ስለ ማሕበራዊ ኑሮ የሚገልጽ መጽሐፍ ስለ ማሕበራዊ ኑሮ የሚገልጽ መጽሐፍ 

የማሕበራዊ ኑሮ አለመመጣጠን በር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እይታ በሚል አርዕስት መጽሐፍ ታተመ።

በብሉይ ኪዳን ዘመን ለስደተኛ ልዩ አክብሮት ይሰጠው እንደነበር አስታውሰው ዛሬ ግን ለአንድ ስደተኛ ሊሰጠው የሚገባ ክብር መቀነሱን ገልጸዋል። የረጅም ጊዜ ታሪክን መለስ ብሎ መመልከቱ ከስሕተታችን እንድንማር እና ለችግሮቻችን መፍትሄን ለማግኘት ያግዛል ብለው የእግዚአብሔር ቃል ለችግሮች በሙሉ መልስ የሚገኝበት ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም በሚገኝ ላ ሳፔንሳ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የጂኦግራፊ መምህር እና ደራሲ የሆኑት ፕሮፌሰር ጂኖ ደ ቨኪስ፣ የማሕበራዊ ኑሮ አለመመጣጠን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እይታ በሚል አርዕስት አንድ መጽሐፍ ለንባብ ማብቃታቸው ተገለጸ። የመጽሐፋቸው ይዘት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ የአገልግሎት ዓመታት ሲያቀርቧቸው በቆዩት አስተምህሮች እና መልዕክቶች ላይ መሠረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል።

የምጣኔ ሃብት ቀውስ በስፋት በሚታይበት ባሁኑ ጊዜ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ የማሕበራዊ ኑሮ አለመመጣጠን አስመልክተው በተለያዩ አጋጣሚዎች መናገራቸው ይታወሳል። የምጣኔ ሃብት የበላይነት፣ ከሰው ልጅ ይልቅ ለሐብት ክምችት የበለጠ ዋጋን መስጠት፣ በቂ የጤና አገልግሎትን ለተወሰኑት ሰዎች ብቻ ማዳረስ የሚሉትን እና ሌሎች ተመሳሳይ ርዕሠ ጉዳዮችን፣ በሆንዱራስ የቴጓሲጋልፓ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል ሮድሪገስ ማራዲያጋ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ መጥቀሳቸው ታውቋል።

የመጽሐፉ ሃሳብ ውዳሴ ላንተ ይሁን ከሚለው መልዕክት ይመነጫል፣                  

ፕሮፌሰር ጂኖ ደ ቨኪስ ለንባብ ባበቁት መጽሐፋቸው ማሕበራዊ ኑሮን፣ ስደትን እና ድህነትን አስመልክተው አዳዲስ ሃሳቦችን ማፍለቃቸው ታውቋል። ፕሮፌሰ ደ ቨኪስ መጽሐፋቸውን ለማሳተም ምክንያት የሆናቸውን ነጥብ ከሁሉም በላይ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት እንደሆነ ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የማሕበረሰብን የኑሮ አለመመጣጠን በሦስት መንገድ ተመልክተዋል ያሉት ፕሮፌሰር ደ ቨኪስ የአካባቢ ጥበቃ፣ ድህነት እና ማሕበራዊ ሕይወት እንደሆኑ ገልጸው እነዚህ ሦስቱ በአንድነት ካለመታያቸው የተነሳ ለኤኮኖሚ ቀውስ እና ለማሕበራዊ ሕይወት አለመመጣጠን እንደ ዋና ምክንያት ሊወሰዱ ይችላሉ ብለው ነገር ግን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህን ሦስቱን ርዕሠ ጉዳዮች አንድ አድርገው መመልከታቸውን ገልጸዋል። በማሕበራዊ ሕይወት የሰዎች ኑሮ አለመመጣጠን ኤኮኖሚያዊ ይዘት ቢኖረውም ማሕበራዊ እና ባሕላዊ ይዘቶች እናዳሉበት ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በምድራችን የፍጥረታት ጩሄት ባሉት ሃሳባቸው መካከል የሰው ልጅ የድህነት ሕይወትንም አካትተዋል ብለዋል። ምክንያቱም ስለ ምጣኔ ሃብት ሲነሳ በድህነት ሕይወት የሚሰቃዩት የዓለማችን ሰዎች ተረስተው ይቀራሉ ብለዋል።

ስደትን ለማስታወስ ያለፈውን ታሪክ መመልከት ያስፈልጋል፣

በሮም ከተማ በሚገኝ በግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ የሆኑት ኑሪያ ካልዱክ ቤናገስ ስደትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጋር አገናዝበው ባቀረቡት ገለጻቸው ምንም እንኳን የጊዜ፣ የቦታ እና የባሕል ልዩነቶች ቢኖሩም ስደትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጋር አዛምዶ መመልከት ያስፈልጋል ብለዋል። ክስተቱ ዛሬም ቢሆን ተመሳሳይነት እንዳለው ያስረዱት ኑሪያ ካልዱክ፣ በስደት ላይ የሚገኙ የዘመናችን ሰዎች ችግሮች ከብሉይ ኪዳን ዘመን ችግሮች ጋር ተመመሳሳይነት እንዳላቸው አስረድተዋል። በብሉይ ኪዳን ዘመን ለስደተኛ ልዩ አክብሮት ይሰጠው እንደነበር አስታውሰው ዛሬ ግን ለአንድ ስደተኛ ሊሰጠው የሚገባ ክብር መቀነሱን ገልጸዋል። የረጅም ጊዜ ታሪክን መለስ ብሎ መመልከቱ ከስሕተታችን እንድንማር እና ለችግሮቻችን መፍትሄን ለማግኘት ያግዛል ብለው የእግዚአብሔር ቃል ለችግሮች በሙሉ መልስ የሚገኝበት ነው ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

         

05 March 2019, 15:07