው  ሳምንት አጋማሽ ላይ እንዳስታወቁት ሁለቱ የደቡብ ሱዳን መንግሥት መሪዎች፣ ክቡር ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ምክትል ፕሬዚደንት ሪክ ማቻር በሚቀጥለው ሳምንት በቫቲካን ከተማ ሱባኤን ለመግባት እቅድ መያዙን ገልጸዋል።      

በሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር የተመራ የቅድስት መንበር ልኡካን በመጋቢት 16 ቀን 2011 ዓ. ም. ወደ ደቡብ ሱዳን ሲደርስ የደቡብ ሱዳን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ተወካዮች እና የተቋማት መሪዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር ከደቡብ ሱዳን ብጹዓን ጳጳሳት ጋር በሃገሪቱ በመካሄድ ስላለው ሐዋርያዊ አገልግሎት፣ ከአጎራባች አገሮች ጋር ስላሉ ግንኙነቶች እና ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ስለሚታዩ የእርስ በእርስ ግጭቶችን አስመልክተው መወያየታቸው ታውቋል። የደቡብ ሱዳን ብጹዓን ጳጳሳት በውይይታቸው ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለደቡብ ሱዳን ሰላም እና እርቅ ለሚሰጡት ትኩረት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የደቡብ ሱዳን ብጹዓን ጳጳሳት በጥር ወር 2011 ዓ. ም. በዋና ከተማ ጁባ ላይ ባካሄዱት ጠቅላላ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ይፋ ባደረጉት መልዕክታቸው በኢትዮጵያ መዲና በአዲስ አበባ፣ በኢትዮጵያ፣ በሰሜን ሱዳን፣ በኡጋንዳ እና በኬንያ አደራዳሪነት፣ ሁለቱ የደቡብ ሱዳን መሪዎች ክቡር ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ምክትል ፕሬዚደንት ሪክ ማቻር የፈረሙትን የሰላም ስምምነት አስታውሰዋል።

ለሰላም ጥረት የሚደረግ ድጋፍ፣

የቅድስት መንበር ልዑካን ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ከከፍተኛ የመንግሥት አካላት ጋር ባደረገው ውይይት የደብቡ ሱዳን መንግሥት ከቅድስት መንበር ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላት ጠቅሰው በመጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ. ም. የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ቫቲካንን መጎብኘታቸውን አስታውሰዋል። የደቡብ ሱዳን የምትገኝበትን ጠቅላላ ሁኔታ በግልጽ የተወያዩት የሁለቱ መንግሥታት ተወካዮች፣ በፖለቲካ ተቀናቃኞች እና በመንግሥት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ የሚሆነበትን መንገድ እንደሆነ ሲታወቅ ቅድስት መንበርም ለስኬማነቱ የበኩሏን ድጋፍ እንደምታድረግ ማረጋገጧ ታውቋል። 

በደቡብ ሱዳን ሰብዓዊ ክብር ተጠብቆ፣ ሰዎች በሰላም እና በአንድነት መኖራቸውን ማየት የቅድስት መንበር ምኞት እንደሆነ በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር በጁባ ከተማ 1,500 ተማሪዎችን በማስተናገድ ላይ በሚገኝ ካቶሊካዊ ዩኒቨርስቲ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር በጁባ በተገኙበት ወቅት የፍትህ እና ሰላም ማዕከል ግንባታ የመጀመሪያ ድንጋይ የባረኩ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው የተመሠረተበት አስረኛ ዓመት መታሰቢያ የሚያበስር ዛፍ መትከላቸው ታውቋል። ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር በጁባ ከተማ በሚገኘው የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤትም ተገኝተው፣ የደቡብ ሱዳን የጸጥታ ጉዳይ ምክር ቤት ፕሬዚደንት በሆኑት በወይዘሮ አንጀሊና ቴኒ የተመሩትን የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ነጻ አውጪ እንቅስቃሴ መሪዎች ጋር ተገናኝተው በመስከረም ወር 2011 ዓ. ም. ስለ ተፈረመው የሰላም ስምምነት መወያየታቸው ታውቋል።

­­­ስደተኞችን እና ተፈናቃዮችን በተመለከተ፣

በጁባ ከተማ አቅራቢያ በርካታ ተፈናቃዮች በሚገኙበት መጠለያ ካምፕ አጠገብ በሚገኝ በቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ተገኝተው ለዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና መምህራን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን የመሩት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር፣ ወጣቶች የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በታማኝነት በመከተል እርሱ ለመሠረታት ቤተክርስቲያን የቸርነት አገልግሎትን ማበርከት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ከዚህም ጋር አያይዘው በአገሪቱ ውስጥ በጦርነት እና በአመጽ ምክንያት የተፈናቀሉ ባሁኑ ወቅት በተባበሩት መንሥታት ድረጅት እርዳታን በማግኘት ላይ የሚገኙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው የጸሎት ስነ ስርዓት ላይ ከተፈናቃዮች የቀረቡትን ምስክርነቶች እና ከፍራችስካዊያን ኣና ከኮብምቦን ማሕበር አባላት የቀረቡትን የተስፋ ንግግር ያዳመጡት ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር ለምዕመናኑ በሙሉ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተላከላቸውን ሐዋርያዊ ቡራኬ አድርሰዋል። ባሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን ውስጥ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ 2. 1 ሚሊዮን ሰዎች መኖራቸው እና ወደ አጎራባች አገሮች የተሰደዱ 2.5 ሚሊዮን ተፈናቃዮች መኖራቸው ታውቋል።

ጥላቻን እና የጦር መሣሪያን ማስወገድ ያስፈልጋል፣

በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር ከቀድሞ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ከጆን ጋራንግ ባለቤት ከእርብቃ ኛደንግ እና በአገሪቱ ከሚገኙ የተለየዩ አገሮች ዲፕሎማሲ አካላት ጋር መገናኘታቸው ታውቋል። ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር በጁባ ከተማ በሚገኘው የሕጻኑ ኢየሱስ ቅስድስት ተሬዛ ካቴድራል ተገኝተው የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት የመሩ ሲሆን በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት እና የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር መካፈላቸው ታውቋል። ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ጋላገር በመስዋዕተ ቅዳሴው የጸሎት ስነ ስርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር፣ ልብን ለመልካም ዓላማ በማዘጋጀት፣ ሰላምን እና ጠቅላላ ማሕበራዊ እድገትን ለማምጣት ይቅርታ እና ግልጽ ውይይትና በማድረግ ጥላቻን እና የጦር መሣሪያን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ለሕዝብ መራራት እንደሚያስፈልግ፣

በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር የደቡብ ሱዳን ጉብኝታቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልዕክተኛ ከሆኑት አቶ ዴቪድ ሺረር ጋር በፖለቲካ እና በጸጥታው መስክ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የሥራ ድርሻን አስመልክተው መወያየታቸው ታውቋል። ከደቡብ ሱዳን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ካህናት ጋር ተገናኝተው በወንጌል አገልግሎት ስርጭት እና የተረጋጋ ማሕበራዊ ኑሮን መልሶ ለማምጣት በሚቻልባቸው መንገዶች ተውያይተውቃል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪሪን በቫቲካን ተቀብለው ባነጋገሯቸው ጊዜ ወደ ደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ምኞት እንዳላቸው መግለጻቸውን አስታውሰዋል።        

06 April 2019, 17:15